. . . ሥልጣን ከሰማያት
እንደ ሆነ ካወቅህ . . . ትንቢት ዳንኤል 4፡26
ዳንኤል የንጉስ አማካሪ የነበረ በዘመኑ ከነበሩት አዋቂ
ተብዬዎች በጥበብና በማስተዋል አስር እጅ የበለጠ ነበር። ትንቢት ዳንኤል 4 ላይ ለሚያማክረው ንጉስ ናቡከደናጾርም ህልም ሲፈታለት
በአጽንዖት የሚነግረው አንድ ጉዳይ ነበር፣ ይህም ስልጣን “ከሰማይ እንደሆን እድዲያውቅ ነው”። ከዛም በመቀጠል “የደህንነትህ ዘመንህ
ወይም በንግስና/በስልጣን የመቆየትህ ዘመን ይረዝም ዘንድ ኃጢአትህን በጽድቅ ፥ በደልህንም ለድሆች በመመጽወት አስቀር” ይለዋል።
በእኔ የግል አስተያየት በኢትዮጵይ ውስጥ የሰለጠነ
የመንግስት አስዳደር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ የዳንኤልን ምክር የሰማም ሆን ያነበበ የአገር መሪ ኢትዮጵያ ነበራት
ብዬ አላስብም። ሃይማኖትን ከስልጣን ጋር ቀላቅለው ያስተዳደሯት አፄዎችም ስዩመ እግዚአብሄር ብለው ተጠያቂነትን ከራሳቸው ለማውረድ
እናም እድሜ ልክ ለመንገስ ተጠቀሙበት እንጂ ፣ በትክክል ትርጉሙ ገብቷቸው አልኖሩበትም። በዚህም ምክንያት አሁን ያለችውን ኢትዮጵያን
አስረክበውናል። እግዚአብሄርን ፈርተው ፣ ሥልጣን ከሰማያት እንደ ሆነ አውቀው ቢመሩን ኖሮ ምንኛ በታደልን ነበር።
ብዙ ሰዎች ኢትዮጵያ ፈርጀ ብዙ ችግሮች ያሉባት ፣
እነዚህንም ችግሮች ለመፍታት አዳጋች እንደሆነ ፥ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖምያዊ እና ማህበራዊ ትንታኔዎችን በመስጠት ጭብጥ ያላቸው መረጃዎችን
በማቅረብ ትንተናዎችን ሲያቀርቡ ይደመጣል። በእርግጥም ኢትዮጵያ ፈርጀ ብዙ ችግሮች ያሉባት ሃገር ለመሆንዋ የምንከራከርበት ጉዳይ
አይደለም። ነገር ግን እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የምንጠቀመው ዘዴ ነው እንጂ ችግሮችን ለመፍታት አዳጋች የሚያደርገው ፣ በእኔ
እይታ ለእነዚህ ፈርጀ ብዙ ችግሮች መፍትሔ ማምጣት ከባድ ነው ብዬ አላምንም።
ዋናው የእኔ መልዕክት ለአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትራችን በስልጣን የመቆየትዎ ዘመን
የተሳካና የረዘመ ይሆን ዘንድ እርስዎም ሆነ ካቢኔዎ ውስጥ የሚመርጧቸው ሰዎች እስከዛሬ የተሰራውን ኃጢአት በጽድቅ፥ እስከዛሬ የተሰራውን
በደልንም ለድሆች በመቆርቆርና ፍትህን በማስፈን እንዲቀይሩ፤ በዚህም ውስጥ እግዚአብሄርን ፈርተው ፣ ሥልጣን ከሰማያት እንደ ሆነ
አውቀው ቢመሩን ፣ ከባድ የተባለው ችግር በሰው ዓይን እንጂ በእግዚአብሄር ዓይን እጅግ ቀላል እንደሆነና፣ መፍትሔውንም እራሱ የሚፈሩት
እግዚአብሄር በእጅዎ ይሰጥዎታ የሚል ነው። የጥበብ መጀመርያ እግዚአብሄርን መፍራት ነው ፤ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው። ምሳሌ
9፥10
ወደ ተጨባጭ ሁኔታዎች ስንመጣ ፣ በእኔ የግል አስተያየት
የአገራችንን ችግሮች በሦስት እከፍላቸዋለሁ።
1 ወጥ የሆነ መዋቅራዊ የሆነ አሰራር ማጣት በእንግሊዝኛው system የምንለው በተቀናጀ
መልኩ አለመኖሩ፣
2 የትምህርት መዋቅራችን ወይም curriculum ገና ሀ ተብሎ የሰለጠነ የትምህርት አሰጣጥ ሲመጣ ጀምሮ የተበላሸ
መሆኑ እና
3 አገራችን ኢትዮጵያ በዘመኗ በሙሉ ይሄ ነው የተባለ የባህል አብዮት አለማካሄድዋ ናቸው።
