Wednesday, October 11, 2017

የማንቂያ ደወል

ስለዚህ ንቃ፤ ሊሞት የተቃረበውን የቀረውን ነገር አጽና፤ ሥራህ በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትም።እንግዲህ የተቀበልኸውንና የሰማኸውን አስታውስ፤ ታዘዘውም፤ ንስሓም ግባ። ባትነቃ ግን እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ፤ በየትኛው ሰዓት እንደምመጣብህም አታውቅም። ራዕይ 62—3

በዚህ ጦማር ላይ ላጋራ የፈለኩት ጉዳይ በሃሰታኞች ነቢያት ዙርያ በኢትዮጲያ ወንጌላውያን አብይተክርስቲያናት ሕብረት (ኢወአክሕ የተሰጠውን መግለጫና ከዛም ጋር ተያይዞ ስለሚነሱ ሃሳቦች ይሆናል። በመጀመርያ እንደተለመደው አቋሜን ግልጽ በማድረግ ልጀምር።
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ማንንም ቡድን ወይም ግለሰብ ለመንቀፍ ወይም የማንም ትምህርት ላይ ጣት ለመቀሰር አይደለም። እንዲሁም በዚህ ጦማር ላይ የሚወጡ ማንኛውም ጽሑፎች ሃሳብንና አስተሳሰብን የሚሞግቱ ብቻ እንጂ ከግለሰብ፣ ከድርጅት ወይም ከማንኛውም ቡድን ጋር ጠብ የሌላቸው እንዲሁም ያልወገኑ ናቸው።
ሃሳቤን በጥሩ ሁኔታ ለማካፈል ይረዳኝ ዘንድ በፈርጅ እያስቀመጥኩ አብራራለሁ። በመጀመርያ ኢወአክሕ ማን ነው ከሚለው ጀምሬ፣ በሃሰታኞች ነቢያት ዙርያ የተሰጠው መግለጫ ምን ፋይዳ አለው የሚለውን አስከትዬ፣ አሁን ባለው ሁኔታ ውስጥ እንደኔ ያሉ ተራ ዓማኞች ምን ማወቅና ማድረግ አለባቸው የሚለውን እዳስሳለሁ።

1 የኢትዮጲያ ወንጌላውያን አብይተክርስቲያናት ሕብረት (ኢወአክሕማን ነው
            እንደኔ እምነት ምንም ከማለታችን በፊት ኢወአክሕ ማን ነው ማንንስ ይወክላል ብለን መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል። ኢወአክሕ እንቅስቃሴ የተጀመረው በኛ አቆጣጠር በ60ዎቹ ውስጥ ሲሆን፣ በዛን ጊዜ ነበረው መንግስት ሲከተለው ከነበረው የሶሻሊስት ስርዓት ምክንያት ለረጅም ዘመን በህቡዕ የተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ የመንግስት ለውጥ በ80ዎቹ ላይ ሲመጣ ሰኔ 20 ቀን 1983 ዓ ም ከኢትዮጵያ ፍትህ ሚኒስቴር ሕጋዊ ዕውቅናን አግኝቶ ተመሰረተ። በዚያን ጊዜ ዘጠኝ በሚሆኑ ቤተክረስቲያኖች የተመሰረተ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ 29805 በአገር ውስጥ 15 በውጭ ሃገር ያሉ ቤተክርስቲያኖችን እንዲሁም 29 የሚሆኑ እምነት ተኮር ተቋሞችን በአባልነት የያዘ ሕብረት ነው። በጥቅሉም ወደ 13 ሚሊዮን የሚሆኑ አማኞች በዚህ ህብረት ስር ይታቀፋሉ። ለበለጠ መረጃ የህብረቱን ድህረ ገጽ ይመልከቱ http://www.ecfethiopia.org/
            የኢወአክሕ ውክልና የሕብረቱ አባል ለሆኑት ቤተክርስቲያኖችና በስሮቻቸው ላሉ አባላት ነው። ይህም በመሆኑ የተሰጠው መግለጫ የሚወክለው የነዚህኑ አባላት አቋም መሆኑን መገንዘብ ግድ ይላል። መግለጫውን የሰጡት ግለሰብ የኢወአክሕን ወክለው እንጂ እንዳው እሳቸው ብቻ ብድግ ብለው የሰጡት አይደለም። በዚህ ከተግባባን የተሰጠውን መግለጫ ከአቅራቢው ጋር እያገናኝን እሱስ እንዲህና እንዲያ አድርጎ አልነበር ብለንም መሰረት የለቀቀ አታካራ ውስጥ መግባትን ያልበሰል ክርክርና ጠብ ውስጥ ሊጨምር ስለሚችል ከወዲሁ ልናስወግደው ይገባል ብዬ እመክራለሁ። እንደዚህ ስል የአመራር አባሎች የሆኑትን ሰዎች ብቃት አላቸው/የላቸውም፣ ስህተት ሰርተው አያውቁም እያልኩ እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል። እንዲሁም የኢወአክሕ የአሰራር ችግር የለበትም ወይም እስከዛሬ ድረስ ያለ እንከን ሲሰራ የቆየ ተቋም ነው የሚልም አቋም የለኝም። ይልቁንም አሁን ለተፈጠሩት ችግሮች በዋና ተጠያቂነት ውስጥ ከሚዘረዘሩት ውስጥ አንዱ ነው ብዬም አምናለሁ። ነገር ግን ይህ አሁን የምንነጋገርበትን መግለጫ ማውጣቱን ግን እንደ ስህተት ወይም ፈራጅ እንደመሆን አድርጌ አልቆጥረውም። ይልቁንም በዚህ አጋጣሚ ይህ መግለጫ ምን ፋይዳ አለው ብለን በሰከነ መልኩ ብንወያይ መልካም ነው።

