Wednesday, August 23, 2017

መታወቅ ወይስ ማወቅ?

. . . . . . . . በዚያ ጊዜ፣ ‘ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንት ክፉዎች፤ ከእኔ ራቁ’ ብዬ በግልጽ እነግራቸዋለሁ። ማቴዎስ 7: 23
በመጀመሪያ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ማንንም ቡድን ወይም ግለሰብ ለመንቀፍ ወይም የማንም ትምህርት ላይ ጣት ለመቀሰር እንዳልሆነ ለአንባቢዎቼ ለማስገንዘብ እፈልጋለሁ። የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ያለንበት ዘመን የመጨረሻው ዘመን መሆኑን ግነዛቤ ውስጥ በማስገባት ቀለል ባለ ገለጻ የራሴን እይታ ለማስተላለፍና ሌሎችንም ለማነጽ ነው።

“አላወቅኋችሁም” የምትለውን ቃል በጣም የምፈራት ይህን ቃል ሳነብ ነው። ምክንያቱም አውቀዋለሁ የምንለው ሁሉ እኛን ላያውቅን እንደሚችል እንዳስበው ስላምታስገድደኝ ነው። ለምሳሌ ብዙ ታዋቂ ሰዎችን ብዙ ጊዜ በተለያየ መገናኛ ብዙሃን ስለምናያቸው ወይም ስለነሱ ማንበብ ስለቻልን የምናውቃቸው ያህል ይሰማናል። በእርግጥ ይህ አይነት ዕውቀት ራሱን የቻለ ደረጃ ያለው ዕውቀት ነው። ከዚህ አልፈን ዕውቀትን መተንተን የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ስላልሆነ በዚሁ እንለፈው። ከዛም አልፈን በደንብ ቀረብ ብለን የምናውቃውቸው ሰዎች ይኖራሉ፣ ምን እንደሚወዱ ምን እንደሚጠሉና ከዛም ዘልቀን የግል ጉዳያቸውንም ሳይቀር ጠንቅቀን የምናውቅላቸው ሰዎች እኛን ያውቁናል ብለን በልበ ሙሉነት የምንናገርላቸው ሰዎች ይኖሩ ይሆናል።

አንድን ሰው ያወቅነው ስለመሰለን ወይም በደንብም ስላወቅነው በእርግጠኝነት ያ ሰው እኛን ያውቀናል ማለት አይቻልም። ጉዱ የሚታየው ስለማውቃቸው ያውቁናል ብለን ያሰብናቸው ሰዎች ስለኛ ሲጠየቁ ስለኛ ጠንቅቀው አውቀው መመለስ መቻላቸውን ስናረጋግጥ ብቻ ነው። ባጭሩ ያወቅነው የመሰለንን ነገር ሁሉ አውቀነዋል ማለት እንደማይቻል ሁሉ ፤ ያወቅነው ሁሉ አያውቀነም። ለዚህም ነው፣ “አላወቅኋችሁም” የምትለውን ቃል በጣም የምፈራት ይህን ቃል ሳነብ ነው ያልኩት።

በማቴዎስ 7 እና 25 ላይ የምናነበው የመጨረሻ ፍርድ በሚሆንበት ጊዜ የሚከሰተውን ሁኔታ ነው። በዚያም “አላወቅኋችሁም” የሚባሉት ሰዎች ”ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ“ ብለው የሚጠሩቱ፣ አጠራራቸውም የሚመስለው “እንዴ እኛኮ እናውቅሃለን ከማወቅም አልፈን እኮ በስምህ ብዙ ሰርተናል፣ ስላንተ እኮ ብዙ አውርተናል” የሚል ነው። ምስክሮች ኧረ አሉን የሚሉም ይመስላሉ። በተቃራኒው ደግሞ “አውቄያችኋለው” የተባሉቱ “እንዲህ አርገን ነበር እኮ፣ እንዲህ ብለን ነበር እኮ” እያሉ ሲደክሙ አይሰሙም። ኧረ ማድረጋችንንም አናስታውስም ነው የሚሉት።

