Monday, May 23, 2016

መታዘዝ ወይስ ብቃት?

"... እነሆ! መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ ማዳመጥም ከአውራ በግ ሥብ ይበልጣል።..." 1 ሳሙኤል 15:22

እንሰውኛ በብቃት የሚደሰት አምላክ ቢኖረን ኖሮ ምን ይውጠን ነበር እያልኩ በማስብበት ጊዜ ሁሌም የማስበው ይህንን ቃል ነው። በብቃት የሚረካው የኛ ማንነት ሁሌም መታተርና የተሻለ ሆኖ መገኘት ያረካዋል። ብቃት ብቻውን የሚቀረው የምንወዳደረው ውይም የሚያየን ሰው የሌለ ጊዜ ነው። ማንም የሚያየን የለም ያልን ቀን ስለብቃታችን መጨነቅ ከጀመርን አንድ እውነት ገብቶናል ማለት ነው። መታዘዝ የሚባለው እውነት። መታዘዝ ውስጥ ብቃት አለ። የመጀመርያ የእርካታ ማግኛው እግዚአብሔርን መታዘዝ የሆነ ሰው ብቃት አያስጨንቀውም። ብቃትን መታዘዝ ካልቀደመው ትርፉ መጽሐፉን እንዳጠበችው ተረት ላይ እንደምናውቃ ሴትዮ መሆን ነው። መታዘዝ በህይወት መኪናችን ውስጥ እግዚአብሔርን የሾፌር ወንበር ላይ እሺ ብለን አስቀምጠን ተሳፋሪ ሆነን መጓዝን ይጠይቃል። በብቃት ብቻ መተማመን ን አይ የኔን መኪናማ መሾፈር አያቅተኝም ብለን በመሾፈር ብቃታችን ብቻ ተማምነን የማናውቀው ሃገር ውስጥ ያለ መሪ የፈለኩበት ቦታ እሄዳለሁ እንደ ማለት ነው። ብቃት ከመማርና ከልምድ የምናገኘው ሲሆን ለመማርና ልምድ ለመቅሰም ግን መታዘዝ መሰረት ነው። መጠንቀቅ ያለብን ትንሽ ስናውቅ መታዘዝን እንዳንጥላት እና በምናውቃት ብቻ ስንገላበጥ እንዳንኖር ነው። ዐመፅ እና እልኽኝነት የትንሽ እውቀት መገላጫዎች ናቸው። እግዚአብሔር በልምድ የሚገለገል አምላክ ሳይሆን ሁሌም እንደአዲስ እየታዘዝነው የሚመለክ ጌታ ነው። በልማድ ስንመላልስ የሚከተሉት ባህሪያት ይታዩብናል፤ ቃሉ በእኛ ላይ ያለው ተፀዕኖ ይቀንሳል፣ ላልዳኑ ሰዎች ማዘን እናቆማለን፣ ሲመችን ብቻ ቤተክርስቲያን ሂያጆች እንሆናለን፣ ነፍሳት ሲድኑ እንደ ቀድሞው በደስታ መሞላት እናቆማለን፣ ችግር ሲመጣ ብቻ ፀላዮችና የትርፍ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች እንሆናለን እና የመሳሰሉት ነገሮች። መታዘዝ ግን የህይወታችን መመሪያ ሲሆን ተቃራኒው በህይወታችን ይሆናል። መታዘዝ ውስጥ ብቃት አለና። መታዘዛችንም ለክርስቶስ ያለንን ፍቅር ያሳያል።

ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ ደስ የሚለውን ያህል፣ እግዚአብሔር፣ በሚቃጠል ቍርባንና መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ! መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ ማዳመጥም ከአውራ በግ ሥብ ይበልጣል። ዐመፅ እንደ ጥንቈላ ያለ ኀጢአት፣ እልኸኝነትም እንደ ጣዖት አምልኮ ያለ ክፉ ነገር ነው። አንተ የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ናቅህ፣ እርሱም ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል።” 1 ሳሙኤል 15:22-23

እግዚአብሔር እርሱን መታዘዝ እንድንችል ይርዳን።

No comments:

Post a Comment