Wednesday, May 18, 2016

ያልከው ላይቀየር

እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት5:7

ሰው ሁሉን ማድረግ እንደማይችል እያወቀ ስለሁሉም የሚጨነቅ ፍጥረት ነው። ሰው ከጭንቀቱ የሚያ  ፈው ሁሉን ቻዩን እግዚአብሔርን መታመኛው ያደረገ ቀን ነው። ልክ ኢዮብ እንዳለው እግዚአብሔር ያለው ብቻ እንደሚሆን ሲገባን ማረፍ እንጀምራለን። ‘ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደ ሆንህ፥ አሳብህም ይከለከል ዘንድ ከቶ እንደማይቻል አወቅሁ።’ መጽሐፈ ኢዮብ 41:2

አንተ ያልከው ላይቀየር
የወሰንከው ላይሻር
የከፈትከው ላይዘጋ
ታድያ ለምን እኔ ልስጋ?
ሃሳብ ጭንቄን ባንተ ጥዬ
ልኑር እንጂ ተማምኜ።
አንዴ ቆርጠህ ወደኽኛል
በልጅህ ደም ወልደኽኛል፣
ልጅ ሆኛለሁ አንዴ በቃ
ለዛውም የንጉሱ የሁሉ አለቃ።
ስለዚህ ንጉሥ ሆይ
አንተ ያልከው ላይቀየር
የወሰንከው ላይሻር
የከፈትከው ላይዘጋ
ታድያ ለምን እኔ ልስጋ?
አውቄ አባቴ ሁሉን እንዲያዘጋጅ
ልኑር እንጂ ተዘልዬ ልክ እንደ ልጅ።

ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፥ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? ስለ ልብስስ ስለ ምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም። እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? እንግዲህ። ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል። የማቴዎስ ወንጌል 6:25-34


ጭንቀታችንን ሁሉ በእርሱ ላይ ጥለን የእርሱን ጽድቅ እንድንፈልግ እግዚአብሔር ይርዳን።

No comments:

Post a Comment