Thursday, May 19, 2016

እንደ ንስር

እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን፣ ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም።  ትንቢተ ኢሳያስ 40:31

መጠበቅ በክርስትና ጉዟችን ውስጥ ከባድ ከሆኑ ነገሮች ውስጥ አንዱ ነው። በሰውኛ ሲታይ መጠበቅ አሰልቺና ተስፋ አስቆራጭ መስላል በእግዚአብሔር በኩል ሲታይ ደግሞ የሚያጓጓ ውጤቱ ምን ይሆን እያስባለ የሚያሳስብ የመሰራትና ሥር የመስደጃ ጊዜ ነው። ክርሲቲን ኬይን የምትባል ሰባኪ ምን አለች 'አንዳንዴ በጨለማ ውስጥ ወይም በመጠበቅ ውስጥ ስንሆን የተቀበርን ይመስለናል፣ ነገር ግን በዛ ወቅት በእርግጥ እየተተከልን ስር እየሰደድን ነው' መጠበቅ በሚከብድበት ጊዜ እንድንበረታታ የሚያግዙንን አንዳንድ ነጥቦች ላንሳ። የመጀመርያው እግዚአብሔርን ተስፈ ማድረግ ነው። ሁለተኛው እስካሁን የተደረጉልንን በረከቶች መቁጠር ነው። የመጠበቂያው ጊዜ የመሰርያ፣ የመጎልመሻ፣ ስር የመስደጃ እና ከሁሉ በላይ እምነታችን የሚመዘንበት ጊዜ መሆኑን ደጋግመን ማሰታውስ ነው። በመጠበቅ ውስጥ ያበቀልነው ስር ወደፊት ከሚመጣው ዝናብ፣ ጎርፍ፣ ነፋስ እንዲሁም ከተለያዩ ተግዳሮቶች ፀንተን እንድንቆም ይረዳናል። እኛ ዛሬን ወይም ነገን እያየን ምን አለ ከዚህ ጥበቃ ቶሎ ብገላገል ስንል እግሂአብሔር ደግሞ የዛሬን እና የነገን ብቻ ሳይሆን የወደፊቱን በኛ ሊሰራ ያለውን ስራ እያየ ቆይ ትንሽ እያለ ይሰራናል። መጠበቅ ቢቆረቁርም ቆራጥ ያደርጋል፣ ቢታክትም የማይታክት ማንነት ሰጥቶን ያልፋል፣ ቢያደክምም በቀላሉ የማይረታ ስብእናን ሰቶን ያልፋል።  ንስር ከወፍ ዝርያዎች ውስጥ በጣም ከፍ ብሎ ወደ ላይ መውጣት የሚችል የወፍ ዝርያ ነው። 10 እስከ 15 ጫማ ከፍታ መብረር ሲችል በሰዓት እስከ 65 ሜትር ወደላይ የመብረር አቅም አለው። ወደላይም ከወጣ በኋላ ያለማቋረጥ ለሰዓታት መብረር ይችላል። በመጠበቅ ውስጥ እንደ ንስር መሆን አለ፤ ወደ ከፍታ መውጣት፣ መሮጥ፣ መሄድ፣ አለመታከትና አለመድከም።


ያዕቆብ ሆይ፤ ለምን እንዲህ ትላለህ? እስራኤል ሆይ፤ ለምን እንዲህ ትናገራለህ? “መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች፤ ፍርዴም በአምላኬ ቸል ተብላለችለምን ትላለህ? አታውቅምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፣ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው። አይደክምም፤ አይታክትም፤ ማስተዋሉም በማንም አይመረመርም። ለደከመው ብርታት ይሰጣል፤ ለዛለው ጒልበት ይጨምራል። ወጣቶች እንኳ ይደክማሉ፤ ይታክታሉም፤ ጐበዛዝትም ተሰናክለው ይወድቃሉ። እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን፣ ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም። ትንቢተ ኢሳያስ 40:27-34


እግዚአብሔር እርሱን ተስፋ የምናደርግ እንድንሆን ይርዳን።

No comments:

Post a Comment