            2 በሃሰታኞች ነቢያት ዙርያ ከኢወአክሕ የተሰጠው መግለጫ ምን ፋይዳ አለው
            ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተቀጣጠለ ያልውን የነብያት አገልግሎትን ሙሉ ለሙሉ ለመቃወምና ስህተት ነው በማለት መፈረጅ ፍርደ ገምድል ሊያሰኝ ስለሚችል፣ ይህን ጉዳይ አጽንኦት ሰጥተን መገምገም ያለብን ሲሆን፣ ለምንስ ይህን ያህል ድብልቅልቅ ስሜት እስኪፈጥር ድረስ ቸል ተባለ የሚለውን መመለስ ተገቢ ነው። የዚህን ዝርዝር መልስ በዚህ ጦማር ላይ መመለስ አላሰብኩም፣ ነገር ግን በሌላ ጊዜ በሰፊው ልመጣበት የምችል ሃሳብ ይሆናል።
            በነብያቶቹ በኩል እየታዘብን ያለነው ተጨባጭ እውነታ የቤተክርስቲያኖቻቸው ባለራዕይም መስራችም መሪም እነርሱው እራሳቸው መሆናቸውን ነው። ይህ ነገር ደግሞ እያደር ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ከልካይና ፈቃጅ በሌለበት፣ እንደ እኔ ያለውን ተራውን ምእመን ያሰኛቸውን ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። በዚህም ምክንያት የሆነ ታዛቢና ኧረ ተዉ የሚል ከልካይ አስፈላጊ መሆኑ የሚያከራክረን ጉዳይ አይሆንም። በዚህ አጋጣሚ የኢወአክሕን የአመራር አባላት ብቃት እና የድሮ ስህተት ወደኋላ እያየን መግለጫውን ችላ ከማለት ይልቅ መግለጫው ምን ፋይዳ አለው ብለን ስንጠይቅ አብረን ወደፊትስ እስክ አሁን ያጠፉትን ነገር በምን አይነት መልኩ ያስተካክሉ የሚለውንም እንድናስብ ይረዳናል። ወደ አሁኑ መግለጫ ስንመጣና ስንመዝነው ማየት ያሉብን ነገሮች 1 መግለጫው የወጣበት ምክንያት ልክ ነው ወይ 2 የተነሱት ነጥቦችስ የተቀመጡት ከምን አንጻር ተገምግሞ ነው 3 ለወደፊትስ ከዚህ ልንማር የምንችለው ምንድን ነውየሚሉትን ይሆናል።
            በእኔ እምነት መግለጫው ምክንያታዊ ነው፣ ተጨባጭ ማስረጃም ይዞ ነው የቀረበው። ዋና ጉዳዮም በቅርቡ “ነብይ” እስራኤል ዳንሳ የተነበየው ትንቢት እንደ ተነበየው አልተፈጸመም ነው። ትንቢቱን በዚህ መስመር ይስሙት https://youtu.be/0d91CAeG_I8። ይህን ደግሞ መከራከርያ አድርገን እንዲህ ነው እንዲያ ነው ብለን ወደ የትም እንዳንሄድ የብዙ ሰዎች ጥያቄና የመወያያ አጀንዳ ሆኖ የሰነበተ ጉዳይ ነው። የተነሱትም ነጥቦች ከመጽሓፍ ቅዱስ አንጻር የተዋቀሩ ሲሆን በማስረጃም የተደገፉ ስለሆኑ የሚያከራክረን አይሆንም። እዚህ ላይ አንድ ቅር ያለኝ እና ማወቅ የምፈልገው ነገር የኢወአክሕን “ነብይ” እስራኤል ዳንሳን በግል አግኝቶ ለማናገር እና በትንቢቱ ላይ የእርሱ አቋም እና መልስ ምን እንደሆነ ለማወቅ ያደረገው ጥረት ምን ያህል መሆኑን ነው። ከዚህ በኋላ መጠበቅ ያለብን የ“ነብይ” እስራኤል ዳንሳን መልስ ይሆናል። ከዚህም ዋና መማር ያለብን ነገር እንደ ሃገር ማሰብ መጀመር እንዳለብን ሲሆን፣ ልቅ የሆነ አሰራር ሁሌም ውዥንብር የሚፈጥር መሆኑን ለማወቅ ይህ የመጀመርያችን እንዳልሆነ ሁሉ፣ ያሁኑ ግን የመንቂያ ደወል ይሁንልን እላለሁ። በጥቅማ ጥቅም ተያይዘንም ይሁን ወይም ከዚህ በፊት “ነብይ” እስራኤል ዳንሳን የሚያክል የለም ስላልን፣ ስህተቱን እንዳላየ ለማለፍና ጣታችንን የኢወአክሕ ላይ እየቀሰርን አድበስብሰን ለማለፍ ብንወስን ዞሮ ዞሮ ተጎጂዎቹ እራሳችን ነን። ከዛም በላይ ልጁን ወደተጨማሪ ስህተት መንዳት ይሆናል። “ነብይ” እስራኤል ዳንሳ ለተናገረው ትንቢት ማብራርያ ወይም ስህተቱን የሚያምንበትንና ንስሃ የሚገባበትን ሁኔታ እንዲፈጠር እግዚአብሔር እንዲረዳው ከቻልን በግል እና በህብረት ጸሎት ብናደርግለትና በሌላ በቻልነው ሁሉ ብንረዳው መልካም ነው። “ነብይ” እስራኤል ዳንሳ ብዙ መልካም ነገር የሰራ ነው፣ የታዩ በምስክር የተረጋገጡ ተዓምራቶች ያደረገ ነውና እንዴት ተሳሳትክ ይባላል የሚል እንደምታ ያለው ክርክርም በሌላ በኩል ቢመጣም፣ ምንም እንኳን ለዙህ ዓይነቱ ሁለት ፈርጅ ያለው ምላሽ ቢኖርም፣ ለጊዜው ነገር ለማብረድ አንደኛውን መልስ ትተን፣ ልክ ነው መልካም ምስክርነቶች አሉት ምስክሮችንም ሰምተናል ብንል እና ብንስማማ እንኳን ያን ስላደረገ አይሳሳትም፣ ወይም ስህተትም ቢያደርግም ችግር የለም ብለን ማለፍ አለብን ብዬ አላምንም። ይልቁንም የኢወአክሕ መግለጫ ፋይዳ ያለው የሚሆነው እዚህ ነው። “ነብይ” እስራኤል ዳንሳ ሰው ነው ሊሳሳት ይችላል፣ ሲሳሳት ደግሞ ስህተቱን አስተካክሎ እንዲመለስ ማበረታታትና በፍቅር ማቅናት የሁሉም ህዝበ ክርስቲያን ግዴታ ነው። የኢወአክሕ መግለጫም ይሄንኑ ያካተተ በመሆኑም የፈራጅነት ወይም የድንጋይ ወርዋሪነት ባህሪ እንደሌለው ያሳያል። ታዲይ ይህ ዓይነትን ትእይንት እየተደጋገመ እኛን ከማሰልቸት አልፎ በማያምኑት ዘንድ መላገጫ ሆነን ወንጌልን ለመስበክ የሚያዳግትበት ደረጃ እንደ ደረሰ እየታዘብን ባለንበት ወቅት እንደኔ ያሉ ተራ ዓማኞች ምን ማወቅና ማድረግ አለባቸው የሚለው ጋ እንምጣ።

