Friday, October 9, 2020

በእ/ር ቃል መቃኘት

 

“እርሱ ኋጢአትን ሊያስወግድ እንደተገለጠ ታውቃላችሁ፤ በእርሱም ኋጢአት የለም። በእርሱ የሚኖር ኋጢአትን  አያደርግም፤ ኋጢአትን  የሚያደርግ ግን እርሱን አላየውም ወይም  አላወቀውም። ልጆች ሆይ፤ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ እርሱ ጻድቅ እንደሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ጻድቅ ነው። ኋጢአትን የሚያደርግ ከዲያቢሎስ ነው። ምክንያቱም ዲያቢሎስ ከመጀመርያው አንስቶ ኋጢአትን የሚያደርግ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ የተገለጠውም የዲያቢሎስን ስራ ሊያፈርስ ነው። ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኋጢአትን አያደርግም፤ የእርሱ ዘር በውስጡ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔር የተወለደ ኋጢአትን ሊያደርግ አይችልም። የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያቢሎስ ልጆች ተለይተው የሚታወቁት በዚህ ነው፤ ጽድቅን የማያደርግ፣ ወንድሙንም የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።”  1 ዮሐንስ 3 ፡ 5—10

የነዚህን አምስት ቁጥሮች በአጥጋቢ መልኩ ለመረዳት በጠቅላላ የዮሐንስ መልዕክትን ማወቅ ግድ ስለሚል፣ የዮሐንስን መልዕክት በአጭሩ እንከልሰውና፣ በዚህ ዘመን ከዚህ መልዕክት ምን እንማራለን የሚለውን አይተን እንጨርሳለን።

ሐዋርያው ዮሐንስ በጥንቷ ኤፌሶን ተቀምጦ ሳለ ሐዋርያዊ ሃላፊነት ተቀብሎባቸው ለነበሩ በአጎራባች ከተሞች ላሉ በርከት ያሉ የቤት ለቤት ቤተክርስቲያኖችን የተጻፈ ተጓዥ  መልዕክት ነው ለዚህ ነው በአንደኛ መልዕክቱ ላይ ለማን እንደተጻፈ ያልተገለጠበት ምክንያት።


በመልዕክቶቹ ላይ እንደምንረዳው የተጻፈላቸው አማኞች ለሆኑ አይሁዶች የነበረ ሲሆን፣ የተጻፈበት ዋና ምክንያትም በዛ ወቅት በነበረው የሃሰት ትምህርት እንዳይናወጡ ነው።

ይህ የሃሰት ትምህርትም የተነሳው በተወሰኑ ቤተክርስቲያናቱን ጥለው በወጡ ስብስቦች ሲሆን፣ እነርሱም

·    የክርስቶስን መሲህነት የማይቀበሉ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የሚክዱና ይህን የሃሰት ትምህርትንም አንቀበልም ብለው በቤተክርስታያናቸው የቀሩትን ሰዎች እንደ አላዋቂዎችና ለእውነት ጠላቶች አድርገው ይቆጥሩ ስለነበር ነው።

እነዚህ የሃሰት አስተማሪዎች ወይም ሐዋርያው ዮሐንስ “አሳቾች”የሚላቸው፣ የሚያስተምሩት ከኋጢአትና ከዓለም መለየት ድነትን ለሚያስገኝ እምነት አስፈላጊ አይደሉም በማለት  ስለነበር ነው።

ይህንንም ዓይነት ትምህርት በማስተማር ከሥነ—ምግባር ውጭ የሆነ ኋጢአትን የማይጠየፍ የኑሮ ልምምድ ይከተሉ የነበሩ ሲሆን፣

ለዚህ ነው ዮሐንስ

“በእርሱ የሚኖር ኋጢአትን  አያደርግም፤ ኋጢአትን  የሚያደርግ ግን እርሱን አላየውም ወይም  አላወቀውም። ልጆች ሆይ፤ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ እርሱ ጻድቅ እንደሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ጻድቅ ነው። ኋጢአትን የሚያደርግ ከዲያቢሎስ ነው።” ብሎ የፃፈው።

ወደዚህ ዓይነት አኗኗር ያስገባቸው ትልቁ ስህተትና የትምህርታቸው ዋና መሰረት የሆነው፣ መንፈስ በጠቅላላው ጥሩ ሲሆን፣ ቁስ ወይም ስጋ ደግሞ ሰይጣናዊ ነው የሚለው Gnosticism የተባለው አስየምህሯቸው ነው።

