Thursday, August 17, 2017

በእርግጥ መጽሐፉ ምን ይላል?

ለዚህ ጽሑፍ ምክንያት የሆነኝን ጉዳይ አንስቼ ልጀምር። በቅርቡ ከአንድ የቅርብ ወዳጄ ጋር ሆነን ስለ ብልጽግና ወንጌል እንዲሁም አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ስለተስፋፋው ”የነብያት“ እንቅስቃሴ አንስተን ስንጫወት የሊሊ መዝሙር እንደ አንድ ጥሩ መልስ መቅረቡ ስላስገረመኝ እስኪ ምንአልባት ይህ ጉዳይ ለብዙዎች የመነጋገርያ ጉዳይ ስለሆነ በሰፊው ልምጣበት ብዬ ይህን ጽሁፈ ጫር ጫር እንዳደርግ ምክንያት ሆነኝ።

ከአንኳሩ ጉዳይ ልጀምርና ፤ የትኛውንም የክርስትና አስተምህሮ መመዘን ያለብን በምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ በአጭሩና በማያሻማ መልኩ ስንመልሰው በመጽሓፍ ቅዱስ ብለን ነው። ለዚህም ነው ወንድሜ በመዝሙር መልስ ለመስጠት ሲታገል ሳየው ያሳዘነኝ። መጽሓፉ በእርግጥ ምን ይላል አትታመሙም፣ አትደኽዪም፣ ችግር ወይም መከራ አያገኛችሁም፣ አተጎሳቆሉም፣ አትሞቱም ይላል ሃብት በምድር አከማቹ፣ ጤነኞች ካልሆናችሁ ስለመዳናችሁ ተጠራጠሩ፣ ችግር ወይም መከራ ከመጣባችሁ የኔ ደቀ መዛሙርት ላለመሆናችሁ ምልክት ይሁን፣ ደግሞም የምን መጎሳቆል እንደዛማ ከሆናችሁ የኔ አይደላችሁም ይላል

በእርግጥ መጽሓፉ ምን ይላል እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንትም እኔን ምሰሉ ሲል ጳውሎስ ፤ ክርስቶስ በእርግጥ በምድር ሳለ በምድራዊ ቁሳቁስ ልቡ ተይዞ በዘመኑ አንደኛ የተባለ መኖርያ ቤት ውስጥ ይኖር ነበር፣ ሲጓጓዝም ምርጥ ምርጥ ጀልባዎች ላይ ይሳፈር ነበር እንዳውም አብዛኛዎቹ ጀልባዎች የግሎቹ ነበሩ፣ ደቀ መዛሙርቱም ዋናው ስራቸው የእርሱ ክቡር ዘበኛ መሆን ነበር፣ ከህዝብ በተሰበሰበ ገንዘብ የተሰራ በጊዜው አለ የተባለ መድረክ ላይ ነበር ትምህርት የሚያስተምረው ማለቱ ይሆን

በእርግጥ መጽሓፉ ምን ይላል ኧረ እንዳውም እኔ ስሄድ በእኔ ስም ህዝብ ሰብስባችሁ ሰዎችን ሰብስባችሁ ደስ ደስ የሚሉ ቃላቶች የሞሉባቸውን ትምህርቶች እያስተማራችሁ፣ አጋንንት በስሜ እያስወጣችሁ፣ ሰዉን ስጋዊ ፈውስ ብቻ እየፈወሳችሁ፣ ከቻላችሁ በዶላር ካልቻላችሁም ደግሞ በብር ገንዘብ እየሰበሰባችሁ ጠብቁኝ፣ ስመጣ ሂሳብ አወራርዳለሁ ይላልበእርግጥ መጽሓፉ ይህን ይላል
በእርግጥ መጽሓፉ ምን ይላልከእናንተ ላነሰው ለዛ ወንደማችሁ ወይም እህታችሁ ካልቻላችሁ በፌስ ቡክ ከቻላችሁ በራሳችሁ ቴሌቪዥን ምን ያህል ከሌላው የተሻለ ዕውቀትና የኑሮ ደረጃ እንዳላችሁ ጉራችሁን እየዘራችሁ ጠብቁኝ እንጂ የምን የተራበ ማብላት፣ የተጠማ ማጠጣት፣ የታረዘ ማልበስ ነው ለዛውም ማንም ሳያያችሁ፣ ሳይጨበጨብላችሁ ይል ይሆን  

በእርግጥ መጽሓፉ ምን ይላልእንኳን ካላችሁ ላይ ልትሰጡ ቀርቶ ከቻላችሁ በተዓምር ብር አባዝታችሁ ካልሆነም በእኔ ስም ተከልላችሁ ምንም የማያውቁትን የዋሆች አሳምናችሁ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በምድር አከማችታችሁ የሚያማምሩ ልብሶችንና  መኪናዎችን በየቀኑ እያቀያየራችሁ በሃብት ሰክራችሁ ስስትን ጠግባችሁ እኔን ከማያውቁኝና ከፈሪሳውያን በልጣችሁ ካልጠበቃችሁኝማ እኔም በተራዬ አላውቃችሁም እላችኋለሁ ይል ይሆን  

