Sunday, April 1, 2018

እውነተኛ ክርስትና ምንድን ነው?

በማግሥቱ ከቢታንያ ሲወጡ ኢየሱስ ተራበ። እርሱም ቅጠል ያላት የበለስ ዛፍ ከሩቅ አየ፤ ምናልባት ፍሬ ይገኝባት እንደሆነ ብሎ ወደ እርሷ መጣ፤ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። ከዚያም ዛፏን፣ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ፍሬ ከአንቺ አይብላ” አላት። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲናገር ሰሙ። ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፣ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያስወጣ ጀመር። የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ ገለባበጠ፤ ማንም ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳያልፍ ከለከለ። ሲያስተምራቸውም፣ “ ‘ቤቴ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት!” አላቸው። የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም፣ ይህን ሲሰሙ እንዴት እንደሚያጠፉት መንገድ ይፈልጉ ጀመር፤ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ በመገረማቸው ፈርተውታልና። በመሸም ጊዜ ከከተማዪቱ ወጥተው ሄዱ። የማርቆስ ወንጌል 11 ፥ 12 — 19

በዚህ ክፍል ውስጥ ኢየሱስ ሁለት ነገሮችን ሲያደርግ እንመለከታለን 1 ፍሬ ያላፈራችውን የበለስ ዛፍ ሲረግማትና 2 ለሁለተኛ ጊዜ ቤተ መቅደስ ውስጥ ገብቶ ነጋዴዎችን ሲያስወጣ እንመለከታለን። ሁለቱንም ድርጊቶች የፈጸመው የህማማት ሳምንት ተብሎ በሚገለፀው ሳምንት ውስጥ ነው። ሁለቱም ድርጊቶች አንድ አይነት ሃሳብ አላቸው ብዬ አምናለሁ። እስኪ ሁለቱንም በተራ እንመልከታቸው።

1 ፍሬ ያላፈራችውን የበለስ ዛፍ፦ የበለስ ዛፍ በተፈጥሮው ሰፋፊ ቅጠሎች ያሉት፣ ስሩ በጣም ጥልቅና ውሃን ከሩቅ ቦታ ስቦ ማምጣት የሚችል ሲሆን፣ ፍሬውና ቅጠሉ እኩል ነው የሚወጡት። በብሉይ ኪዳንም የበለስ ዛፍ የእስራኤል ብሔራዊ ምልከት ነበር። ክርስቶስ ፍሬ አገኛለሁ ብሎ ወደ ዛፏ የተጠጋው ቅጠሎቿን ከሩቅ አይቶ ነበር። ነገር ግን ፍሬ አጥቶባት ዳግመኛ እንዳታፈራ ሲረግማት እናያለን። በማግስቱ ጠዋትም ደቀ መዛሙርቱ ደርቃ አይተዋት ተገርመው ሲጠይቁት ስለ እምነት ሲያስተምራቸው በሚቀጥለው ክፍል ላይ እናያለን። እዚህ ክፍል ላይ የምንታዘበው የበለስ ዛፍዋን አስመሳይነት ነው። ፍሬ እንዳለው የበለስ ዛፈ በቅጠሎች ብቻ የታጀበች ነገር ግን ምንም ፍሬ የሌላት። ከዚህም ጋር ሌላ ተያይዞ የምናየው ጠቅላላ እስራኤል እንደ መንግስት ፍሬ አልባ ከሃይማኖተኝነት በቀር መንፈሳዊ መካን እንደሆነች በምሳሌአዊ ዘይቤ የሚያስረዳ ድርጊት ኢየሱስ እንደተናገረ የሚገልጽም አሉ።

2 የክርስቶስ ቤተ መቅደሱ ማንፃት፦ ቤተ መቅደሱ የፋሲካ በዓል በመድረሱ ብዙ ሰዎች የመንፃት ስርዓትን ለመፋጸም የሚመጡትን ሰዎች በማሰብ በቤተ መቅደሱ አካባቢና ውስጥ ይሸጡና ገንዘብ ይለውጡ ነበር። እነዚህ ነጋዴዎች የህዝቡን ልብ ያወቁና ጊዜውንም ተጠቅመው ብዙ ትርፍ ለግላቸው ሰብስበው ለመሄድ የመጡ እንጂ፣ ለህዝቡ ወይም ለእግዚአብሔር ቤት አስበው የመጡ እንዳልነበሩ በግልጽ ይታያል። ቤተ መቅደሱንም ካፀዳ በኋላ ኢየሱስ ቤተ መቅደሱን ለትክክለኛ ተግባር ሲያውለው እናያለን፣ ይኽውም ለማስተማርና እውነተኛ ፈውስ የሚፈልጉን በነፃ መፈወስ ነበር። ማቴዎስ 21 ፥ 12 — 15 ይመልከቱ።
እነዚህ ሁለት የኢየሱስ ድርጊቶች አስመሳይ የሆነ ወይም እውነታኛ ያልሆነን ክርስትና ከሩቅ በሚታዪ አማላይና ሃይማኖታዊ ነገሮች የታጀበ ነገር ግን ሲጠጉት ፍሬ ቢስ የሆነና፣ ሁኔታንና አመቺ ጊዜን ተጠቅሞ ግላዊ ጥቅምን ብቻ የሚሳድዱትን እየተቃወመ እንደሆነ ያሳዪናል። እንግዲህ ይህን ነገር ወደ ራሳችን፣ ወደ ቤተክርስትያናችን፣ ወደ ሃገራችንና ብሎም ወደ ዘመናችን ስናመጣው እንዲህ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ፍሬ ያለው እውነተኛ ክርስትያን ነኝን? ሁኔታንና አመቺ ጊዜን ተጠቅሜ ግላዊ ጥቅሜን ብቻ የሚሳድድ ነኝን?እውነትኛ ፍሬ ያለው ክርስቲያን አስመሳይና ሁኔታንና አመቺ ጊዜን ተጠቅሞ ግላዊ ጥቅምን ብቻ የሚሳድድ ሊሆን በፍፁም  አይችልም። እውነትኛ የመንፈስ ፍሬዎች በገላትያ መጽሃፍ ምዕራፍ 5፡22 — 26 ላይ ተጠቅሷል። የሥጋ ፍሬዎችም እነደዚሁ በገላትያ መጽሃፍ ምዕራፍ 5፡19 — 21 ላይ ተጠቅሷል። ታድያ እነዚህን እውነትኛ የመንፈስ ፍሬዎች ለማፍራት ምን ማድረግም እንዳለብን በዪሐንስ 15 ላይ በግልጽ ተጽፏል። የዪሐንስ 15 ዋና መልዕት እውነትኛ የመንፈስ ፍሬዎች ለማፍራት ከግንዱ መጣበቅ እንዳለብን ይተነትናል፣ ይህም ግንድ እራሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ተገልጿል። ከግንዱ መጣበቅስ ምን ማለት ነው? እንዴት ነውስ የምንጣበቀው?በዪሐንስ 15 ቁጥር 17 ላይ በግልጽ ተጽፏል፣ እንዲህም ይላል “እርስ በእርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትዕዛዜ ይህቺ ናት”። ስለዚህም በግንዱ ላይ መጣበቅ ማለት በፍቅር መኖር ማለት ነው፣ በዪሐንስ 15 ቁጥር 9 ላይ “አብ እንደ ወደደኝ ሁሉ እኔም ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ” ተብሎ ተጽፏል። ስለዚህ እውነትኛ የመንፈስ ፍሬዎችን ለማፍራት ፍቅር ቁልፉ ነው ማለት ነው። ለዚህም ነው ክርስቶስ እንዚህን ሁለት ነገሮች ባደረገበት ሳምንት በመስቀል ላይ የፍቅርን ጥግ ያሳየን። በዪሐንስ 15 ቁጥር 13 ላይ “ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።” ይላል። ዳዊትም በመዝሙር 63፡3 “ፍቅርህ ክህይወት ይበልጣልና ከንፈሮቼ ያመሰግኑሃል።” ይላል።

ክርስቶስም በማርቆስ 12፡28 – 34 ላይ ስለ ታላቁ ትዕዛዝ ይናገራል። “ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ከሁሉ የሚበልጠው ይህ ነው፤ እስራኤል ሆይ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤ አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ።’ ሁለተኛውም ይህ ነው፤ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።“ ከእነዚህም የሚበልጥ ትእዛዝ የለም።” በማቴዎስ 22፡40 ላይም “ሕግና ነብያት በሙሉ በነዚህ ሁለት ትዕዛዛት ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው።” ብሎ ኢየሱስ ይናገራል። ይህን ሲል ምን ማለቱ ነው፤ እግዚአብሔር አምላክህን ከወደድክ እንዲሁም ጐረቤትህን እንደራስህ ከወደድክ የቀሩትን ትዕዛዛት መፈጸም እጅግ በጣም ቀላል ነው ማለቱ ነው። ስለዚህ እውነተኛ ክርስትና ፍቅር ነው ብለን በአንድ ቃል መግለጥ እንችላለን። ጳውሎስ ስለ እውነትኛ የመንፈስ ፍሬዎች በገላትያ መጽሃፍ ምዕራፍ 5፡22 — 26 ላይ ሲተነትንም “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደነዚህ ያሉትንም የሚከለክል ሕግ የለም። የክርስቶስ ኢየሱስ የሆኑት ሥጋን ከክፉ ምኞቱና መሻቱ ጋር ሰቅለውታል። በመንፈስ የምንኖር ከሆን፣ በመንፈስ እንመላለስ። እርስ በርሳችን እየተጎነታተልንና እየተቀናናን በከንቱ ውዳሴ አንመካ።” ይላል። ለዚህ ይሆናል ፍቅርን በአንደኝነት የጠቀሰው። ከዛም በበለጠ ጳውሎስ 1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 13 ላይ በጣም የተብራራ መልዕክት ስለ ፍቅር ጽፏል። 1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 13ትን በተለይ ከቁጥር 4 ጀምሮ ስታንቡት ፍቅር እውነትኛ የመንፈስ ፍሬዎች አጭቆ የያዘ የሁሉም ፍሬዎች መፈልፈያ እንደሆነ ልብ ማለት አያዳግትም። “ፍቅር ታጋሽ ነው፤ ደግሞም ቸር ነው። ፍቅር አይመቀኝም፤ አይመካም፤ አይታበይም፤ ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፤ ራስ ወዳድ አይደለም፤ አይበሳጭም፣ በደልን አይቈጥርም። ፍቅር ከእውነት ጋር እንጂ በዐመፅ ደስ አይሰኝም። ፍቅር ሁል ጊዜ ይታገሣል፤ ሁል ጊዜ ያምናል፤ ሁል ጊዜ ተስፋ ያደርጋል፤ ሁል ጊዜ ጸንቶ ይቆማል።