የዚህ አስተምህሮ ከዋናዎቹ መሰረታዊ ስህተቶቹ ጥቂቶቹ፡

1.      ቁስ ስለሆነ ሰዎች ስጋ ሳይሆኑ መንፈስ ናቸው፣ ምክንያቱም ቁስ ከሰይጣን ነው፣ መንፈስ ብቻ ነው ከእ/ር የሆነው

2.     ክርስቶስ በስጋ አልተገለጠም ወይም ሥጋ የሚመስል ነገር ነበር ያለው እንጂ ስጋ ለብሶ አልተመላለሰም

3.     የክርስቶስ አምላካዊ ባህርይ በምድር የተገለጠው ክርስቶስ ሲጠመቅ እንጂ ሰውም አምላክም ሆኖ አልመጣም፣ ደግሞም ሲጠመቅ የተገለጠው አምላካዊ ባህርይ ሲሞት ተለይቶታል።

4.     ስጋ ከሰይጣን ስለሆነና ቁስ ብቻ ስለሆነ በስጋችን የእ/ርን ሕግ ብንጥስም ምንም አይነት ችግር አያመጣም፣ ምክንያቱም መንፈሳችን ብቻ ነው ደህንነት ያገኘው የሚሉት ናቸው

ዚህ ዮሐንስ በዚያ ዘመን (1 ና 2ኛ ክ/ዘመን) ላይ ለነበሩ እውነተኛውን ወንጌል የተቀበሉት ሰዎች በነዚህ የሃሰት ትምህርቶች እንዳይናወጡ ነው ይህን መልዕክት የሚጽፍላቸው።

ይህ መልዕክት ከደብዳቤነቱ ይልቅ ግጥማዊ ቃና ያለው ለየት ባለ የአፃፃፍ ዘይቤ “Amplification” የተባለውን ዓይነት በስዕላዊ መግለጫና ዋናውን የወንጌልን ሃሳብ

·         ይወትን፣ እውነትንና ፍቅርን

በተደጋጋሚ በተለያዩ አንግሎች በማንሳትና፤

·         ውነትን ከውሸት፣

·         ፍቅርን ከጥላቻ፣

·         ብርሃንን ከጨለማ፣

·         የእ/ር ልጅነትን ከዲያቢሎስ ልጅነት

ንጽጽር እያስቀመጠ ከዚህ በፊት ያስተማራቸውን የወንጌል ትምህርት በድጋሚ የሚያብራራበት ክፍል ነው።

ቅድም ያነበብነው ክፍል ላይም

“የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያቢሎስ ልጆች ተለይተው የሚታወቁት በዚህ ነው፤ ጽድቅን የማያደርግ፣ ወንድሙንም የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።” ይላል።

ጠቅልል አድርገን ስናየው ይህ የዮሐንስ መልዕክት ጠንካራ መግቢያ Introduction 1:1-4 ያለው ሲሆን

“ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመርያ የነበረውን፣የሰማነውን፣ በዓይኖቻችን ያየነውንና እጆቻችን የዳሰሱትን እንናገራለን።” ብሎ በጠንካራ መግቢያ ይጀምራል

ዩሐንስ ምን እያላቸው ነው፣ ከክርስቶስ ከራሱ የተማርነውን ፣ ክርስቶስን በስማ በለው አይደለም የምናውቀው፣ ሕያው ምስክሮች ነን።

በመደምደምያው Conclusion ላይ ደግሞ 5፡18—21 እርግጠኝነት በተላበሰ አባባል ተመሳሳይ ነገር ይናገራ።

“የእግዚአብሔር ልጅ እንደመጣ፣ እውነተኛ የሆነውን እርሱን እርሱን እንድናውቅ ማስተዋልን እንደሰጠን እናውቃለን፤ እኛም እውነተኛው በሆነው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አለን።  እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።”

