Wednesday, October 11, 2017

የማንቂያ ደወል

ስለዚህ ንቃ፤ ሊሞት የተቃረበውን የቀረውን ነገር አጽና፤ ሥራህ በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትም።እንግዲህ የተቀበልኸውንና የሰማኸውን አስታውስ፤ ታዘዘውም፤ ንስሓም ግባ። ባትነቃ ግን እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ፤ በየትኛው ሰዓት እንደምመጣብህም አታውቅም። ራዕይ 62—3

በዚህ ጦማር ላይ ላጋራ የፈለኩት ጉዳይ በሃሰታኞች ነቢያት ዙርያ በኢትዮጲያ ወንጌላውያን አብይተክርስቲያናት ሕብረት (ኢወአክሕ የተሰጠውን መግለጫና ከዛም ጋር ተያይዞ ስለሚነሱ ሃሳቦች ይሆናል። በመጀመርያ እንደተለመደው አቋሜን ግልጽ በማድረግ ልጀምር።
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ማንንም ቡድን ወይም ግለሰብ ለመንቀፍ ወይም የማንም ትምህርት ላይ ጣት ለመቀሰር አይደለም። እንዲሁም በዚህ ጦማር ላይ የሚወጡ ማንኛውም ጽሑፎች ሃሳብንና አስተሳሰብን የሚሞግቱ ብቻ እንጂ ከግለሰብ፣ ከድርጅት ወይም ከማንኛውም ቡድን ጋር ጠብ የሌላቸው እንዲሁም ያልወገኑ ናቸው።
ሃሳቤን በጥሩ ሁኔታ ለማካፈል ይረዳኝ ዘንድ በፈርጅ እያስቀመጥኩ አብራራለሁ። በመጀመርያ ኢወአክሕ ማን ነው ከሚለው ጀምሬ፣ በሃሰታኞች ነቢያት ዙርያ የተሰጠው መግለጫ ምን ፋይዳ አለው የሚለውን አስከትዬ፣ አሁን ባለው ሁኔታ ውስጥ እንደኔ ያሉ ተራ ዓማኞች ምን ማወቅና ማድረግ አለባቸው የሚለውን እዳስሳለሁ።

1 የኢትዮጲያ ወንጌላውያን አብይተክርስቲያናት ሕብረት (ኢወአክሕማን ነው
            እንደኔ እምነት ምንም ከማለታችን በፊት ኢወአክሕ ማን ነው ማንንስ ይወክላል ብለን መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል። ኢወአክሕ እንቅስቃሴ የተጀመረው በኛ አቆጣጠር በ60ዎቹ ውስጥ ሲሆን፣ በዛን ጊዜ ነበረው መንግስት ሲከተለው ከነበረው የሶሻሊስት ስርዓት ምክንያት ለረጅም ዘመን በህቡዕ የተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ የመንግስት ለውጥ በ80ዎቹ ላይ ሲመጣ ሰኔ 20 ቀን 1983 ዓ ም ከኢትዮጵያ ፍትህ ሚኒስቴር ሕጋዊ ዕውቅናን አግኝቶ ተመሰረተ። በዚያን ጊዜ ዘጠኝ በሚሆኑ ቤተክረስቲያኖች የተመሰረተ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ 29805 በአገር ውስጥ 15 በውጭ ሃገር ያሉ ቤተክርስቲያኖችን እንዲሁም 29 የሚሆኑ እምነት ተኮር ተቋሞችን በአባልነት የያዘ ሕብረት ነው። በጥቅሉም ወደ 13 ሚሊዮን የሚሆኑ አማኞች በዚህ ህብረት ስር ይታቀፋሉ። ለበለጠ መረጃ የህብረቱን ድህረ ገጽ ይመልከቱ http://www.ecfethiopia.org/
            የኢወአክሕ ውክልና የሕብረቱ አባል ለሆኑት ቤተክርስቲያኖችና በስሮቻቸው ላሉ አባላት ነው። ይህም በመሆኑ የተሰጠው መግለጫ የሚወክለው የነዚህኑ አባላት አቋም መሆኑን መገንዘብ ግድ ይላል። መግለጫውን የሰጡት ግለሰብ የኢወአክሕን ወክለው እንጂ እንዳው እሳቸው ብቻ ብድግ ብለው የሰጡት አይደለም። በዚህ ከተግባባን የተሰጠውን መግለጫ ከአቅራቢው ጋር እያገናኝን እሱስ እንዲህና እንዲያ አድርጎ አልነበር ብለንም መሰረት የለቀቀ አታካራ ውስጥ መግባትን ያልበሰል ክርክርና ጠብ ውስጥ ሊጨምር ስለሚችል ከወዲሁ ልናስወግደው ይገባል ብዬ እመክራለሁ። እንደዚህ ስል የአመራር አባሎች የሆኑትን ሰዎች ብቃት አላቸው/የላቸውም፣ ስህተት ሰርተው አያውቁም እያልኩ እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል። እንዲሁም የኢወአክሕ የአሰራር ችግር የለበትም ወይም እስከዛሬ ድረስ ያለ እንከን ሲሰራ የቆየ ተቋም ነው የሚልም አቋም የለኝም። ይልቁንም አሁን ለተፈጠሩት ችግሮች በዋና ተጠያቂነት ውስጥ ከሚዘረዘሩት ውስጥ አንዱ ነው ብዬም አምናለሁ። ነገር ግን ይህ አሁን የምንነጋገርበትን መግለጫ ማውጣቱን ግን እንደ ስህተት ወይም ፈራጅ እንደመሆን አድርጌ አልቆጥረውም። ይልቁንም በዚህ አጋጣሚ ይህ መግለጫ ምን ፋይዳ አለው ብለን በሰከነ መልኩ ብንወያይ መልካም ነው።