ፍቅር ከቶ አይወድቅም፤ ነገር ግን ትንቢት ቢሆን ይሻራል፤ ልሳንም ቢሆን ይቀራል፤ ዕውቀትም ቢሆን ይሻራል። ምክንያቱም የምናውቀው በከፊል ነው፤ ትንቢት የምንናገረውም በከፊል ነው። ነገር ግን ፍጹም የሆነው ሲመጣ በከፊል የነበረው ይሻራል።”
ስጠቀልለው እውነተኛ ክርስትና ማለት በፍቅር መመላለስ ማለት ነው። ወይም ደግሞ እውነተኛ ክርስትና በአንድ ቃል ግለጹት ከተባልን “ፍቅር” ብለን መግለጸ እንችላለን። ደግሞም ኢየሱስ ይህን ፍቅር በተግባር አሳይቶናል። በፍቅር በመኖር፣ እርስ በርሳችን በመዋደድ፣ አልፎም ጠላቶቻችንን በመውደድ ፍሬ ያለው እውነተኛ ክርስትናን እንኑር፣ አስመሳይ፣ ሁኔታንና አመቺ ጊዜን ተጠቅመን ግላዊ ጥቅምን ብቻ የሚሳድዱ ክርስቲያኖች ከመሆንም ከእንደዛ አይነቶቹም እንጠበቅ።

”ጸሓፊውም እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ መልካም ብለሃል፤ እርሱ አንድ መሆኑን፣ ከእርሱም ሌላ አለመኖሩን መናገርህ ትክክል ነው፤ እርሱን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም አእምሮህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ መውደድ፣ እንዲሁም ባልንጀራህን እንደ ራስህ መውደድ ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች ይበልጣል።”“ ማርቆስ 12፡ 32 — 33

Thursday, March 29, 2018

ይድረስ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትራችን


 . . . ሥልጣን ከሰማያት እንደ ሆነ ካወቅህ . . . ትንቢት ዳንኤል 4፡26

ዳንኤል የንጉስ አማካሪ የነበረ በዘመኑ ከነበሩት አዋቂ ተብዬዎች በጥበብና በማስተዋል አስር እጅ የበለጠ ነበር። ትንቢት ዳንኤል 4 ላይ ለሚያማክረው ንጉስ ናቡከደናጾርም ህልም ሲፈታለት በአጽንዖት የሚነግረው አንድ ጉዳይ ነበር፣ ይህም ስልጣን “ከሰማይ እንደሆን እድዲያውቅ ነው”። ከዛም በመቀጠል “የደህንነትህ ዘመንህ ወይም በንግስና/በስልጣን የመቆየትህ ዘመን ይረዝም ዘንድ ኃጢአትህን በጽድቅ ፥ በደልህንም ለድሆች በመመጽወት አስቀር” ይለዋል።

በእኔ የግል አስተያየት በኢትዮጵይ ውስጥ የሰለጠነ የመንግስት አስዳደር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ የዳንኤልን ምክር የሰማም ሆን ያነበበ የአገር መሪ ኢትዮጵያ ነበራት ብዬ አላስብም። ሃይማኖትን ከስልጣን ጋር ቀላቅለው ያስተዳደሯት አፄዎችም ስዩመ እግዚአብሄር ብለው ተጠያቂነትን ከራሳቸው ለማውረድ እናም እድሜ ልክ ለመንገስ ተጠቀሙበት እንጂ ፣ በትክክል ትርጉሙ ገብቷቸው አልኖሩበትም። በዚህም ምክንያት አሁን ያለችውን ኢትዮጵያን አስረክበውናል። እግዚአብሄርን ፈርተው ፣ ሥልጣን ከሰማያት እንደ ሆነ አውቀው ቢመሩን ኖሮ ምንኛ በታደልን ነበር።

ብዙ ሰዎች ኢትዮጵያ ፈርጀ ብዙ ችግሮች ያሉባት ፣ እነዚህንም ችግሮች ለመፍታት አዳጋች እንደሆነ ፥ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖምያዊ እና ማህበራዊ ትንታኔዎችን በመስጠት ጭብጥ ያላቸው መረጃዎችን በማቅረብ ትንተናዎችን ሲያቀርቡ ይደመጣል። በእርግጥም ኢትዮጵያ ፈርጀ ብዙ ችግሮች ያሉባት ሃገር ለመሆንዋ የምንከራከርበት ጉዳይ አይደለም። ነገር ግን እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የምንጠቀመው ዘዴ ነው እንጂ ችግሮችን ለመፍታት አዳጋች የሚያደርገው ፣ በእኔ እይታ ለእነዚህ ፈርጀ ብዙ ችግሮች መፍትሔ ማምጣት ከባድ ነው ብዬ አላምንም።

 ዋናው የእኔ መልዕክት ለአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትራችን በስልጣን የመቆየትዎ ዘመን የተሳካና የረዘመ ይሆን ዘንድ እርስዎም ሆነ ካቢኔዎ ውስጥ የሚመርጧቸው ሰዎች እስከዛሬ የተሰራውን ኃጢአት በጽድቅ፥ እስከዛሬ የተሰራውን በደልንም ለድሆች በመቆርቆርና ፍትህን በማስፈን እንዲቀይሩ፤ በዚህም ውስጥ እግዚአብሄርን ፈርተው ፣ ሥልጣን ከሰማያት እንደ ሆነ አውቀው ቢመሩን ፣ ከባድ የተባለው ችግር በሰው ዓይን እንጂ በእግዚአብሄር ዓይን እጅግ ቀላል እንደሆነና፣ መፍትሔውንም እራሱ የሚፈሩት እግዚአብሄር በእጅዎ ይሰጥዎታ የሚል ነው። የጥበብ መጀመርያ እግዚአብሄርን መፍራት ነው ፤ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው። ምሳሌ 9፥10

ወደ ተጨባጭ ሁኔታዎች ስንመጣ ፣ በእኔ የግል አስተያየት የአገራችንን ችግሮች በሦስት እከፍላቸዋለሁ። 

1 ወጥ የሆነ መዋቅራዊ የሆነ አሰራር ማጣት በእንግሊዝኛው system የምንለው በተቀናጀ መልኩ አለመኖሩ፣ 
2 የትምህርት መዋቅራችን ወይም curriculum ገና ሀ ተብሎ የሰለጠነ የትምህርት አሰጣጥ ሲመጣ ጀምሮ የተበላሸ መሆኑ እና 
3 አገራችን ኢትዮጵያ በዘመኗ በሙሉ ይሄ ነው የተባለ የባህል አብዮት አለማካሄድዋ ናቸው። 

እነዚህ ሶስቱ በጥቅሉ ተጠያቂነት የጎደለው የመንግስት የስራ አስፈፃሚ እንዲፈጠር ፣ ለአገር ችግር መፍትሔ ሰጪ የፈጠራ ሰው innovative የሆነ የተማረ ሃይል እንዳይኖር እና የህብረተሰቡ የአስተሳሰብ አድማስ እንዳይሰፋ ያደረጉ ችግሮች ናቸው።እንዚህን ችግሮች ለመፍታትም መጠቅም ያሉብን መንገዶች እንደተለመደው ከላይ ወደ ታች ሳይሆን፤ ከታች ወደ ላይ መሆን ይገባዋል። ይህ ምን ማለት ነው፣ በተለምዶ የተማሩና ችግር ለመፍታት አቅም ያላቸውን ሰዎች critical thinkers and problem solvers በሚኒስትር ደረጃ አስቅምጦ መፍትሔ ማፈላለግ እሩቅ የማያስኬድና ፈጣን መፍትሔም ለማምጣት የማይበጅ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለማንሳት ወደድኩ። መዋቅራዊ የሆነ አሰራርንም ቢሆን ከታች ወደ ላይ ማለትም ከቀበሌ ወይም ከወረዳ ወደ አገር አቀፍ ማሳደግ፣ የተማሩና ችግር ለመፍታት አቅም ያላቸውን ሰዎች የቀበሌ እና የወረዳ መሪዎች በማድረግ የተማረውን እና ቀና የሆነውን የሰው ሃይል ለድሆችና ላልተማሩት ዕውቀቱን የሚያውልበትን መንገድ ማመቻቸት ግድ ይለናል። ትምህርት ቤቶችንና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ደግሞ ለውጣዊ progressive የሆነን ትምህርት በሂደት እዲያስተምሩና፣ በዘላቂነት ደግሞ ኢትጵያዊ የሆነ አዲስ የትምህርት መርሓ ግብር curriculum በመንደፍ አሮጌውን መቀየር ወሳኝ ነው። በአጭር ጊዜም መፍትሔያዊ የሆኑ እንቅስሴዎች እንዲዳብሩን የፈጠራ ማዕከሎችን innovation centers በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ እንዲቋቋሙ ማድረግና፣ መንግስት ከግል ተቋማት፣ ከከፍተኛ ትምህርትና አሁን በስራ ላይ ካሉ የምርምር ተቋማት ጋር በመሆን ፈጣን ሃገራዊ ችግር ፈቺ እና ፈር ቀያሽ ምርምሮችንና ጥናቶችን የሚያካሂድ ጠንካራ ተቋምን በአጭር ጊዜ ውስጥ ቢያቋቁም መልካም ነው የሚል ሃሳብ አለኝ።