በእርግጥ መጽሓፉ ምን ይላልእስቲ እኔ ከምነግራችሁ እራሱ መጽሓፉን ምን እንደሚል አብረን አናነበውም።
ዮሐንስ 16: 33 “በእኔ ሰላም እንዲኖራችሁ፣ ይህን ነግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።
ማቴዎስ 10: 38-39 መስቀሉን ተሸክሞ የማይከተለኝ የእኔ ሊሆን አይገባውም። ሕይወቱን ሊያድን የሚፈልግ ያጠፋታል፤ ሕይወቱን ስለ እኔ አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያገኛታል።
ሮሜ 8: 35 ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? ችግር ነው ወይስ ሥቃይ፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ረሀብ፣ ወይስ ዕራቍትነት፣ ወይስ አደጋ ወይስ ሰይፍ?
1 ጴጥሮስ 4: 1 እንግዲህ ክርስቶስ በሥጋው መከራን ስለ ተቀበለ እናንተም በዚሁ ዐላማ ታጥቃችሁ ተነሡ፤ ምክንያቱም በሥጋው መከራን የሚቀበል ሰው ኀጢአትን ትቶአል።
1 ጴጥሮስ 3 : 13,14 መልካም ነገር ለማድረግ ብትቀኑ የሚጐዳችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራ ቢደርስባችሁ ብፁዓን ናችሁ፤ “ዛቻቸውን አትፍሩ፤ አትታወኩም።” 
ገላትያ 6: 2-3አንዱ የሌላውን ከባድ ሸክም ይሸከም፤ በዚህም ሁኔታ የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ። አንድ ሰው ምንም ሳይሆን ትልቅ የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላል። 
ፊልጵስዩስ 1: 29-30 በክርስቶስ እንድታምኑ ብቻ ሳይሆን ስለ እርሱ መከራ እንድትቀበሉም ይህ ጸጋ ተሰጥቶአችኋልና፤ ቀድሞ እንዳያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ በምትሰሙት በዚያው ዐይነት ተጋድሎ እናንተም እያለፋችሁ ነውና።
1 ጴጥሮስ 2: 21የተጠራችሁትም ለዚሁ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው።
ሮሜ8: 18የአሁኑ ዘመን ሥቃያችን ወደ ፊት ሊገለጥ ካለው ለእኛ ከተጠበቀልን ክብር ጋር ሲነጻጸር ምንም እንዳይደለ እቈጥራለሁ።
ማቴዎስ 7: 21 - 23 “በሰማይ ያለውን ያባቴን ፈቃድ ሳይፈጽም ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ አይገባም። በዚያ ቀን ብዙዎች፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህ አጋንንት አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ታምራት አላደረግንምን?’ ይሉኛል። በዚያ ጊዜ፣ ‘ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንት ክፉዎች፤ ከእኔ ራቁ’ ብዬ በግልጽ እነግራቸዋለሁ።

በመጨረሻብ ማቴዎስ 25 ላይ ከቁጥር 23 ጀምሮ እስከ 46 ያለውን እራሳችሁ እንድታነቡ እየጋበዝኩ፡ እንደ ማጠቃለያ በዘመናችን ለተከሰቱት አዲስ ለሚመስሉ ነገር ግን ከነጳውሎስ ዘመን ጀምሮ ለነበሩ እንግዳ መሰል አስተምህሮዎች እጃችንን ከመስጠታችን በፊት በእርግጥ መጽሓፉ ምን ይላል ብለን መጠየቅ እንጂ እነ እከሌ እኮ እንዲህ ብለው ዘምረዋል እንዲህ ብለው አስተምረዋል በማለት ለጆሮዋችን በሚመች መልኩ የመጣውን ትምህርት ይሁን ትንቢት አስተናጋጆች እንዳንሆን እንጠንቀቅ። ይልቁን የዘመኑ ትምህርትና ትንቢት ምነው የተራራውን ስብከት የሚሰብክ እና የሚተነብይ ያልሆነው ምነው ዝቅ በሉ፣ ታገሱ፣ በጽድቅ ኑሩ፣ ያላችሁን ስጡ፣ የተገፉትን ፈልጉ፣ልታይ ልታይ ከማለት ተቆጠቡ የሚል ትምህርት እና ትንቢት የሞኝነት ያህል የተቆጠረው እንዳያሰናክሏችሁ ከዚህ ዓለም ተግዳሮቶች ተጠበቁ ሳይሆን በዓለም እንደ ድል አድራጊነት የሚያስቆጥሩት ቁሳቁስ እና ገንዘብ ታገኛላችሁ ይሆንላችኋል ይሳኩላችኋል ላይ ብቻ ተነጠለጠሉ ይህን መጠየቅ በዘማናዊ ክርስትና ለተጠመቁት እንደ ሞኝነት ነውም አይደል


በእርግጥ መጽሓፉ ምን ይላልአትታመሙም፣ አትደኽዪም፣ ችግር ወይም መከራ አያገኛችሁም፣ አተጎሳቆሉም፣ አትሞቱም ይላል ሃብት በምድር አከማቹ፣ ጤነኞች ካልሆናችሁ ስለመዳናችሁ ተጠራጠሩ፣ ችግር ወይም መከራ ከመጣባችሁ የኔ ደቀ መዛሙርት ላለመሆናችሁ ምልክት ይሁን፣ ደግሞም የምን መጎሳቆል እንደዛማ ከሆናችሁ የኔ አይደላችሁም ይላል

እንደዛማ ከሆነ ብልጽግና ወንጌልን ብልጥ - ግና ብለን ብንጠራው ይሻል ይሆን

No comments:

Post a Comment