በሰዎች ሁሉ ላይ ከደረሰው የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም፤ እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም፤ ነገር ግን በምትፈተኑበት ጊዜ ፈተናውን መታገሥ እንድትችሉ፣ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል። 1 ቆሮንቶስ 10:13
'ፈተና እኮ ለምን?' ብለን ጠይቀን ነበር አሁን ደግሞ 'ፈተና እስከመቼ?' የሚለውን ደግሞ እንዳሰው። እንግዲህ ወርቅ የሚፈተነው እስከ መጨረሻው ማለተም 99.9% ንፁህ እስኪሆን ነው። ለመጀመርያ ጊዜ ተጣርቶ ንፁህ ወርቅ ሲሆን 80%ብቻ ነው እንዳልን 99.9% እስኪደርስ መጣራቱ አይቀርምና ይጣራል ይጣራል እንዲሁም ይጣራል። የኛም ነገር እንደዛው ነው፤ ፍፁም እስክንሆን መጣራት የግድ ነውና ፈተናው እስከመቼ የሚለውን ይመልስልናል። አዎ ፈተናው ሳያልቅ መሰብሰባችን ይቀድምና ሁሌም ፈተና ውስጥ ሆነን እናልፋለን። ነገር ግን እያንዳንዱ ፈተና እያሳደገን እያጠራን ስለምንሄድ 'ፈተና እኮ ለምን?' የሚለውን ጥያቄ መጠየቃችንን እንተውና 'ከዚህ ፈተና ምን አገኛለሁ፣ ከዛስ ከኔ አልፌ ለሚቀጥለው ተተኪ ምን አስቀምጣለሁ ብለን ማሰብ እንጀምራለን'። ብዙ ፈተና ያለፈው ወርቅ የመጨረሻ ጠርቶ ካበቃ በኋላ ለዘላለም አይኖርም ይጠፋል ያረጃል በሌላ ጌጥ ይተካል። በእኛ ሕይወት ውስጥ ግን ፈተና ሲመጣ ለማያልፈው ዘላለማዊ ማንነታችንም ጭምር የሚሆን ብቃትን ሰጥቶን ያልፋል። ለዚህ ነው ጴጥሮስ
‘በእሳት ተፈትኖ ቢጠራም፣ ጠፊ ከሆነው ወርቅ ይልቅ እጅግ የከበረው
እምነታችሁ’ ያለው። ፈተና ከገባንና የእግዚአብሔርን ነገር ከፈለግን ካንዱ ፈተና ወደሚቀጥለው ስናልፍ ይበልጥ እርሱ የሚፈልገንን አይነት ሰው እየሆንን እናድጋለን። ይህ ከገባን ደግሞ ለጠላት ስራ እንሆንበታለን እንጅ በሰበቡ እየገባ የሚያንሾካሹከው ውሸት አያስፈራንም።
በዚህ ብቻ ሳይሆን በመከራችንም ሐሤት እናደርጋለን፤ ምክንያቱም መከራ ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን። ትዕግሥት ጽናትን፣ ጽናት የተፈተነ ባሕርይን፣ የተፈተነ ባሕርይ ተስፋን፤ ይህም ተስፋ ለዕፍረት አይዳርገንም፤ እግዚአብሔር በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ ፍቅሩን በልባችን አፍስሶአልና። ወደ ሮሜ ሰዎች 5:3-6
እግዚአብሔር በፈተና ውስጥ ስናልፍ ልንሰራ እንደሆነ እንዲገባን ይርዳን።
No comments:
Post a Comment