ከሁሉ በላይ ይቅርታ የተሞላው፣ ያለፈውን ትተን ወደፊታችን ላይ ያሚያተስኩር፣ የግለሰብን መብት የሚያከብር እና ከቡድን አሳቢነት የሚገላግል፤ ፍቅርን ማዕከላዊ ያደረገ ርዕዮተ ዓለም ለምድራችን ያስፈልጋታል። የህግና የትዕዛዛት ሁሉ ማንጠልጠያ የሆኑትን ሁለቱን ትዕዛዛት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እንዝራ በማለት መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።

መልካም የአገልግሎት ዘመን እንዲሆንልሆ እየተመኝሁ እግዚአብሄር ፀጋና ጥበብ እንዲያበዛልዎ ፀሎቴ ነው። ስራው የእርስዎ ብቻ ሳይሆን የሁላችን ስለሆነ ሕዝቡንም በቀናነት መሪያችንን እያገዝን የበኩላችንን ድርሻ እንፈጽም ብዬ አሳስባለሁ።   

ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው፤ ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል፤ ይህም፣ ‘ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለው ነው፤ ሕግና ነቢያት በሙሉ በእነዚህ ሁለት ትእዛዛት ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው።” ማቴዎስ 22፡ 37 — 40

Wednesday, October 11, 2017

የማንቂያ ደወል

ስለዚህ ንቃ፤ ሊሞት የተቃረበውን የቀረውን ነገር አጽና፤ ሥራህ በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትም።እንግዲህ የተቀበልኸውንና የሰማኸውን አስታውስ፤ ታዘዘውም፤ ንስሓም ግባ። ባትነቃ ግን እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ፤ በየትኛው ሰዓት እንደምመጣብህም አታውቅም። ራዕይ 6:2—3

በዚህ ጦማር ላይ ላጋራ የፈለኩት ጉዳይ በሃሰታኞች ነቢያት ዙርያ በኢትዮጲያ ወንጌላውያን አብይተክርስቲያናት ሕብረት (ኢወአክሕ) የተሰጠውን መግለጫና ከዛም ጋር ተያይዞ ስለሚነሱ ሃሳቦች ይሆናል። በመጀመርያ እንደተለመደው አቋሜን ግልጽ በማድረግ ልጀምር።
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ማንንም ቡድን ወይም ግለሰብ ለመንቀፍ ወይም የማንም ትምህርት ላይ ጣት ለመቀሰር አይደለም። እንዲሁም በዚህ ጦማር ላይ የሚወጡ ማንኛውም ጽሑፎች ሃሳብንና አስተሳሰብን የሚሞግቱ ብቻ እንጂ ከግለሰብ፣ ከድርጅት ወይም ከማንኛውም ቡድን ጋር ጠብ የሌላቸው እንዲሁም ያልወገኑ ናቸው።
ሃሳቤን በጥሩ ሁኔታ ለማካፈል ይረዳኝ ዘንድ በፈርጅ እያስቀመጥኩ አብራራለሁ። በመጀመርያ ኢወአክሕ ማን ነው ከሚለው ጀምሬ፣ በሃሰታኞች ነቢያት ዙርያ የተሰጠው መግለጫ ምን ፋይዳ አለው የሚለውን አስከትዬ፣ አሁን ባለው ሁኔታ ውስጥ እንደኔ ያሉ ተራ ዓማኞች ምን ማወቅና ማድረግ አለባቸው የሚለውን እዳስሳለሁ።

1 የኢትዮጲያ ወንጌላውያን አብይተክርስቲያናት ሕብረት (ኢወአክሕ)ማን ነው?
            እንደኔ እምነት ምንም ከማለታችን በፊት ኢወአክሕ ማን ነው ማንንስ ይወክላል ብለን መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል። የኢወአክሕ እንቅስቃሴ የተጀመረው በኛ አቆጣጠር በ60ዎቹ ውስጥ ሲሆን፣ በዛን ጊዜ የነበረው መንግስት ሲከተለው ከነበረው የሶሻሊስት ስርዓት ምክንያት ለረጅም ዘመን በህቡዕ የተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ የመንግስት ለውጥ በ80ዎቹ ላይ ሲመጣ ሰኔ 20 ቀን 1983 ዓ ም ከኢትዮጵያ ፍትህ ሚኒስቴር ሕጋዊ ዕውቅናን አግኝቶ ተመሰረተ። በዚያን ጊዜ ዘጠኝ በሚሆኑ ቤተክረስቲያኖች የተመሰረተ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ 29805 በአገር ውስጥ 15 በውጭ ሃገር ያሉ ቤተክርስቲያኖችን እንዲሁም 29 የሚሆኑ እምነት ተኮር ተቋሞችን በአባልነት የያዘ ሕብረት ነው። በጥቅሉም ወደ 13 ሚሊዮን የሚሆኑ አማኞች በዚህ ህብረት ስር ይታቀፋሉ። ለበለጠ መረጃ የህብረቱን ድህረ ገጽ ይመልከቱ http://www.ecfethiopia.org/ ።
            የኢወአክሕ ውክልና የሕብረቱ አባል ለሆኑት ቤተክርስቲያኖችና በስሮቻቸው ላሉ አባላት ነው። ይህም በመሆኑ የተሰጠው መግለጫ የሚወክለው የነዚህኑ አባላት አቋም መሆኑን መገንዘብ ግድ ይላል። መግለጫውን የሰጡት ግለሰብ የኢወአክሕን ወክለው እንጂ እንዳው እሳቸው ብቻ ብድግ ብለው የሰጡት አይደለም። በዚህ ከተግባባን የተሰጠውን መግለጫ ከአቅራቢው ጋር እያገናኝን እሱስ እንዲህና እንዲያ አድርጎ አልነበር ብለንም መሰረት የለቀቀ አታካራ ውስጥ መግባትን ያልበሰል ክርክርና ጠብ ውስጥ ሊጨምር ስለሚችል ከወዲሁ ልናስወግደው ይገባል ብዬ እመክራለሁ። እንደዚህ ስል የአመራር አባሎች የሆኑትን ሰዎች ብቃት አላቸው/የላቸውም፣ ስህተት ሰርተው አያውቁም እያልኩ እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል። እንዲሁም የኢወአክሕ የአሰራር ችግር የለበትም ወይም እስከዛሬ ድረስ ያለ እንከን ሲሰራ የቆየ ተቋም ነው የሚልም አቋም የለኝም። ይልቁንም አሁን ለተፈጠሩት ችግሮች በዋና ተጠያቂነት ውስጥ ከሚዘረዘሩት ውስጥ አንዱ ነው ብዬም አምናለሁ። ነገር ግን ይህ አሁን የምንነጋገርበትን መግለጫ ማውጣቱን ግን እንደ ስህተት ወይም ፈራጅ እንደመሆን አድርጌ አልቆጥረውም። ይልቁንም በዚህ አጋጣሚ ይህ መግለጫ ምን ፋይዳ አለው ብለን በሰከነ መልኩ ብንወያይ መልካም ነው።