እነዚህ ሶስቱ በጥቅሉ ተጠያቂነት
የጎደለው የመንግስት የስራ አስፈፃሚ እንዲፈጠር ፣ ለአገር ችግር መፍትሔ ሰጪ የፈጠራ ሰው innovative የሆነ የተማረ ሃይል
እንዳይኖር እና የህብረተሰቡ የአስተሳሰብ አድማስ እንዳይሰፋ ያደረጉ ችግሮች ናቸው።እንዚህን ችግሮች ለመፍታትም መጠቅም ያሉብን
መንገዶች እንደተለመደው ከላይ ወደ ታች ሳይሆን፤ ከታች ወደ ላይ መሆን ይገባዋል። ይህ ምን ማለት ነው፣ በተለምዶ የተማሩና ችግር
ለመፍታት አቅም ያላቸውን ሰዎች critical thinkers and problem solvers በሚኒስትር ደረጃ አስቅምጦ መፍትሔ
ማፈላለግ እሩቅ የማያስኬድና ፈጣን መፍትሔም ለማምጣት የማይበጅ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለማንሳት ወደድኩ። መዋቅራዊ የሆነ አሰራርንም
ቢሆን ከታች ወደ ላይ ማለትም ከቀበሌ ወይም ከወረዳ ወደ አገር አቀፍ ማሳደግ፣ የተማሩና ችግር ለመፍታት አቅም ያላቸውን ሰዎች
የቀበሌ እና የወረዳ መሪዎች በማድረግ የተማረውን እና ቀና የሆነውን የሰው ሃይል ለድሆችና ላልተማሩት ዕውቀቱን የሚያውልበትን መንገድ
ማመቻቸት ግድ ይለናል። ትምህርት ቤቶችንና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ደግሞ ለውጣዊ progressive የሆነን ትምህርት በሂደት
እዲያስተምሩና፣ በዘላቂነት ደግሞ ኢትጵያዊ የሆነ አዲስ የትምህርት መርሓ ግብር curriculum በመንደፍ አሮጌውን መቀየር ወሳኝ
ነው። በአጭር ጊዜም መፍትሔያዊ የሆኑ እንቅስሴዎች እንዲዳብሩን የፈጠራ ማዕከሎችን innovation centers በከፍተኛ ትምህርት
ተቋማት ውስጥ እንዲቋቋሙ ማድረግና፣ መንግስት ከግል ተቋማት፣ ከከፍተኛ ትምህርትና አሁን በስራ ላይ ካሉ የምርምር ተቋማት ጋር
በመሆን ፈጣን ሃገራዊ ችግር ፈቺ እና ፈር ቀያሽ ምርምሮችንና ጥናቶችን የሚያካሂድ ጠንካራ ተቋምን በአጭር ጊዜ ውስጥ ቢያቋቁም
መልካም ነው የሚል ሃሳብ አለኝ።
ከሁሉ በላይ ይቅርታ የተሞላው፣ ያለፈውን ትተን ወደፊታችን
ላይ ያሚያተስኩር፣ የግለሰብን መብት የሚያከብር እና ከቡድን አሳቢነት የሚገላግል፤ ፍቅርን ማዕከላዊ ያደረገ ርዕዮተ ዓለም ለምድራችን
ያስፈልጋታል። የህግና የትዕዛዛት ሁሉ ማንጠልጠያ የሆኑትን ሁለቱን ትዕዛዛት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እንዝራ በማለት መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።
መልካም የአገልግሎት ዘመን እንዲሆንልሆ እየተመኝሁ
እግዚአብሄር ፀጋና ጥበብ እንዲያበዛልዎ ፀሎቴ ነው። ስራው የእርስዎ ብቻ ሳይሆን የሁላችን ስለሆነ ሕዝቡንም በቀናነት መሪያችንን
እያገዝን የበኩላችንን ድርሻ እንፈጽም ብዬ አሳስባለሁ።
ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው፤ ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል፤ ይህም፣ ‘ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለው
ነው፤ ሕግና ነቢያት በሙሉ በእነዚህ ሁለት ትእዛዛት ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው።” ማቴዎስ 22፡ 37 — 40
No comments:
Post a Comment