            3 እንደኔ ያሉ ተራ ዓማኞች በዚህ ወቅት ምን ማወቅና ማድረግ አለባቸው
            1 ይህ አጋጣሚ የማንቂያ ደወል እንዲሆንልን እግዚአብሔር ይርዳን። ዘመኑ የመጨረሻው መሆኑን ልብ ብለን ወደ ቃሉ እንመለስ። በግል ከእግዚአብሔር ጋር ጊዜ በመውሰድ ቃሉን ማንበብ  በግላችን በይበልጥ መጸለይ ከምን ጊዜውም በላይ ማብዛት ግድ የሚልበት ሰዓት ላይ መሆኑን ማወቅና መተግበር። የመጣው ነፋስ ሁሉ የሚያንዥዋዥወን በዓለቱ ላይ ስላልተመሰረትን መሆኑን ማወቅ አለብን። እውነተኛውን በደንብ ካላወቅነው አታላዩን መለየት አንችልም
            2 ተዓምራት ስላየን እና ትንቢት ስለተነገረን ብቻ የምንከተል ሳንሆን ይልቁንም እንደዚህ ዓይነት ልምምዶችን ከማጽደቃችን በፊት ጊዜ ወስደን መመርመርና፣ ስህተት ስናይ በቀናነት ማቅናትን መለማመድ አለብን። ጌታ ሆይ ያሉትን ሁሉና በስሙ የነገዱትን ሁሉ ከጌታ እንደተላኩልን በሞኝነት መቀበል የምናቆምበት ጊዜው አሁን ነው። ማቴዎስ 721 23
            3 ተዓምራትና ድንቆችን የምንከተል ሳንሆን የሚከተሉን እንደሆነ መጽሓፍ ቅዱስ ይነግረናል ማርቆስ 161718 ፣ ስለዚህ እ አጥብቀን ክርስቶስን መከተል ይገባናል። በጎቼ ድምጼን ያውቃሉ ተብሎ እንደተጻፈ የክርስቶስን ድምጽ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መለማመድ ያለብን ዘመን በመሆኑ ተዓምራትና ድንቅን ስናሳድድ ድንገት ስዓቱ እንዳይደርስብን ማስተዋል የሚያስፈልግን ጊዜ መሆኑን ልብ ማለት አለብን።  
            4 ተሳስታችኋል አርሙ ሲባሉ የባጥ የቆጡን ለሚዘባርቁት በተለይም አሁን አሁን የማምለጫ ንግግር ሆኖ የመጣው እኛን ማን አስተማረንና የኛ ጥፋት አይደለም የሚባልን ሰበብ ሰምተን የምንታለል እንዳንሆን፣ ይልቁንም ለጥፋቱ ሃላፊነት የሚወስድ ትውልድ ለማፍራት እራሳች ማዘጋጀት ይጠበቅብናል። ፍሬን እንጂ የፈውስና የያልፍልሃል አይዞህን ፍርፋሪ የሚዘሩትን፣ በግድ አሜን እያስባሉ የነርሱ ተጧሪዎች ሊያደርጉ የሚተጉትን ያለፍርሃት መገሠጽ የምንችልበትን ብቃት ማዳበር አለብን።  
            5 እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች ሲመጡ ሊያስደነግጡ ቢችሉም በማስተዋልና በቀናነት ካየናቸው ከተሳሳትንበት ጎዳና ሊመልሱን፣ የጣልነውን የመደማመጥና የመከባበር ባህላችንን መልሰን ልናመጣበት የሚያስችል አጋጣሚ ሊፈጥሩልን እንደሚችሉ አስበን እንደ መልካም አጋጣሚ ልንጠቀምባቸው ይገባል።
            6 ያጠፉትን በፍቅር መክረን መልሰን ገንዘቦቻችን ማድረግን ባህላችን የምናረግበት አጋጣሚ መሆኑንም ልብ ልንል ያስፈልጋል። ከምንም አይነት ፍላጎት ተነስተው ይስሩት፣ በቸልታ ይሁን ወይ ጥቅማ ጥቅም ዓይናቸውን አሳውሮት፣ ዋናው ጉዳይ ከልባቸው ተጸጽተው ንስሃ ከገቡ መልሰን ገንዘቦቻችን አርገን መቀበል አለብን።
7 አሁንም ደግሜ ደጋግሜ የምናገረው ከሁሉ በላይ ፍጥረት ሁሉ በናፍቆት የሚጠብቀው ከተዓምራቶቻችንና ከዲስኩሮቻችን የበለጠ በየትኛውም ጊዜ ሳንዛነፍ በፍቅር የምንገለጥበትን ጊዜ እንደሆ ልብ ማለት አለብን ብዬ አሳሰባለሁ። ሮሜ 819
ስለዚህ ንቃ፤ ሊሞት የተቃረበውን የቀረውን ነገር አጽና፤ ሥራህ በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትም።እንግዲህ የተቀበልኸውንና የሰማኸውን አስታውስ፤ ታዘዘውም፤ ንስሓም ግባ። ባትነቃ ግን እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ፤ በየትኛው ሰዓት እንደምመጣብህም አታውቅም። ራዕይ 62—3

No comments:

Post a Comment