            2 በሃሰታኞች ነቢያት ዙርያ ከኢወአክሕ የተሰጠው መግለጫ ምን ፋይዳ አለው?
            ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተቀጣጠለ ያልውን የነብያት አገልግሎትን ሙሉ ለሙሉ ለመቃወምና ስህተት ነው በማለት መፈረጅ ፍርደ ገምድል ሊያሰኝ ስለሚያስችል፣ ይህን ጉዳይ አጽንኦት ሰጥተን መገምገም ያለብን ሲሆን፣ ለምንስ ይህን ያህል ድብልቅልቅ ስሜት እስኪፈጥር ድረስ ቸል ተባለ የሚለውን መመለስ ተገቢ ነው። የዚህን ዝርዝር መልስ በዚህ ጦማር ላይ መመለስ አላሰብኩም፣ ነገር ግን በሌላ ጊዜ በሰፊው ልመጣበት የምችል ሃሳብ ይሆናል።
            በነብያቶቹ በኩል እየታዘብን ያለነው ተጨባጭ እውነታ የቤተክርስቲያኖቻቸው ባለራዕይም መስራችም መሪም እነርሱው እራሳቸው መሆናቸውን ነው። ይህ ነገር ደግሞ እያደር ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ከልካይና ፈቃጅ በሌለበት፣ እንደ እኔ ያለውን ተራውን ምእመን ያሰኛቸውን ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። በዚህም ምክንያት የሆነ ታዛቢና ኧረ ተዉ የሚል ከልካይ አስፈላጊ መሆኑ የሚያከራክረን ጉዳይ አይሆንም። በዚህ አጋጣሚ የኢወአክሕን የአመራር አባላት ብቃት እና የድሮ ስህተት ወደኋላ እያየን መግለጫውን ችላ ከማለት ይልቅ መግለጫው ምን ፋይዳ አለው ብለን ስንጠይቅ አብረን ወደፊትስ እስክ አሁን ያጠፉትን ነገር በምን አይነት መልኩ ያስተካክሉ የሚለውንም እንድናስብ ይረዳናል። ወደ አሁኑ መግለጫ ስንመጣና ስንመዝነው ማየት ያሉብን ነገሮች 1 መግለጫው የወጣበት ምክንያት ልክ ነው ወይ? 2 የተነሱት ነጥቦችስ የተቀመጡት ከምን አንጻር ተገምግሞ ነው? 3 ለወደፊትስ ከዚህ ልንማር የምንችለው ምንድን ነው?የሚሉትን ይሆናል።
            በእኔ እምነት መግለጫው ምክንያታዊ ነው፣ ተጨባጭ ማስረጃም ይዞ ነው የቀረበው። ዋና ጉዳዮም በቅርቡ “ነብይ” እስራኤል ዳንሳ የተነበየው ትንቢት እንደ ተነበየው አልተፈጸመም ነው። ትንቢቱን በዚህ መስመር ይስሙት https://youtu.be/0d91CAeG_I8። ይህን ደግሞ መከራከርያ አድርገን እንዲህ ነው እንዲያ ነው ብለን ወደ የትም እንዳንሄድ የብዙ ሰዎች ጥያቄና የመወያያ አጀንዳ ሆኖ የሰነበተ ጉዳይ ነው። የተነሱትም ነጥቦች ከመጽሓፍ ቅዱስ አንጻር የተዋቀሩ ሲሆን በማስረጃም የተደገፉ ስለሆኑ የሚያከራክረን አይሆንም። እዚህ ላይ አንድ ቅር ያለኝ እና ማወቅ የምፈልገው ነገር የኢወአክሕን “ነብይ” እስራኤል ዳንሳን በግል አግኝቶ ለማናገር እና በትንቢቱ ላይ የእርሱ አቋም እና መልስ ምን እንደሆነ ለማወቅ ያደረገው ጥረት ምን ያህል መሆኑን ነው። ከዚህ በኋላ መጠበቅ ያለብን የ“ነብይ” እስራኤል ዳንሳን መልስ ይሆናል። ከዚህም ዋና መማር ያለብን ነገር እንደ ሃገር ማሰብ መጀመር እንዳለብን ሲሆን፣ ልቅ የሆነ አሰራር ሁሌም ውዥንብር የሚፈጥር መሆኑን ለማወቅ ይህ የመጀመርያችን እንዳልሆነ ሁሉ፣ ያሁኑ ግን የመንቂያ ደወል ይሁንልን እላለሁ። በጥቅማ ጥቅም ተያይዘንም ይሁን ወይም ከዚህ በፊት “ነብይ” እስራኤል ዳንሳን የሚያክል የለም ስላልን፣ ስህተቱን እንዳላየ ለማለፍና ጣታችንን የኢወአክሕ ላይ እየቀሰርን አድበስብሰን ለማለፍ ብንወስን ዞሮ ዞሮ ተጎጂዎቹ እራሳችን ነን። ከዛም በላይ ልጁን ወደተጨማሪ ስህተት መንዳት ይሆናል። “ነብይ” እስራኤል ዳንሳ ለተናገረው ትንቢት ማብራርያ ወይም ስህተቱን የሚያምንበትንና ንስሃ የሚገባበትን ሁኔታ እንዲፈጠር እግዚአብሔር እንዲረዳው ከቻልን በግል እና በህብረት ጸሎት ብናደርግለትና በሌላ በቻልነው ሁሉ ብንረዳው መልካም ነው። “ነብይ” እስራኤል ዳንሳ ብዙ መልካም ነገር የሰራ ነው፣ የታዩ በምስክር የተረጋገጡ ተዓምራቶች ያደረገ ነውና እንዴት ተሳሳትክ ይባላል የሚል እንደምታ ያለው ክርክርም በሌላ በኩል ቢመጣም፣ ምንም እንኳን ለዙህ ዓይነቱ ሁለት ፈርጅ ያለው ምላሽ ቢኖርም፣ ለጊዜው ነገር ለማብረድ አንደኛውን መልስ ትተን፣ ልክ ነው መልካም ምስክርነቶች አሉት ምስክሮችንም ሰምተናል ብንል እና ብንስማማ እንኳን፣ ያን ስላደረገ አይሳሳትም፣ ወይም ስህተትም ቢያደርግም ችግር የለም ብለን ማለፍ አለብን ብዬ አላምንም። ይልቁንም የኢወአክሕ መግለጫ ፋይዳ ያለው የሚሆነው እዚህ ነው። “ነብይ” እስራኤል ዳንሳ ሰው ነው ሊሳሳት ይችላል፣ ሲሳሳት ደግሞ ስህተቱን አስተካክሎ እንዲመለስ ማበረታታትና በፍቅር ማቅናት የሁሉም ህዝበ ክርስቲያን ግዴታ ነው። የኢወአክሕ መግለጫም ይሄንኑ ያካተተ በመሆኑም የፈራጅነት ወይም የድንጋይ ወርዋሪነት ባህሪ እንደሌለው ያሳያል። ታዲይ ይህ ዓይነትን ትእይንት እየተደጋገመ እኛን ከማሰልቸት አልፎ በማያምኑት ዘንድ መላገጫ ሆነን ወንጌልን ለመስበክ የሚያዳግትበት ደረጃ እንደ ደረሰ እየታዘብን ባለንበት ወቅት እንደኔ ያሉ ተራ ዓማኞች ምን ማወቅና ማድረግ አለባቸው የሚለው ጋ እንምጣ።

            3 እንደኔ ያሉ ተራ ዓማኞች በዚህ ወቅት ምን ማወቅና ማድረግ አለባቸው?
            1 ይህ አጋጣሚ የማንቂያ ደወል እንዲሆንልን እግዚአብሔር ይርዳን። ዘመኑ የመጨረሻው መሆኑን ልብ ብለን ወደ ቃሉ እንመለስ። በግል ከእግዚአብሔር ጋር ጊዜ በመውሰድ ቃሉን ማንበብ ፣ በግላችን በይበልጥ መጸለይ ከምን ጊዜውም በላይ ማብዛት ግድ የሚልበት ሰዓት ላይ መሆኑን ማወቅና መተግበር። የመጣው ነፋስ ሁሉ የሚያንዥዋዥወን በዓለቱ ላይ ስላልተመሰረትን መሆኑን ማወቅ አለብን። እውነተኛውን በደንብ ካላወቅነው አታላዩን መለየት አንችልምና።
            2 ተዓምራት ስላየን እና ትንቢት ስለተነገረን ብቻ የምንከተል ሳንሆን ይልቁንም እንደዚህ ዓይነት ልምምዶችን ከማጽደቃችን በፊት ጊዜ ወስደን መመርመርና፣ ስህተት ስናይ በቀናነት ማቅናትን መለማመድ አለብን። ጌታ ሆይ ያሉትን ሁሉና በስሙ የነገዱትን ሁሉ ከጌታ እንደተላኩልን በሞኝነት መቀበል የምናቆምበት ጊዜው አሁን ነው። ማቴዎስ 7:21 — 23
            3 ተዓምራትና ድንቆችን የምንከተል ሳንሆን የሚከተሉን እንደሆነ መጽሓፍ ቅዱስ ይነግረናል ማርቆስ 16:17—18 ፣ ስለዚህ እኛ አጥብቀን ክርስቶስን መከተል ይገባናል። በጎቼ ድምጼን ያውቃሉ ተብሎ እንደተጻፈ የክርስቶስን ድምጽ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መለማመድ ያለብን ዘመን በመሆኑ ተዓምራትና ድንቅን ስናሳድድ ድንገት ስዓቱ እንዳይደርስብን ማስተዋል የሚያስፈልግን ጊዜ መሆኑን ልብ ማለት አለብን።  
            4 ተሳስታችኋል አርሙ ሲባሉ የባጥ የቆጡን ለሚዘባርቁት በተለይም አሁን አሁን የማምለጫ ንግግር ሆኖ የመጣው እኛን ማን አስተማረንና የኛ ጥፋት አይደለም የሚባልን ሰበብ ሰምተን የምንታለል እንዳንሆን፣ ይልቁንም ለጥፋቱ ሃላፊነት የሚወስድ ትውልድ ለማፍራት እራሳችንን ማዘጋጀት ይጠበቅብናል። ፍሬን እንጂ የፈውስና የያልፍልሃል አይዞህን ፍርፋሪ የሚዘሩትን፣ በግድ አሜን እያስባሉ የነርሱ ተጧሪዎች ሊያደርጉ የሚተጉትን ያለፍርሃት መገሠጽ የምንችልበትን ብቃት ማዳበር አለብን።  
            5 እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች ሲመጡ ሊያስደነግጡ ቢችሉም በማስተዋልና በቀናነት ካየናቸው ከተሳሳትንበት ጎዳና ሊመልሱን፣ የጣልነውን የመደማመጥና የመከባበር ባህላችንን መልሰን ልናመጣበት የሚያስችል አጋጣሚ ሊፈጥሩልን እንደሚችሉ አስበን እንደ መልካም አጋጣሚ ልንጠቀምባቸው ይገባል።
            6 ያጠፉትን በፍቅር መክረን መልሰን ገንዘቦቻችን ማድረግን ባህላችን የምናረግበት አጋጣሚ መሆኑንም ልብ ልንል ያስፈልጋል። ከምንም አይነት ፍላጎት ተነስተው ይስሩት፣ በቸልታ ይሁን ወይ ጥቅማ ጥቅም ዓይናቸውን አሳውሮት፣ ዋናው ጉዳይ ከልባቸው ተጸጽተው ንስሃ ከገቡ መልሰን ገንዘቦቻችን አርገን መቀበል አለብን።
7 አሁንም ደግሜ ደጋግሜ የምናገረው ከሁሉ በላይ ፍጥረት ሁሉ በናፍቆት የሚጠብቀው ከተዓምራቶቻችንና ከዲስኩሮቻችን የበለጠ በየትኛውም ጊዜ ሳንዛነፍ በፍቅር የምንገለጥበትን ጊዜ እንደሆነ ልብ ማለት አለብን ብዬ አሳሰባለሁ። ሮሜ 8:19
ስለዚህ ንቃ፤ ሊሞት የተቃረበውን የቀረውን ነገር አጽና፤ ሥራህ በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትም።እንግዲህ የተቀበልኸውንና የሰማኸውን አስታውስ፤ ታዘዘውም፤ ንስሓም ግባ። ባትነቃ ግን እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ፤ በየትኛው ሰዓት እንደምመጣብህም አታውቅም። ራዕይ 6:2—3

