Thursday, May 26, 2016

ከወርቅ የሚበልጥ

'እነዚህ ነገሮች በእናንተ ላይ የደረሱት፣ በእሳት ተፈትኖ ቢጠራም፣ ጠፊ ከሆነው ወርቅ ይልቅ እጅግ የከበረው እምነታችሁ እውነተኛ መሆኑ እንደተረጋገጠና ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን ክብርንና፣ ውዳሴን እንዲያስገኝላችሁ ነው።' 1 ጴጥሮስ 1:7

ወርቅ እጅግ ውድ ከሆኑት የተፈጥሮ ድንጋዮች ውስጥ አንዱ ነው። የወርቅ ውድነት አንድም እንደልብ የማይገኝ ከመሆኑ የተነሳ ነው ሌላው ደሞ ከተገኘ በኋላ የሚደረግለት የማንጠር ወይም የማጥራት ስራ ውድ ስለሆነ ነው። ወርቅ አንድ ቦታ ላይ መኖሩን ለማረጋገጥ ብዙ ድካም ይጠይቃል፣ ከተገኘና ከወጣ በኋላ ደግሞ ያለው የስራ ሂደት እጅግ አታካችና እልህ አስጨራሽ ነው። ዛሬ ልጽፍም የፈለኩት ስለ ማጥራት ሂደቱ ነው። የማጥራቱ ሰራ ምን ያህል አድካሚ እንደሆነ ለመንገንዘብ ያህል አንዲት ብቻ ማስረጃ ልስጥ፣ በምድር ከርስ ውስጥ በአንድ ቶን አፈር ውስጥ በግምት 0.004 ግራም ወርቅ ብቻ ነው የሚገኘው። አንድ ቶንን ወደ ግራም ስንቀይረው 907,185 ግራም ወይም እንዲቀለን ወደ ኪሎግራም ብንቀይረው በግምት 907 ኪሎግራም ማለት ነው። ይህ ማለት እንግዲህ ከግማሽ ግራም ወርቅ እጅግ ያነሰ ወርቅ ለማግኘት በትንሹ 900 ኪሎ አቧራ ማራገፍ ይጠበቅብናል  እሱንም እንዳው እጅግ በጣም አቃለነው ማለት ነው። አቧራ ስንል ደግሞ አፈር ብቻ እንዳልሆነ ልብ ማለት ይገባል። ሌሎች ድንጋዮች፣ ፈሳሽ፣ ብረት፣ ቆሻሻ እና የመሳሰሉትን ሌሎች ነገሮች ያካትታል። 900 ኪሎውም ከተራገፈለት በኋላ ወርቁ ራሱ ደሞ ደረጃውን ለማውቅ የተለያዩ የማጣራት እና የምደባ ሂደቶችን ያልፋል፣ ለዛም ነው ወርቅ በተላያዩ ካራቶች ተፈርጆ የሚሸጠው። መቼም ሃሳቤ ወርቅ ላይ ብቻ እንደማያልቅ የታወቀ ነው። እርሱም  ከወርቅ ስለሚበልጠው ከመሬት ሳይሆን ከሰው ልብ ተፈትኖ ሰለሚወጣው እምነት ሰለሚባለው ነገር ነው።  መቼም እውነተኛ ክርስትና እንዳው በዘበት እንደማይመጣ የታወቀ ነው። ነገር ግን ክርስቲያን ከፈተናው የሚያተርፈው ብዙ ነገር ሰላለ መፈተኑ ይጠቅመዋል እንጂ አይጎዳውም። ልክ የወርቅን የማጥራት ሂደት እንዳየነው እግዚአብሔር እኛን ከተቀበርንበት የሞት ኑሮ በልጁ ደም ቆፍሮ ካወጣን በኋላ እንደወርቅ ከዛም አልፎ ውድ የሆነውን እምነታችንን ሊያጠራው ሲል በተለያዩ መንገዶች ያሳልፈናል። ምን አልባትም ይህን እያነበብን እያለ ትልቁ ጥያቄ በልባችን የሚመላለሰው 'ለምን? ለምን ጌታ ሆይ ፈተናዬን አበዛኸው?' እያልን ይሆናል። ወርቅ በዋዛ እንደማይጠራ ሁሉ፣ ከእርሱ የሚበልጠውማ እምነት ይበልጥ እንዴት በእሳት አይፈተን? ዳዊትም እንዲህ ብሏል፤

'አምላክ ሆይ፤ አንተ ፈተንኸን፤ እንደ ብርም አነጠርኸን። ወደ ወጥመድ አገባኸን፤ በጀርባችንም ሸክም ጫንህብን። ሰዎች በራሳችን ላይ እንዲፈነጩ አደረግህ፤ በእሳትና በውሃ መካከል አለፍን፤ የኋላ ኋላ ግን ወደ በረከት አመጣኸን።' መዝሙረ ዳዊት 66:10-12

እግዚአብሔር በፈተና ውስጥ ስናልፍ እርሱን ብቻ የምናይበትን የጨከነ ልብ ይስጠን።


‘ፈተናው እኮ ለምን?’ የሚለውን ጥያቄ በሚቀጥሉት ጦማሮች ለመዳሰስ አስቤያሁ።

No comments:

Post a Comment