            2 በሃሰታኞች ነቢያት ዙርያ ከኢወአክሕ የተሰጠው መግለጫ ምን ፋይዳ አለው
            ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተቀጣጠለ ያልውን የነብያት አገልግሎትን ሙሉ ለሙሉ ለመቃወምና ስህተት ነው በማለት መፈረጅ ፍርደ ገምድል ሊያሰኝ ስለሚችል፣ ይህን ጉዳይ አጽንኦት ሰጥተን መገምገም ያለብን ሲሆን፣ ለምንስ ይህን ያህል ድብልቅልቅ ስሜት እስኪፈጥር ድረስ ቸል ተባለ የሚለውን መመለስ ተገቢ ነው። የዚህን ዝርዝር መልስ በዚህ ጦማር ላይ መመለስ አላሰብኩም፣ ነገር ግን በሌላ ጊዜ በሰፊው ልመጣበት የምችል ሃሳብ ይሆናል።
            በነብያቶቹ በኩል እየታዘብን ያለነው ተጨባጭ እውነታ የቤተክርስቲያኖቻቸው ባለራዕይም መስራችም መሪም እነርሱው እራሳቸው መሆናቸውን ነው። ይህ ነገር ደግሞ እያደር ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ከልካይና ፈቃጅ በሌለበት፣ እንደ እኔ ያለውን ተራውን ምእመን ያሰኛቸውን ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። በዚህም ምክንያት የሆነ ታዛቢና ኧረ ተዉ የሚል ከልካይ አስፈላጊ መሆኑ የሚያከራክረን ጉዳይ አይሆንም። በዚህ አጋጣሚ የኢወአክሕን የአመራር አባላት ብቃት እና የድሮ ስህተት ወደኋላ እያየን መግለጫውን ችላ ከማለት ይልቅ መግለጫው ምን ፋይዳ አለው ብለን ስንጠይቅ አብረን ወደፊትስ እስክ አሁን ያጠፉትን ነገር በምን አይነት መልኩ ያስተካክሉ የሚለውንም እንድናስብ ይረዳናል። ወደ አሁኑ መግለጫ ስንመጣና ስንመዝነው ማየት ያሉብን ነገሮች 1 መግለጫው የወጣበት ምክንያት ልክ ነው ወይ 2 የተነሱት ነጥቦችስ የተቀመጡት ከምን አንጻር ተገምግሞ ነው 3 ለወደፊትስ ከዚህ ልንማር የምንችለው ምንድን ነውየሚሉትን ይሆናል።
            በእኔ እምነት መግለጫው ምክንያታዊ ነው፣ ተጨባጭ ማስረጃም ይዞ ነው የቀረበው። ዋና ጉዳዮም በቅርቡ “ነብይ” እስራኤል ዳንሳ የተነበየው ትንቢት እንደ ተነበየው አልተፈጸመም ነው። ትንቢቱን በዚህ መስመር ይስሙት https://youtu.be/0d91CAeG_I8። ይህን ደግሞ መከራከርያ አድርገን እንዲህ ነው እንዲያ ነው ብለን ወደ የትም እንዳንሄድ የብዙ ሰዎች ጥያቄና የመወያያ አጀንዳ ሆኖ የሰነበተ ጉዳይ ነው። የተነሱትም ነጥቦች ከመጽሓፍ ቅዱስ አንጻር የተዋቀሩ ሲሆን በማስረጃም የተደገፉ ስለሆኑ የሚያከራክረን አይሆንም። እዚህ ላይ አንድ ቅር ያለኝ እና ማወቅ የምፈልገው ነገር የኢወአክሕን “ነብይ” እስራኤል ዳንሳን በግል አግኝቶ ለማናገር እና በትንቢቱ ላይ የእርሱ አቋም እና መልስ ምን እንደሆነ ለማወቅ ያደረገው ጥረት ምን ያህል መሆኑን ነው። ከዚህ በኋላ መጠበቅ ያለብን የ“ነብይ” እስራኤል ዳንሳን መልስ ይሆናል። ከዚህም ዋና መማር ያለብን ነገር እንደ ሃገር ማሰብ መጀመር እንዳለብን ሲሆን፣ ልቅ የሆነ አሰራር ሁሌም ውዥንብር የሚፈጥር መሆኑን ለማወቅ ይህ የመጀመርያችን እንዳልሆነ ሁሉ፣ ያሁኑ ግን የመንቂያ ደወል ይሁንልን እላለሁ። በጥቅማ ጥቅም ተያይዘንም ይሁን ወይም ከዚህ በፊት “ነብይ” እስራኤል ዳንሳን የሚያክል የለም ስላልን፣ ስህተቱን እንዳላየ ለማለፍና ጣታችንን የኢወአክሕ ላይ እየቀሰርን አድበስብሰን ለማለፍ ብንወስን ዞሮ ዞሮ ተጎጂዎቹ እራሳችን ነን። ከዛም በላይ ልጁን ወደተጨማሪ ስህተት መንዳት ይሆናል። “ነብይ” እስራኤል ዳንሳ ለተናገረው ትንቢት ማብራርያ ወይም ስህተቱን የሚያምንበትንና ንስሃ የሚገባበትን ሁኔታ እንዲፈጠር እግዚአብሔር እንዲረዳው ከቻልን በግል እና በህብረት ጸሎት ብናደርግለትና በሌላ በቻልነው ሁሉ ብንረዳው መልካም ነው። “ነብይ” እስራኤል ዳንሳ ብዙ መልካም ነገር የሰራ ነው፣ የታዩ በምስክር የተረጋገጡ ተዓምራቶች ያደረገ ነውና እንዴት ተሳሳትክ ይባላል የሚል እንደምታ ያለው ክርክርም በሌላ በኩል ቢመጣም፣ ምንም እንኳን ለዙህ ዓይነቱ ሁለት ፈርጅ ያለው ምላሽ ቢኖርም፣ ለጊዜው ነገር ለማብረድ አንደኛውን መልስ ትተን፣ ልክ ነው መልካም ምስክርነቶች አሉት ምስክሮችንም ሰምተናል ብንል እና ብንስማማ እንኳን ያን ስላደረገ አይሳሳትም፣ ወይም ስህተትም ቢያደርግም ችግር የለም ብለን ማለፍ አለብን ብዬ አላምንም። ይልቁንም የኢወአክሕ መግለጫ ፋይዳ ያለው የሚሆነው እዚህ ነው። “ነብይ” እስራኤል ዳንሳ ሰው ነው ሊሳሳት ይችላል፣ ሲሳሳት ደግሞ ስህተቱን አስተካክሎ እንዲመለስ ማበረታታትና በፍቅር ማቅናት የሁሉም ህዝበ ክርስቲያን ግዴታ ነው። የኢወአክሕ መግለጫም ይሄንኑ ያካተተ በመሆኑም የፈራጅነት ወይም የድንጋይ ወርዋሪነት ባህሪ እንደሌለው ያሳያል። ታዲይ ይህ ዓይነትን ትእይንት እየተደጋገመ እኛን ከማሰልቸት አልፎ በማያምኑት ዘንድ መላገጫ ሆነን ወንጌልን ለመስበክ የሚያዳግትበት ደረጃ እንደ ደረሰ እየታዘብን ባለንበት ወቅት እንደኔ ያሉ ተራ ዓማኞች ምን ማወቅና ማድረግ አለባቸው የሚለው ጋ እንምጣ።