በመግቢያውና በመደምደምያው መሃከል ደግሞ ለሁለት ከፍሎ ሰፋ ያለ ማብራርያ ይሰጠናል።

በመጀመርያው ክፍል 1፡5 — 3፡10 ስለ ብርሃን የሚገልጽበት ሲሆን

ሁለተኛው ክፍል 3፡11—5፡17  ደግሞ ስለ ፍቅር የሚገልጽበት ነው።

በሁለቱም ክፍሎች መግቢያ

1፡5 ከእርሱ የሰማነውን ለእናንተም የምንነግራችሁ መልዕክት 

3፡11 ከመጀመርያ የሰማችኋት . . . . . . ይህች ናት this is the message

ባጭሩ ዮሐንስ በመጀመርያው ክፍል ላይ በብርሃን መመላለስ ማለት ከእ/ር ጋር ህብረት ማድረግ ማለት ነው ይላል። ህብረት የሚለው ቃል በተለይ እዚህ ጋር ትርጉሙ ጥምረት፣ ተካፋይ መሆን፣ ተሳታፊ መሆን ማለት ነው። ከእ/ር ጋር ያጣመረን፣ ተካፋዮች የሆነው ደግሞ በልጁ በክርስቶስ በኩል ነው የለናል።

ከእ/ር ጋር ህብረት አለን ስንል ደግሞ በብርሃን እንመላለለን ማለት ነው። በብርሃን መመላለስ ማለት ደግሞ ትዕዛዙን እንጠብቃለን ማለት ነው። ይህ ማለት እ/ርን በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችን፣ በፍጹም ሃሳባችን መውደድ ማለት ሲሆን፣ ነገር ግን ትዕዛዛቱን ሁሉ መጠበቅ ከባድ ቢሆንም ነገር ግን ብትወድቁ ከኋጥያት የሚያነጻችሁ የክርቶስ ደም አለ ብሎ      1፡5—10 ያገልጽላቸዋል።

በብርሃን መመላለስ ደግሞ ማለት እርስ በእርስ ህብረት መፍጠርም ጭምር ነው ብሎም ይገልጸዋል።

ደግሞም በብርሃን ከተመላለሳችሁ በዚህ አለም ላይ ድል ትቀዳጃላችሁ በዚህም ኋጥያትን እንዳትሰሩ ትጠበቃላችሁ የሚልም መልዕክ ያስተላልፍላችዋል።

በሁለተኛውም ክፍል 3፡11 — 5 ፡17

እ/ር ፍቅር ነው እናም የእ/ር የሆኑት እርስ በእርስ ይዋደዳሉ፣ ስለዚህ ጥላቻ በእናንተ ዘንድ አይኑር ይላቸዋል። ይህንንም የተማርነው ከአንዱ ከእ/ር ልጅ ከክርስቶስ ነው፣ እርሱም ስለእኛ ነፍሱን አሳልፎ እስኪሰጠን ድረስ አለም ወዷልና። ስለዚህ ክርስቶስ ያስተማረን ባልንጀራህን ውደድ የሚል ነው። ለዚህም ነው ባነበብነው ክፍል ላይም “ወንድሙንም የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።”

ስለዚህ መናፍስትን መርምሩ ምክንያቱም ብዙ ሃሰተኛ ነቢያት ወደ ዓለም መጥተዋልና። እነዚህንም ሃሰታኛ ነብያት የምትለዩዋቸው በትምህርታቸው ነው። ብሎ በም 4 ላይ ይናገራል።

እነርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ አልተገለጠም ብለው የሚያስተምሩና የዓለምን ስርዓት የሚከተሉ ናችው፣ የሚናገሩትም እንደ ዓለም ነው፣ ዓለምም ይሰማቸዋል። ስለዚህ ዓለም እናንተን ባይሰማችሁ አይግረማችሁ እናንተ ከዓለም ስላይደላችሁ ነው።

በ2፡16 —17 “በዓለም ያለው ሁሉ፥ የስጋ ምኞት፣ ያዓይን አምሮት የኑሮ ትምክህት ከዓለም የሚመጣ እንጂ ከእ/ር አይደለም። ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእ/ርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።”  ይላል።

ሐዋርያው ደጋግሞ የምጽፍላችሁ የመጀመርያውን የቆየውን ትዕዛዝ እንጂ ሌላ አዲስ ትዕዛዝ አይደለም እያለ ይነግራቸዋል። ይህም ማለት በመጀመርያ ከክርስቶስ የተማርነውንና ያየነውን የነገርናችሁን አሁንም አጥብቃችሁ ያዙ እያላቸው ነው።

ይህች በመጀመርያ ከክርስቶስ የሰሟት ትዕዛዝ በማቴዎስ ወንጌል 22፡35 — 40 ላይ ያለው

“ከእነርሱም አንድ የኦሪት ሕግ አዋቂ ሊፈትነው ፈልጎ እንዲህ አለው።

መምህር ሆይ ከህግ ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ትዕዛዝ ነው?