በዘመናችንም ይህ ታሪክ እየተሰራ ያለ ይመስላል። በተለይም የኢንፎርሜሽን ዘመን ከመሆኑ የተነሳ እንዲሁም የማህበራዊ መገናኛዎች መፈጠርና በቀላሉ ለብዙሃኑ በአንድ መድረክ ብቻ መደረስ የሚቻልበት ዘመን ላይ ስለደረስን እዩኝ እዩኝ ማለት የጊዜያችን ትልቁ ፈተና ነው። በአሁኑ ዘመን እራሳችንን በራሳችን ቀድተን የምንኖርበትን ቤት ይሁን፣ የለበስነውን ልብስ ወይ የምንነዳውን መኪና ይሁን ወይ ቁመናችንን ለማሳየት ግልጽ ባልሆነ መልኩ እዚህ ግቡ የማይናሉ ዓላማቸው ምን እንደሆነ የማይታወቁ መልዕክቶችን ማስተላለፍ የጊዜው ብሂል ከሆነ ቆይቷል። ከዛም አልፎ የቴሌቪዥን አገልግሎት ከሌላችሁ ወንጌል መስበክ አይቻልም የተባለ እስኪመስል ድረስ  ብሎ መናገር የማይከብድበት ጊዜ ሆኗል። ኧረ ይሄ ነገር ልክ አይደለም ብሎ ሃሳብ መሰንዘር ጊዜው እንዳለፈበት ሰው አስቆጠሮ “እንዴ ወጣት አይደለህ፣ እንዴ አራዳ መስለኽኝ፣ ውይ የክፍለ ሃገር ልጅ ነህ እንዴ” የሚያስብልበት ደረጃ ደርሰናል።

እነዚህ “አላወቅኋችሁም” የተባሉ ሰዎች በእርግጠ ስለ ክርስቶስ ብዙ የሚያወሩ፣ ከዛም አልፈው ተዓምራትና ድንቅ የሚፈጽሙ ኧረ እንዳውም በስሙ ሁሉ አጋንንት የሚያስወጡ ናቸው። ታዲያ እንዲህ ማለትህ በዚህ ዘመን የምናያቸው ይህን አይነት ነገር የሚያደጉ ሰዎች “አላወቅኋችሁም” ይባላሉ ልትለን ነው ብላችሁ መጠየቃችሁ ደግ ነው። እንግዲህ ከጠየቃችሁ መልስ ብዬ የምሰጣችሁ የሚከተለውን ይሆናል።

በክርስቶስ ዘንድ የሚታወቁትንና የማይታወቁትን ለመለየት መልሱን የምናገኘው በዛው በማቴዎስ 7 እና 25 ላይ ነው።
በማቴዎስ 7 15 — 18 “በውስጣቸው ነጣቂ ተኵላዎች ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው መካከላችሁ በመግባት ከሚያሸምቁ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ፤ ከእሾህ ቍጥቋጦ ወይን፣ ከኵርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁም ጥሩ ዛፍ ሁሉ ጥሩ ፍሬ፣ መጥፎ ዛፍ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል። ጥሩ ዛፍ መጥፎ ፍሬ፣ መጥፎም ዛፍ ጥሩ ፍሬ ማፍራት አይችልም። 

ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ ሲለን ስለ ክርስቶስ ብዙ የሚያወሩ፣ ከዛም አልፈው ተዓምራትና ድንቅ የሚፈጽሙ እና በስሙ አጋንንት የሚያስወጡ ሁሉ በደፈናው “አላወቅኋችሁም” ይባላሉ ብዬ አላምንም። ነገር ግን እንዲህ ማድረግ በራሱ ብቻ ፍሬ እንዳልሆነ ያሳየናል እንጂ። ፍሬ ለማየት ጊዜ ወስዶ መከታተል ይጠይቃል።