Monday, September 11, 2017

2010 የምን ዓመት ይሁንልን ወይስ በ2010 ምን እንሁን?

እኛ ለእናንተ ፍቅር እንዳለን ሁሉ እርስ በርስ ያላችሁን ፍቅርና ለሌሎችም ያላችሁን ፍቅር ጌታ ያብዛላችሁ፤ ያትረፍርፍላችሁም። 1 ተሰሎንቄ 3:12 

በመጀመሪያ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ማንንም ቡድን ወይም ግለሰብ ለመንቀፍ ወይም የማንም ትምህርት ላይ ጣት ለመቀሰር እንዳልሆነ ለአንባቢዎቼ ለማስገንዘብ እፈልጋለሁ። በዚህ ጦማር ላይ የሚወጡ ማንኛውም ጽሑፎች ሃሳብንና አስተሳሰብን የሚሞግቱ ብቻ እንጂ ከግለሰብ፣ ከድርጅት ወይም ከማንኛውም ቡድን ጋር ጠብ የሌላቸው እንዲሁም ያልወገኑ መሆናቸውን ከወዲሁ ማሳሰብ እወዳለሁ።

ይህ ጦማር የ 2010 ዓ ም አዲስ ዓመትን አስመልክቶ እንኳን አደረሳችሁ ለማለትና ስለ አዲስ ዓመት መርሖች ለመሞገት የተጻፈ መልዕትን መሆኑን አንባቢዎቼ ልብ እንዲሉ አሳስባለሁ። ከላይ ርእሱ ላይ እንደሚነበበው የ2010 ዓ ም መርሗችንን እያስመረጥኩ ነው። የምንጥስበት፣ የምንባረክበት፣ የምንወጣበት፣ ከፍ የምንልበት፣ የሞገስ የምናገኝበት፣ የምንልቅበት ወይስ የምን ይሁንልን? መምረጥ ቢቻል ብዬ ነበር። የኔ ሙግት ግን ሌላ ነው፣ በእርግጥ ለኔ አይደለም ዓመታቶቹ ቀናቶቹም ሁሉ የድል ናቸው ብዬ ነው የማምነው። ተባርከን፣ጥሰን፣ ወጥተን፣ ከፍ ብለን፣ ሞገስ አግኝተንና ልቀን ካበቃን 2010 ዓመታቶች እንዳለፉ የረሳን መሰለኝና ይህን ጽሑፍ ጫር ጫር ለማድረግ ተነሳሁ።  

ክርስትናን ከሌላው እምነት የሚለየው ዋናው ነገር ክርስቶስ በሞቱ ሞትን ድል ነስቶ በትንሳኤው ድል አድራጊነቱን አረጋግጦ ፈጽሞ ወዳለቀ ስራ የጠራን መሆኑ ነው። ክርስቲያን አሁን ሰይጣንን ድል ለማረግ ሳይሆን የሚተጋው፣ በክርስቶስ ያገኘውን ድል ለመውራስ ነው የሚተጋው። በረከትን፣ ከፍታን፣ ሞገስን በክርስቶስ ወራሾች ሆነናል ስለዚህ ዓመት በተቀየረ ቁጥር የመውረስ፣ የመባረክ እያልን ከመታገል ይልቅ የሚበጀን የተሰጠንን የምንወርስበት ዓመት እንዲሆንልን ምን እናድርግ ብለን የምንጠይቅበት እንዲሆ እመክራለሁ። በመጀመርያ እስከዛሬ ባለፉት ዓመታት ያልናቸው ተፈጽመዋል ወይ ብለን ቆም ብለን የምንጠይቅበት ዓመት ይሆንልን ዘንድ እየተመኝሁ፣ የዚህ ዓመት መርሗችንን ከሁሉ በላይ የበረከት፣ የከፍታ፣ የሞገስ፣ የመላቅና የመውጣት ቁልፍ የሆነው እርስ በርስ ያለን ፍቅር እና ለሌሎችም ያለን ፍቅር የሚበዛበትና ብሎም የሚትረፈረፍበት ዓመት ብለን ብናውጀው፥ አንድም ካለንበት የድንብርብር ኑሮ ሳያመን እንወጣለን፣ ደግሞም በተጨማሪ እስካዛሬ ስንመኘው ስንናፍቀው ወደቆየነው፣ ይዘነው እንዳልያዝነው ወደ ቆጠርነው የበረከትና የከፍታ ኑሮ ይዞን ይገባል።

በመጀመርያ ለምን ያለፉት ዓመታት እንዴት አለፉ ብሎ መጠየቅ ለምን ያስፈልጋል? በእኔ አስተሳሰብ የኋላውን የማያውቅ የወደፊቱን ለመቀበል ዝግጁ አይሆንም። በእርግጥ ያልነው ሆኗል ብለን የእውንት መመርመራችን ለሁለት ዋና ዋና ነገሮች ይጠቅመናል። አንዱ ልክ ወይም ስህተት መሆናችንን ለማወቅ ሲጠቅመን ሌላው ደግሞ ለወደፊት እይታችንን እንዴት እንደምናስተካክል ትምህርት ይሰጠናል።

ለምን ፍቅር በዝቶ ይትረፍረፍ? ምክንያቱም ክርስትና ፍቅር ስለሆነ። መጽሓፍ ቅዱስ እንደሚናገረው እግዚአብሄር ፍቅር ነው። ፍቅር ከመሆኑም የተነሳም “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና፤” ዮሓንስ 3:16። ማርቆስ 12 ላይ ክርስቶስ ፍቅር የህግ ሁሉ መጠቅለያ ለመሆኑ እንዲህ አለ “ከሁሉ የሚበልጠው ይህ ነው፤ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤ አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ።’ ሁለተኛውም ይህ ነው፤ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።’ ከእነዚህም የሚበልጥ ትእዛዝ የለም።” ማርቆስ 12፡29 — 31። ምን ማለት ይሆን? እኔ የገባኝን አጠርና ቀለል ብሎ እነሆ።

ጌታ አምላክን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ መውደድ ማለት ሁሉ ነገራችንን ለእግዚአብሄር ማስገዛት ማለት ነው። በሁሉ ነገር ለእርሱ ከተገዛን የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም የሚከብደን አይሆንም ስለዚህ ፈቃዱን ስንፈጽም ወደ ርስታችን ገባን ማለት ነው። እግዚአብሄርን ለመውደዳችን ሌላው ማረጋገጫ ደግሞ ባልንጀራችንን በውደዳችን ነው። ባልንጀራችንን መውደዳችን ደግሞ ምን ያህል እራሳችንን እንደምንወድ ያሳያል። እስቲ እናብራራው፣ ”ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ“ ያለን እግዚአብሔር ስለሆነ እኛም እርሱን ስለምንወድ ለቃሉ እንታዘዛለንና በራሳችን ላይ ሊሆንብን የማንፈልገውን ባንጀራችን ላይ እንዲደርስበት አንፈልግም። ስለዚህም በአስርቱ ትዕዛዝ ላይ ያሉትን ስምንቱን ለመፈጸም አንቸገርም ማለት ነው። እኛ ደግሞ እንታዘዝ እንጂ በጸጋ ዘመን ላይ ስለሆንን መንፈስ ቅዱስ ራሱ ያግዘናል። ባልንጀራየን አላማም፣ ክፉ አላስብበትም፣ አላመነዝርም፣ አልሰርቅም ወዘተ። ይልቁን ያለኝን አካፍላለሁ፣ መልካም ነው ብዬ ያሰብኩትን ሁሉ ለባልንጀራዬ አደርጋለሁ፣ እያየሁ እንዳላየሁ ማለፍ አቆማለሁ፣ ከክፋት ጋር አልተባበርም፣ ለተጎዱ መቆርቆር እጀምራለሁ፣ ባልቴቶችንና ወላጅ የሌላቸውን ህፃናት እየፈለኩ መርዳት እጀምራለሁ፣ የተራቡ አበላለሁ፣ የታረዙ አለብሳለሁ እያለ ይቀጥላል። እስቲ አስቡት እኔ ክርስቲያን ነኝ ብሎ የሚናገር ሁሉ በ2010 እኔ አፈቅራለሁ ብሎ ወገቡን ታጥቆ ቢነሳ በ2011 ላይ የድል፣ የመጣስ፣ የመባረክ፣ የከፍታ፣ የሞገስ እያልን የተመኘናቸውን ዓመታቶች ሁሉ ሳናስበው አጠገባችን እናገኛቸው ነበር። ለነገሩማ ቃሉም የሚለው ያን አይደል፥ “አስቀድማችሁ የእግዚአብሄርን መንግስትና ጽድቁንም ፈልጉ እነዚህ ሁሉ ይጨመርላችኋል።“ ማቴዎስ 6:33  እነዚህ ሁሉ የሚላቸው ምድራዊ የሆኑ በረከቶችን ነው።

