Sunday, May 22, 2016

የመጨረሻው ቃል

እግዚአብሔር፣ ለሚወዱትና እንደ ሐሳቡ ለተጠሩት፣ ነገር ሁሉ ተያይዞ ለበጎ እንዲሠራ እንደሚያደርግላቸው እናውቃለን። ወደ ሮሜ ሰዎች 8:28

በእግዚአብሔር ተማምኖ የሚኖር ምንም አይነት መከራ ውስጥ አያልፍም ብሎ ማሰብ ቃሉን አለማወቅ ሲሆን ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ተማምኖ የሚኖር ሰው በመከራ ውስጥ ሲያልፍ ጠላት ምን ቢለፋ ምን በእርሱ ላይ የመጨረሻውን ቃል ሊናገር እንደማይችል መናገር ግን እውነት ነው። በውጣ ወረድ ውስጥ አልፈን ስንወጣ እግዚአብሔርን ይበልጥ አውቀነው ብቻ ሳይሆን ሁሌም እርሱ የተናገርው ብቻ እና ብቻ በሕይወታችን እንደሚፈፀምም አውቀን ነው የምንወጣው። እርሱ ደግሞ ለኛ ያለው ዕቅድ በጎና ፍፃሜው ያማረ እንጂ ተጀምሮ የሚቀር አይደለም። ስለዚህ በወጀብ ውስጥ ስናልፍ ወጀቡ ድምፅ መሃል የአምላካችንን ድምፅ አጥርተን መስማት ብቻ ሳይሆን የምንማረው ፤ አንደኛ እርሱ በወጀቡ ውስጥም አብሮን እንዳለ፣ ሁለተኛ ወጀብን የሚያዝ አምላክ እንዳለን እናረጋግጣለን፣ ሦስተኛ ከእርሱ ቃል ይውጣ እንጂ የማይታዘዝ እንደሌለ እንማራለን። እርሱ ይሁን ካለ ከመፈፀም የሚከለክለው አንዳች ነገር የለም። እያንዳንዱን እንቅፋት እርሱ የመወጣጫ ደረጃ ያደርገውና እርሱ ወዳየልን በፍጥነት ያደርሰናል። ለዚሁም ማስረጃ ዮሴፍን ልጥቀስ። ዮሴፍ ከነበረበት ቦታ ተነስቶ የግብጽ ጠቅላይ ሚንስቴር ለመሆን በጊዜው የነበረውን የትምህርት ሂደት አጠናቆ የግብጽን ዜግነት አግኝቶ አስፈላጊውን መስፈርት አሟልቶ መሆን ይቻል ቢላል ሳይጋነን 100 ዓመት ይፈጅበት ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር ነገሮችን አያይዞ ለበጎ አርጓቸው ዮሴፍን በ 13 ዓመት ውስጥ የግብጽ ሁለተኛ ሰው አድረገው። ዛሬስ አንቺ አንተ ያላችሁበት ሁኔታና እግዚአብሔር የተናገራችሁ ምንም አልገናኝ ብሎ ግር ብሏችኋል? ከሆነ ታግሳችሁ እርሱን ጠብቁት ባልሰባችሁትና ባልጠበቃችሁት መንገድ ቃል የገባላችሁን ያደርገዋል።

ለእናንተ ያለኝን ዕቅድ እኔ ዐውቃለሁ” ይላልእግዚአብሔር፤ “ዕቅዱም ፍጻሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጥ፣ እናንተንም የሚጠቅም እንጂ የሚጐዳ አይደለም። ትንቢተ ኤርምያስ 29:11

እግዚአብሔርን መጠበቅ እንችል ዘንድ እርሱ ይርዳን።

No comments:

Post a Comment