            3 እንደኔ ያሉ ተራ ዓማኞች በዚህ ወቅት ምን ማወቅና ማድረግ አለባቸው
            1 ይህ አጋጣሚ የማንቂያ ደወል እንዲሆንልን እግዚአብሔር ይርዳን። ዘመኑ የመጨረሻው መሆኑን ልብ ብለን ወደ ቃሉ እንመለስ። በግል ከእግዚአብሔር ጋር ጊዜ በመውሰድ ቃሉን ማንበብ  በግላችን በይበልጥ መጸለይ ከምን ጊዜውም በላይ ማብዛት ግድ የሚልበት ሰዓት ላይ መሆኑን ማወቅና መተግበር። የመጣው ነፋስ ሁሉ የሚያንዥዋዥወን በዓለቱ ላይ ስላልተመሰረትን መሆኑን ማወቅ አለብን። እውነተኛውን በደንብ ካላወቅነው አታላዩን መለየት አንችልም
            2 ተዓምራት ስላየን እና ትንቢት ስለተነገረን ብቻ የምንከተል ሳንሆን ይልቁንም እንደዚህ ዓይነት ልምምዶችን ከማጽደቃችን በፊት ጊዜ ወስደን መመርመርና፣ ስህተት ስናይ በቀናነት ማቅናትን መለማመድ አለብን። ጌታ ሆይ ያሉትን ሁሉና በስሙ የነገዱትን ሁሉ ከጌታ እንደተላኩልን በሞኝነት መቀበል የምናቆምበት ጊዜው አሁን ነው። ማቴዎስ 721 23
            3 ተዓምራትና ድንቆችን የምንከተል ሳንሆን የሚከተሉን እንደሆነ መጽሓፍ ቅዱስ ይነግረናል ማርቆስ 161718 ፣ ስለዚህ እ አጥብቀን ክርስቶስን መከተል ይገባናል። በጎቼ ድምጼን ያውቃሉ ተብሎ እንደተጻፈ የክርስቶስን ድምጽ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መለማመድ ያለብን ዘመን በመሆኑ ተዓምራትና ድንቅን ስናሳድድ ድንገት ስዓቱ እንዳይደርስብን ማስተዋል የሚያስፈልግን ጊዜ መሆኑን ልብ ማለት አለብን።  
            4 ተሳስታችኋል አርሙ ሲባሉ የባጥ የቆጡን ለሚዘባርቁት በተለይም አሁን አሁን የማምለጫ ንግግር ሆኖ የመጣው እኛን ማን አስተማረንና የኛ ጥፋት አይደለም የሚባልን ሰበብ ሰምተን የምንታለል እንዳንሆን፣ ይልቁንም ለጥፋቱ ሃላፊነት የሚወስድ ትውልድ ለማፍራት እራሳች ማዘጋጀት ይጠበቅብናል። ፍሬን እንጂ የፈውስና የያልፍልሃል አይዞህን ፍርፋሪ የሚዘሩትን፣ በግድ አሜን እያስባሉ የነርሱ ተጧሪዎች ሊያደርጉ የሚተጉትን ያለፍርሃት መገሠጽ የምንችልበትን ብቃት ማዳበር አለብን።  
            5 እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች ሲመጡ ሊያስደነግጡ ቢችሉም በማስተዋልና በቀናነት ካየናቸው ከተሳሳትንበት ጎዳና ሊመልሱን፣ የጣልነውን የመደማመጥና የመከባበር ባህላችንን መልሰን ልናመጣበት የሚያስችል አጋጣሚ ሊፈጥሩልን እንደሚችሉ አስበን እንደ መልካም አጋጣሚ ልንጠቀምባቸው ይገባል።
            6 ያጠፉትን በፍቅር መክረን መልሰን ገንዘቦቻችን ማድረግን ባህላችን የምናረግበት አጋጣሚ መሆኑንም ልብ ልንል ያስፈልጋል። ከምንም አይነት ፍላጎት ተነስተው ይስሩት፣ በቸልታ ይሁን ወይ ጥቅማ ጥቅም ዓይናቸውን አሳውሮት፣ ዋናው ጉዳይ ከልባቸው ተጸጽተው ንስሃ ከገቡ መልሰን ገንዘቦቻችን አርገን መቀበል አለብን።
7 አሁንም ደግሜ ደጋግሜ የምናገረው ከሁሉ በላይ ፍጥረት ሁሉ በናፍቆት የሚጠብቀው ከተዓምራቶቻችንና ከዲስኩሮቻችን የበለጠ በየትኛውም ጊዜ ሳንዛነፍ በፍቅር የምንገለጥበትን ጊዜ እንደሆ ልብ ማለት አለብን ብዬ አሳሰባለሁ። ሮሜ 819
ስለዚህ ንቃ፤ ሊሞት የተቃረበውን የቀረውን ነገር አጽና፤ ሥራህ በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትም።እንግዲህ የተቀበልኸውንና የሰማኸውን አስታውስ፤ ታዘዘውም፤ ንስሓም ግባ። ባትነቃ ግን እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ፤ በየትኛው ሰዓት እንደምመጣብህም አታውቅም። ራዕይ 62—3