ስለዚህ አፈቃሪዎች ለመሆን ምን እናድርግ? መልሱ ፍቅርን እንወቅ ነው። ታዲያ ፍቅርን እንዴት ነው የምናውቀው? ፍቅር የሆነውን ክርስቶስን በማወቅ። ክርስቶስን ስናውቀው ከርሱ ፍቅር ይይዘናል፣ ምክንያቱም ፍቅር የሚያሲዝ ልዩ የሆነ ግርማ ስላለው። በቃ ከርሱ ፍቅር ከያዘን እኛም ልክ እንደርሱ አፍቃሪ ለመሆን ምንም አይከብደንም። ይበልጥ ባወቅነው ቁጥር አፍቃሪነታችን ይበልጥ ይበረታል። የሚገርመው ይህ ማርቆስ 12 ላይ ከክርስቶስ ጋር ስለ ትዕዛዛቶች መበላለጥ የሚጠይቀው ፀሃፊ የክርስቶስን መልስ ሰምቶ መምህር ሆይ መልካም ብለሃል ብሎ ከመለሰለት በኋላ ክርስቶስ ፀሃፊውም “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” ብሎ ነበር የመለሰለት።

”ጸሓፊውም እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ መልካም ብለሃል፤ እርሱ አንድ መሆኑን፣ ከእርሱም ሌላ አለመኖሩን መናገርህ ትክክል ነው፤ እርሱን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም አእምሮህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ መውደድ፣ እንዲሁም ባልንጀራህን እንደ ራስህ መውደድ ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች ይበልጣል።”
ኢየሱስም በማስተዋል እንደ መለሰለት አይቶ፣ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው። ከዚህ በኋላ ሊጠይቀው የደፈረ ማንም አልነበረም።“ ማርቆስ 12:32 — 34

የ2010 ጸሎቴ ያገሬን ሕዝብ የአዲስ አመት መርሖውን ከይሁንልን ወደ እንሁን እንዲለውጠው ነው። የዚህ ዓመት መርሗችንን ከሁሉ በላይ የበረከት፣ የከፍታ፣ የሞገስ፣ የመላቅና የመውጣት ቁልፍ የሆነው እርስ በርስ ያለን ፍቅር እና ለሌሎችም ያለን ፍቅር የሚበዛበትና ብሎም የሚትረፈረፍበት ዓመት ብለን ብናውጀው፥ አንድም ካለንበት የድንብርብር ኑሮ ሳያመን እንወጣለን፣ ደግሞም በተጨማሪ እስካዛሬ ስንመኘው ስንናፍቀው ወደቆየነው፣ ይዘነው እንዳልያዝነው ወደ ቆጠርነው የበረከትና የከፍታ ኑሮ ይዞን ይገባል።

ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች የፀለየውን እኔም ለአገሬ ልጆች ልፀልይና ላጠቃልል፥ እርስ በርስ ያላችሁን ፍቅርና ለሌሎችም ያላችሁን ፍቅር ጌታ ያብዛላችሁ፤ ያትረፍርፍላችሁም።

Wednesday, August 23, 2017

መታወቅ ወይስ ማወቅ?

. . . . . . . . በዚያ ጊዜ፣ ‘ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንት ክፉዎች፤ ከእኔ ራቁ’ ብዬ በግልጽ እነግራቸዋለሁ። ማቴዎስ 7: 23
በመጀመሪያ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ማንንም ቡድን ወይም ግለሰብ ለመንቀፍ ወይም የማንም ትምህርት ላይ ጣት ለመቀሰር እንዳልሆነ ለአንባቢዎቼ ለማስገንዘብ እፈልጋለሁ። የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ያለንበት ዘመን የመጨረሻው ዘመን መሆኑን ግነዛቤ ውስጥ በማስገባት ቀለል ባለ ገለጻ የራሴን እይታ ለማስተላለፍና ሌሎችንም ለማነጽ ነው።

“አላወቅኋችሁም” የምትለውን ቃል በጣም የምፈራት ይህን ቃል ሳነብ ነው። ምክንያቱም አውቀዋለሁ የምንለው ሁሉ እኛን ላያውቅን እንደሚችል እንዳስበው ስላምታስገድደኝ ነው። ለምሳሌ ብዙ ታዋቂ ሰዎችን ብዙ ጊዜ በተለያየ መገናኛ ብዙሃን ስለምናያቸው ወይም ስለነሱ ማንበብ ስለቻልን የምናውቃቸው ያህል ይሰማናል። በእርግጥ ይህ አይነት ዕውቀት ራሱን የቻለ ደረጃ ያለው ዕውቀት ነው። ከዚህ አልፈን ዕውቀትን መተንተን የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ስላልሆነ በዚሁ እንለፈው። ከዛም አልፈን በደንብ ቀረብ ብለን የምናውቃውቸው ሰዎች ይኖራሉ፣ ምን እንደሚወዱ ምን እንደሚጠሉና ከዛም ዘልቀን የግል ጉዳያቸውንም ሳይቀር ጠንቅቀን የምናውቅላቸው ሰዎች እኛን ያውቁናል ብለን በልበ ሙሉነት የምንናገርላቸው ሰዎች ይኖሩ ይሆናል።

አንድን ሰው ያወቅነው ስለመሰለን ወይም በደንብም ስላወቅነው በእርግጠኝነት ያ ሰው እኛን ያውቀናል ማለት አይቻልም። ጉዱ የሚታየው ስለማውቃቸው ያውቁናል ብለን ያሰብናቸው ሰዎች ስለኛ ሲጠየቁ ስለኛ ጠንቅቀው አውቀው መመለስ መቻላቸውን ስናረጋግጥ ብቻ ነው። ባጭሩ ያወቅነው የመሰለንን ነገር ሁሉ አውቀነዋል ማለት እንደማይቻል ሁሉ ፤ ያወቅነው ሁሉ አያውቀነም። ለዚህም ነው፣ “አላወቅኋችሁም” የምትለውን ቃል በጣም የምፈራት ይህን ቃል ሳነብ ነው ያልኩት።

በማቴዎስ 7 እና 25 ላይ የምናነበው የመጨረሻ ፍርድ በሚሆንበት ጊዜ የሚከሰተውን ሁኔታ ነው። በዚያም “አላወቅኋችሁም” የሚባሉት ሰዎች ”ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ“ ብለው የሚጠሩቱ፣ አጠራራቸውም የሚመስለው “እንዴ? እኛኮ እናውቅሃለን ከማወቅም አልፈን እኮ በስምህ ብዙ ሰርተናል፣ ስላንተ እኮ ብዙ አውርተናል” የሚል ነው። ምስክሮች ኧረ አሉን የሚሉም ይመስላሉ። በተቃራኒው ደግሞ “አውቄያችኋለው” የተባሉቱ “እንዲህ አርገን ነበር እኮ፣ እንዲህ ብለን ነበር እኮ” እያሉ ሲደክሙ አይሰሙም። ኧረ ማድረጋችንንም አናስታውስም ነው የሚሉት።

በዘመናችንም ይህ ታሪክ እየተሰራ ያለ ይመስላል። በተለይም የኢንፎርሜሽን ዘመን ከመሆኑ የተነሳ እንዲሁም የማህበራዊ መገናኛዎች መፈጠርና በቀላሉ ለብዙሃኑ በአንድ መድረክ ብቻ መደረስ የሚቻልበት ዘመን ላይ ስለደረስን እዩኝ እዩኝ ማለት የጊዜያችን ትልቁ ፈተና ነው። በአሁኑ ዘመን እራሳችንን በራሳችን ቀድተን የምንኖርበትን ቤት ይሁን፣ የለበስነውን ልብስ ወይ የምንነዳውን መኪና ይሁን ወይ ቁመናችንን ለማሳየት ግልጽ ባልሆነ መልኩ እዚህ ግቡ የማይናሉ ዓላማቸው ምን እንደሆነ የማይታወቁ መልዕክቶችን ማስተላለፍ የጊዜው ብሂል ከሆነ ቆይቷል። ከዛም አልፎ የቴሌቪዥን አገልግሎት ከሌላችሁ ወንጌል መስበክ አይቻልም የተባለ እስኪመስል ድረስ  ብሎ መናገር የማይከብድበት ጊዜ ሆኗል። ኧረ ይሄ ነገር ልክ አይደለም ብሎ ሃሳብ መሰንዘር ጊዜው እንዳለፈበት ሰው አስቆጠሮ “እንዴ ወጣት አይደለህ፣ እንዴ አራዳ መስለኽኝ፣ ውይ የክፍለ ሃገር ልጅ ነህ እንዴ” የሚያስብልበት ደረጃ ደርሰናል።