እርሱም እንዲህ አለው፤ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህ በፍጹም ሃሳብህ ውደድ”፣ ይህ የመጀመርያው ከሁሉ የሚበልጠው ትዕዛዝ ነው፤

ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል ይህም “ጎረቤትህን እንደራስህ  ውደድ” የሚለው ነው፤ ሕግና ነቢያት በሙሉ በእነዚህ ሁለት ትዕዛዛት ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው።”

አሁንም ዮሃንስ መልሶ የሚያስተምራቸው ይህንኑ ትዕዛዝ ነው።

እኛም በዚህ ዘመን ሃሰተኞች ነብያትን የምንለየው በዚሁ መንገድ ነው። የቀደመውን ትዕዛዝ በመፈጸም። ያንንም የምናገኘው በእ/ር ቃል ውስጥ ነው።

በአሜሪካ ውስጥ ሃሰተኛ የዶላር ኖቶችን የሚይዙ ሰዎች የሚሰለጥኝት እንዴት እንደሆነ ታውቃላችሁ?

ሃሰተኛ የዶላር ኖቶችን ሰብስቦ በማጥናት አይደለን፣ ይልቁንም እውነተኛውን የዶላር ኖት በደንብ በማጥናት እንጂ። እውነተኛውን በደንብ ጠንውቀው ሰለሚያውቁት ሃሰተኛውን በቀላሉ ይለዩታል።

እኛም የእ/ር ቃል ጠንቅቀን ካወቅን ሃሰተኛ ትምህርቶችን ለይተን ማወቅ እንችላለን። ዳዊት ከዚህ ነው “ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው የሚለው”

የመጀመርያው ሃሰተኛ አስተማሪዎችን የምንለይበት መንገድ ትምህርታቸው ክርስቶስ ማዕከል ያላደረገ እንደሆነ ነው። ለዚህ ነው 4፡3 ኢየሱስን የማይቀበል መንፈስ ግን ከእ/ር አይደለም።

ብዙ ጊዜ ሃሰተኛ አስተማሪዎች ስለራሳቸው ነው የሚያወሩት፣ እነርሱ እንዴት ልዩ እንደሆኑና በእ/ር እንደተመረጡ። እ/ር እነርሱን ብቻ እንደሚናገራቸው፣ እነርሱ ብቻ እንዲታዮ ነው የሚፈልጉት።

ሌላው ዓለማዊ ነገር ላይ፣ የሚያልፍ ነገር ላይ ትኩረት ይሰጣሉ፣ ሃብት ጤና ምቾት። እ/ር ልጁን የላከው እኛ በሚያልፈው ዓለም ላይ ተመችቶን እንድንኖር ሳይሆን ዘላለምን በመንግሰት ሰማያት ከአባታችን ጋር እንድንኖር ነው። ትንቢታቸውም ትምህርታቸውም ትበለጽጊያለሽ ይሳካልሻል ብቻ ነው።

ጽድቅን ብዙ ጊዜ አይሰብኩም፣ ከነርሱ ትምህርት ጋር የማይስማማውንም ልክ እውነትን እንደሳት እንዳልገባው ኋላ እንደቀረ አድርገው ያንቋሽሻሉ።

በመጨረሻም ዮሐንስ የመጀመርያውን መልዕክቱን የደመደመው

“ልጆች ሆይ ራሳችሁን ከጣዖቶች ጠብቁ” ነው ያለው።

ምን ማለቱ ነው ራሳችሁን ከማንኛውም ታላቁን እ/ርን ከራሱ ዕውቀት ብቻ ተነስቶ የእ/ርን ማንነት ለማናገር ከሚያስደፍር ሙከራ አርቁ ማለቱ ነው።

በዚህ ዘመን ያለው ጣዖት ራስን አግዝፎ የማየት፣ የዕውቀት ሁሉ ምንጭ ማድረግ፣ ከዚህም የተነሳ ልክ ዓለም ውስጥ እንዳሉ ሰዎች ሁሉ ለመታወቅ መጣር ነው።

ክርስቶስን ማወቅ ማለት እ/ርን ማወቅና ሌሎችን እንደራስ ማየትና ለሌሎች መኖር ማለት ብቻና ብቻ እንደሆነ ተገንዘቡ።

የሚመጣው ዓመት የሁሉ መሰረት በሆነው በእ/ር ቃል የመቃኘት ዓመት እንዲሆንልን ምኞቴና ፀሎቴ ነው።

No comments:

Post a Comment