ለኔ “አላወቅኋችሁም” ይባላሉ ብዬ የማምነው፥
1 ከክርስቶስ ወንጌል ይልቅ የሰውን ፍልስፍና ወይም መጽሓፍ አንብበው እኔን የገባኝ ካልገባችሁ የሚሉ ወንጌል ሳይሆን ግን የሚመስል ፍልስፍና ይዘው ሌላው ካልገባው ብለው በየሰፈሩና በየአገሩ እየዞሩ ወንጌልን የሚሸቅጡ፤
2 ከክርስቶስ ስም ይልቅ ለራሳቸው ስምና ማዕረግ ብዙ የሚተጉ፣ ምስላቸውን በየቦታው በመለጠፍ ለመታየት የቋመጡ እና የነሱ አስተምህሮ ብቻ እንዲሰማ የሚሯሯጡ፤
3 በትምህርታቸው ላይ ጥያቄ ያነሳን በፍጥነት የሆነ ጎራ ጋ ወስደው የሚፈርጁ፣ ከቻሉም እኔን ከተቃወምክ ትሞታለህ ወይ እግዚአብሄር ይቀጣሃል ከማለት የማይቆጠቡ ደፋሮች፤
4 ነገራቸው ሁሉ ከገንዘብ ጋር የተቆራኘ፣ ብልጣልጥ በሆነ አቀራረብ በትምህርታቸው የሰውን ስሜት አስደስተው ከቻሉ ከየቤተክርስቲያኑ ሰዎች አፈናቅለው የራሳቸውን ቤተክርስቲያን ለመትከል ወደኋላ የማይሉ፣ ካልቻሉ አይን ባወጣ መልኩ ገንዘብ ጠይቀው ሰብስበው የሚሄዱ፤
5 ከእውነተኛው የእግዚአብሄር ቃል ይልቅ ለሰዎች የሚመች ስኬት የማግኛ፣ ከድህነት ማምለጫ፣ ከበሽታ መዳኛ እና የመሳሰሉ ምድር ተኮር ጉዳዮች ላይ በሰፊው ጊዜ የሚያጠፉ፤ ከወንጌል ይልቅ ስሜት አነቃቂ የሆኑ አስተምህዎች ላይ ያተኮሩ motivational speaking)
6 ፍሬ ብለው የሚያሳዩት ምን ያህል ገንዘብ እንዳላቸው፣ ምን ያህል አባል እንደመዘገቡ፣ ምን ያህል በዓለም ላይ ዝናን እንዳገኙ ሲሆን፣ በኛ ትምህርት ወይ ተዓምራት ጌታን የተቀበሉ እያሉ ባልለፉበት ነገር የሚመጻደቁና የቁጥር ስሌት ማሳየት የሚወዱ……. “ያልደከማችሁበትን እንድታጭዱ ላክኋችሁ፤ አድካሚውን ሥራ ሌሎች ሠሩ፤ እናንተም የድካማቸውን ፍሬ ሰበሰባችሁ።” ዮሓንስ 438
7 ያለምንም ማስረጃ በድፍረት እግዚአብሄር እንዲህ ብሎኛል የሚሉና፣ መረጃና መሰረት የሌለው ወሬ በድፍረት የሚያወሩ፤
8 ለሚያምነውም ለማያምነውም ተዓምራት ማድረግና ትንቢት መናገር የሚያዘወትሩና፣ መጽሓፍ ቅዱስን ለራሳቸው የውሸት ትምህርት እንደ ደጋፊ የሚወስዱ እንጂ ላነበቡት መጽሓፍም ይሁን ለተገረሙበት ፍልስፍና መጽሓፍ ቅዱስን እንደ መመረመርያ የማይጠቀሙ።

በተቃራኒው “ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን“ የተባሉት፥
1 ለማዕረጋቸው የማይጨነቁ፣ ከራሳቸው ስም ይልቅ ለክርስቶስ ስም የሚሞቱ፣ ልታይ ልታይ የማይሉ፣
2 ሰው የማያውቃቸው ብቻ ሳይሆኑ የሚያደርጉትን ነገር እንኳን የተለየ እንዳልሆነ የሚሰማቸው፣
3 ብልጣልጥነት የማይገባቸው፣ ነገራቸው ሁሉ ከገንዘብ ጋር ያልተቆራኘ፣ ሃብታም የመሆን ከባድ ምኞት የሌላቸው፣
4 ተዓምራትና ድንቅን በየቦታው እየዞሩ የማይከተሉ፣ ምድር ጊዜያዊ መኖርያቸው መሆኑን ስለተረዱ የዚህ ዓለም ጥቅማ ጥቅም የማያታልላቸው፣
5 የክርስቶስ አምባሣደር እንደሆኑ ስለገባቸው እራሳቸውን ከማንም ቡድን ይሁን ተቋም ጋ የማያቆራኙ፣
6 እንደ ክርስቶስ መኖር የህይወታቸው ዘይቤ ስለሆነ ለሚያደርጉት ነገር ማስረጃ እንኳን የማይሰበስቡ፣ ቁጥር እያሰሉ በኔ አገልግሎት ይህን ያህል ሰው እንዲህ ሆነ የማይሉ ‘ጌታ ሆይ፤ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህ? ወይም ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? እንዲሁም ታመህ ወይም ታስረህ አይተን መቼ ጠየቅንህ?’ በማቴዎስ 25 37᎐39 ብለው የጠየቁ።


ከዚህም በላይ ለሁለቱም ጎራ ዝረዝር ማውጣት ይቻላል። ዋናው ጥያቄ ግን እኔስ የት እሆን ያለሁት ብሎ መጥየቅ ነው። እግዚአብሔር ባስቅመጠን ቦታ ላይ ሆነን የእነ እከሌ መታወቅ አስደምሞን እኔም ካልታወኩ ብለን ከተቀመጥንበት ቦታ ተነስተን እንደ ዝንጉዎቹ ልጃገረዶች ዘየት ልንገዛ ስንሄድ በድንገት ሙሽራው መጥቶ ከሰርጉ እንዳንቀር እግዚአብሔር ይርዳን።  

No comments:

Post a Comment