እነዚህ “አላወቅኋችሁም” የተባሉ ሰዎች በእርግጠ ስለ ክርስቶስ ብዙ የሚያወሩ፣ ከዛም አልፈው ተዓምራትና ድንቅ የሚፈጽሙ ኧረ እንዳውም በስሙ ሁሉ አጋንንት የሚያስወጡ ናቸው። ታዲያ እንዲህ ማለትህ በዚህ ዘመን የምናያቸው ይህን አይነት ነገር የሚያደጉ ሰዎች “አላወቅኋችሁም” ይባላሉ ልትለን ነው? ብላችሁ መጠየቃችሁ ደግ ነው። እንግዲህ ከጠየቃችሁ መልስ ብዬ የምሰጣችሁ የሚከተለውን ይሆናል።

በክርስቶስ ዘንድ የሚታወቁትንና የማይታወቁትን ለመለየት መልሱን የምናገኘው በዛው በማቴዎስ 7 እና 25 ላይ ነው።
በማቴዎስ 7 : 15 — 18 “በውስጣቸው ነጣቂ ተኵላዎች ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው መካከላችሁ በመግባት ከሚያሸምቁ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ፤ ከእሾህ ቍጥቋጦ ወይን፣ ከኵርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁም ጥሩ ዛፍ ሁሉ ጥሩ ፍሬ፣ መጥፎ ዛፍ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል። ጥሩ ዛፍ መጥፎ ፍሬ፣ መጥፎም ዛፍ ጥሩ ፍሬ ማፍራት አይችልም። 

”ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ“ ሲለን ስለ ክርስቶስ ብዙ የሚያወሩ፣ ከዛም አልፈው ተዓምራትና ድንቅ የሚፈጽሙ እና በስሙ አጋንንት የሚያስወጡ ሁሉ በደፈናው “አላወቅኋችሁም” ይባላሉ ብዬ አላምንም። ነገር ግን እንዲህ ማድረግ በራሱ ብቻ ፍሬ እንዳልሆነ ያሳየናል እንጂ። ፍሬ ለማየት ጊዜ ወስዶ መከታተል ይጠይቃል።

ለኔ “አላወቅኋችሁም” ይባላሉ ብዬ የማምነው፥
1 ከክርስቶስ ወንጌል ይልቅ የሰውን ፍልስፍና ወይም መጽሓፍ አንብበው እኔን የገባኝ ካልገባችሁ የሚሉ ወንጌል ሳይሆን ግን የሚመስል ፍልስፍና ይዘው ሌላው ካልገባው ብለው በየሰፈሩና በየአገሩ እየዞሩ ወንጌልን የሚሸቅጡ፤
2 ከክርስቶስ ስም ይልቅ ለራሳቸው ስምና ማዕረግ ብዙ የሚተጉ፣ ምስላቸውን በየቦታው በመለጠፍ ለመታየት የቋመጡ እና የነሱ አስተምህሮ ብቻ እንዲሰማ የሚሯሯጡ፤
3 በትምህርታቸው ላይ ጥያቄ ያነሳን በፍጥነት የሆነ ጎራ ጋ ወስደው የሚፈርጁ፣ ከቻሉም እኔን ከተቃወምክ ትሞታለህ ወይ እግዚአብሄር ይቀጣሃል ከማለት የማይቆጠቡ ደፋሮች፤
4 ነገራቸው ሁሉ ከገንዘብ ጋር የተቆራኘ፣ ብልጣልጥ በሆነ አቀራረብ በትምህርታቸው የሰውን ስሜት አስደስተው ከቻሉ ከየቤተክርስቲያኑ ሰዎች አፈናቅለው የራሳቸውን ቤተክርስቲያን ለመትከል ወደኋላ የማይሉ፣ ካልቻሉ አይን ባወጣ መልኩ ገንዘብ ጠይቀው ሰብስበው የሚሄዱ፤
5 ከእውነተኛው የእግዚአብሄር ቃል ይልቅ ለሰዎች የሚመች ስኬት የማግኛ፣ ከድህነት ማምለጫ፣ ከበሽታ መዳኛ እና የመሳሰሉ ምድር ተኮር ጉዳዮች ላይ በሰፊው ጊዜ የሚያጠፉ፤ ከወንጌል ይልቅ ስሜት አነቃቂ የሆኑ አስተምህዎች ላይ ያተኮሩ( motivational speaking)፣
6 ፍሬ ብለው የሚያሳዩት ምን ያህል ገንዘብ እንዳላቸው፣ ምን ያህል አባል እንደመዘገቡ፣ ምን ያህል በዓለም ላይ ዝናን እንዳገኙ ሲሆን፣ በኛ ትምህርት ወይ ተዓምራት ጌታን የተቀበሉ እያሉ ባልለፉበት ነገር የሚመጻደቁና የቁጥር ስሌት ማሳየት የሚወዱ……. “ያልደከማችሁበትን እንድታጭዱ ላክኋችሁ፤ አድካሚውን ሥራ ሌሎች ሠሩ፤ እናንተም የድካማቸውን ፍሬ ሰበሰባችሁ።” ዮሓንስ 4:38
7 ያለምንም ማስረጃ በድፍረት እግዚአብሄር እንዲህ ብሎኛል የሚሉና፣ መረጃና መሰረት የሌለው ወሬ በድፍረት የሚያወሩ፤
8 ለሚያምነውም ለማያምነውም ተዓምራት ማድረግና ትንቢት መናገር የሚያዘወትሩና፣ መጽሓፍ ቅዱስን ለራሳቸው የውሸት ትምህርት እንደ ደጋፊ የሚወስዱ እንጂ ላነበቡት መጽሓፍም ይሁን ለተገረሙበት ፍልስፍና መጽሓፍ ቅዱስን እንደ መመረመርያ የማይጠቀሙ።

በተቃራኒው “ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን“ የተባሉት፥
1 ለማዕረጋቸው የማይጨነቁ፣ ከራሳቸው ስም ይልቅ ለክርስቶስ ስም የሚሞቱ፣ ልታይ ልታይ የማይሉ፣
2 ሰው የማያውቃቸው ብቻ ሳይሆኑ የሚያደርጉትን ነገር እንኳን የተለየ እንዳልሆነ የሚሰማቸው፣
3 ብልጣልጥነት የማይገባቸው፣ ነገራቸው ሁሉ ከገንዘብ ጋር ያልተቆራኘ፣ ሃብታም የመሆን ከባድ ምኞት የሌላቸው፣
4 ተዓምራትና ድንቅን በየቦታው እየዞሩ የማይከተሉ፣ ምድር ጊዜያዊ መኖርያቸው መሆኑን ስለተረዱ የዚህ ዓለም ጥቅማ ጥቅም የማያታልላቸው፣
5 የክርስቶስ አምባሣደር እንደሆኑ ስለገባቸው እራሳቸውን ከማንም ቡድን ይሁን ተቋም ጋ የማያቆራኙ፣
6 እንደ ክርስቶስ መኖር የህይወታቸው ዘይቤ ስለሆነ ለሚያደርጉት ነገር ማስረጃ እንኳን የማይሰበስቡ፣ ቁጥር እያሰሉ በኔ አገልግሎት ይህን ያህል ሰው እንዲህ ሆነ የማይሉ ‘ጌታ ሆይ፤ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህ? ወይም ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? እንዲሁም ታመህ ወይም ታስረህ አይተን መቼ ጠየቅንህ?’ በማቴዎስ 25: 37᎐39 ብለው የጠየቁ።


ከዚህም በላይ ለሁለቱም ጎራ ዝረዝር ማውጣት ይቻላል። ዋናው ጥያቄ ግን እኔስ የት እሆን ያለሁት ብሎ መጥየቅ ነው። እግዚአብሔር ባስቅመጠን ቦታ ላይ ሆነን የእነ እከሌ መታወቅ አስደምሞን እኔም ካልታወኩ ብለን ከተቀመጥንበት ቦታ ተነስተን እንደ ዝንጉዎቹ ልጃገረዶች ዘየት ልንገዛ ስንሄድ በድንገት ሙሽራው መጥቶ ከሰርጉ እንዳንቀር እግዚአብሔር ይርዳን።  

Thursday, August 17, 2017

በእርግጥ መጽሐፉ ምን ይላል?

ለዚህ ጽሑፍ ምክንያት የሆነኝን ጉዳይ አንስቼ ልጀምር። በቅርቡ ከአንድ የቅርብ ወዳጄ ጋር ሆነን ስለ ብልጽግና ወንጌል እንዲሁም አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ስለተስፋፋው ”የነብያት“ እንቅስቃሴ አንስተን ስንጫወት የሊሊ መዝሙር እንደ አንድ ጥሩ መልስ መቅረቡ ስላስገረመኝ እስኪ ምንአልባት ይህ ጉዳይ ለብዙዎች የመነጋገርያ ጉዳይ ስለሆነ በሰፊው ልምጣበት ብዬ ይህን ጽሁፈ ጫር ጫር እንዳደርግ ምክንያት ሆነኝ።

ከአንኳሩ ጉዳይ ልጀምርና ፤ የትኛውንም የክርስትና አስተምህሮ መመዘን ያለብን በምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ በአጭሩና በማያሻማ መልኩ ስንመልሰው በመጽሓፍ ቅዱስ ብለን ነው። ለዚህም ነው ወንድሜ በመዝሙር መልስ ለመስጠት ሲታገል ሳየው ያሳዘነኝ። መጽሓፉ በእርግጥ ምን ይላል? አትታመሙም፣ አትደኽዪም፣ ችግር ወይም መከራ አያገኛችሁም፣ አተጎሳቆሉም፣ አትሞቱም ይላል? ሃብት በምድር አከማቹ፣ ጤነኞች ካልሆናችሁ ስለመዳናችሁ ተጠራጠሩ፣ ችግር ወይም መከራ ከመጣባችሁ የኔ ደቀ መዛሙርት ላለመሆናችሁ ምልክት ይሁን፣ ደግሞም የምን መጎሳቆል እንደዛማ ከሆናችሁ የኔ አይደላችሁም ይላል?

በእርግጥ መጽሓፉ ምን ይላል? እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንትም እኔን ምሰሉ ሲል ጳውሎስ ፤ ክርስቶስ በእርግጥ በምድር ሳለ በምድራዊ ቁሳቁስ ልቡ ተይዞ በዘመኑ አንደኛ የተባለ መኖርያ ቤት ውስጥ ይኖር ነበር፣ ሲጓጓዝም ምርጥ ምርጥ ጀልባዎች ላይ ይሳፈር ነበር እንዳውም አብዛኛዎቹ ጀልባዎች የግሎቹ ነበሩ፣ ደቀ መዛሙርቱም ዋናው ስራቸው የእርሱ ክቡር ዘበኛ መሆን ነበር፣ ከህዝብ በተሰበሰበ ገንዘብ የተሰራ በጊዜው አለ የተባለ መድረክ ላይ ነበር ትምህርት የሚያስተምረው ማለቱ ይሆን?

በእርግጥ መጽሓፉ ምን ይላል? ኧረ እንዳውም እኔ ስሄድ በእኔ ስም ህዝብ ሰብስባችሁ ሰዎችን ሰብስባችሁ ደስ ደስ የሚሉ ቃላቶች የሞሉባቸውን ትምህርቶች እያስተማራችሁ፣ አጋንንት በስሜ እያስወጣችሁ፣ ሰዉን ስጋዊ ፈውስ ብቻ እየፈወሳችሁ፣ ከቻላችሁ በዶላር ካልቻላችሁም ደግሞ በብር ገንዘብ እየሰበሰባችሁ ጠብቁኝ፣ ስመጣ ሂሳብ አወራርዳለሁ ይላል?በእርግጥ መጽሓፉ ይህን ይላል?
በእርግጥ መጽሓፉ ምን ይላል?ከእናንተ ላነሰው ለዛ ወንደማችሁ ወይም እህታችሁ ካልቻላችሁ በፌስ ቡክ ከቻላችሁ በራሳችሁ ቴሌቪዥን ምን ያህል ከሌላው የተሻለ ዕውቀትና የኑሮ ደረጃ እንዳላችሁ ጉራችሁን እየዘራችሁ ጠብቁኝ እንጂ የምን የተራበ ማብላት፣ የተጠማ ማጠጣት፣ የታረዘ ማልበስ ነው ለዛውም ማንም ሳያያችሁ፣ ሳይጨበጨብላችሁ ይል ይሆን?  

በእርግጥ መጽሓፉ ምን ይላል?እንኳን ካላችሁ ላይ ልትሰጡ ቀርቶ ከቻላችሁ በተዓምር ብር አባዝታችሁ ካልሆነም በእኔ ስም ተከልላችሁ ምንም የማያውቁትን የዋሆች አሳምናችሁ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በምድር አከማችታችሁ የሚያማምሩ ልብሶችንና  መኪናዎችን በየቀኑ እያቀያየራችሁ በሃብት ሰክራችሁ ስስትን ጠግባችሁ እኔን ከማያውቁኝና ከፈሪሳውያን በልጣችሁ ካልጠበቃችሁኝማ እኔም በተራዬ አላውቃችሁም እላችኋለሁ ይል ይሆን?  

በእርግጥ መጽሓፉ ምን ይላል?እስቲ እኔ ከምነግራችሁ እራሱ መጽሓፉን ምን እንደሚል አብረን አናነበውም።
ዮሐንስ 16: 33 “በእኔ ሰላም እንዲኖራችሁ፣ ይህን ነግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”
ማቴዎስ 10: 38-39 መስቀሉን ተሸክሞ የማይከተለኝ የእኔ ሊሆን አይገባውም። ሕይወቱን ሊያድን የሚፈልግ ያጠፋታል፤ ሕይወቱን ስለ እኔ አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያገኛታል።
ሮሜ 8: 35 ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? ችግር ነው ወይስ ሥቃይ፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ረሀብ፣ ወይስ ዕራቍትነት፣ ወይስ አደጋ ወይስ ሰይፍ?
1 ጴጥሮስ 4: 1 እንግዲህ ክርስቶስ በሥጋው መከራን ስለ ተቀበለ እናንተም በዚሁ ዐላማ ታጥቃችሁ ተነሡ፤ ምክንያቱም በሥጋው መከራን የሚቀበል ሰው ኀጢአትን ትቶአል።
1 ጴጥሮስ 3 : 13,14 መልካም ነገር ለማድረግ ብትቀኑ የሚጐዳችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራ ቢደርስባችሁ ብፁዓን ናችሁ፤ “ዛቻቸውን አትፍሩ፤ አትታወኩም።” 
ገላትያ 6: 2-3አንዱ የሌላውን ከባድ ሸክም ይሸከም፤ በዚህም ሁኔታ የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ። አንድ ሰው ምንም ሳይሆን ትልቅ የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላል። 
ፊልጵስዩስ 1: 29-30 በክርስቶስ እንድታምኑ ብቻ ሳይሆን ስለ እርሱ መከራ እንድትቀበሉም ይህ ጸጋ ተሰጥቶአችኋልና፤ ቀድሞ እንዳያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ በምትሰሙት በዚያው ዐይነት ተጋድሎ እናንተም እያለፋችሁ ነውና።
1 ጴጥሮስ 2: 21የተጠራችሁትም ለዚሁ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው።
ሮሜ8: 18የአሁኑ ዘመን ሥቃያችን ወደ ፊት ሊገለጥ ካለው ለእኛ ከተጠበቀልን ክብር ጋር ሲነጻጸር ምንም እንዳይደለ እቈጥራለሁ።
ማቴዎስ 7: 21 - 23 “በሰማይ ያለውን ያባቴን ፈቃድ ሳይፈጽም ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ አይገባም። በዚያ ቀን ብዙዎች፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህ አጋንንት አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ታምራት አላደረግንምን?’ ይሉኛል። በዚያ ጊዜ፣ ‘ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንት ክፉዎች፤ ከእኔ ራቁ’ ብዬ በግልጽ እነግራቸዋለሁ።

በመጨረሻብ ማቴዎስ 25 ላይ ከቁጥር 23 ጀምሮ እስከ 46 ያለውን እራሳችሁ እንድታነቡ እየጋበዝኩ፡ እንደ ማጠቃለያ በዘመናችን ለተከሰቱት አዲስ ለሚመስሉ ነገር ግን ከነጳውሎስ ዘመን ጀምሮ ለነበሩ እንግዳ መሰል አስተምህሮዎች እጃችንን ከመስጠታችን በፊት በእርግጥ መጽሓፉ ምን ይላል ብለን መጠየቅ እንጂ እነ እከሌ እኮ እንዲህ ብለው ዘምረዋል እንዲህ ብለው አስተምረዋል በማለት ለጆሮዋችን በሚመች መልኩ የመጣውን ትምህርት ይሁን ትንቢት አስተናጋጆች እንዳንሆን እንጠንቀቅ። ይልቁን የዘመኑ ትምህርትና ትንቢት ምነው የተራራውን ስብከት የሚሰብክ እና የሚተነብይ ያልሆነው? ምነው ዝቅ በሉ፣ ታገሱ፣ በጽድቅ ኑሩ፣ ያላችሁን ስጡ፣ የተገፉትን ፈልጉ፣ልታይ ልታይ ከማለት ተቆጠቡ የሚል ትምህርት እና ትንቢት የሞኝነት ያህል የተቆጠረው? እንዳያሰናክሏችሁ ከዚህ ዓለም ተግዳሮቶች ተጠበቁ ሳይሆን በዓለም እንደ ድል አድራጊነት የሚያስቆጥሩት ቁሳቁስ እና ገንዘብ ታገኛላችሁ ይሆንላችኋል ይሳኩላችኋል ላይ ብቻ ተነጠለጠሉ? ይህን መጠየቅ በዘማናዊ ክርስትና ለተጠመቁት እንደ ሞኝነት ነውም አይደል?


በእርግጥ መጽሓፉ ምን ይላል?አትታመሙም፣ አትደኽዪም፣ ችግር ወይም መከራ አያገኛችሁም፣ አተጎሳቆሉም፣ አትሞቱም ይላል? ሃብት በምድር አከማቹ፣ ጤነኞች ካልሆናችሁ ስለመዳናችሁ ተጠራጠሩ፣ ችግር ወይም መከራ ከመጣባችሁ የኔ ደቀ መዛሙርት ላለመሆናችሁ ምልክት ይሁን፣ ደግሞም የምን መጎሳቆል እንደዛማ ከሆናችሁ የኔ አይደላችሁም ይላል?

እንደዛማ ከሆነ ብልጽግና ወንጌልን ብልጥ - ግና ብለን ብንጠራው ይሻል ይሆን?