Monday, September 11, 2017

2010 የምን ዓመት ይሁንልን ወይስ በ2010 ምን እንሁን?

እኛ ለእናንተ ፍቅር እንዳለን ሁሉ እርስ በርስ ያላችሁን ፍቅርና ለሌሎችም ያላችሁን ፍቅር ጌታ ያብዛላችሁ፤ ያትረፍርፍላችሁም። 1 ተሰሎንቄ 3:12 

በመጀመሪያ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ማንንም ቡድን ወይም ግለሰብ ለመንቀፍ ወይም የማንም ትምህርት ላይ ጣት ለመቀሰር እንዳልሆነ ለአንባቢዎቼ ለማስገንዘብ እፈልጋለሁ። በዚህ ጦማር ላይ የሚወጡ ማንኛውም ጽሑፎች ሃሳብንና አስተሳሰብን የሚሞግቱ ብቻ እንጂ ከግለሰብ፣ ከድርጅት ወይም ከማንኛውም ቡድን ጋር ጠብ የሌላቸው እንዲሁም ያልወገኑ መሆናቸውን ከወዲሁ ማሳሰብ እወዳለሁ።

ይህ ጦማር የ 2010 ዓ ም አዲስ ዓመትን አስመልክቶ እንኳን አደረሳችሁ ለማለትና ስለ አዲስ ዓመት መርሖች ለመሞገት የተጻፈ መልዕትን መሆኑን አንባቢዎቼ ልብ እንዲሉ አሳስባለሁ። ከላይ ርእሱ ላይ እንደሚነበበው የ2010 ዓ ም መርሗችንን እያስመረጥኩ ነው። የምንጥስበት፣ የምንባረክበት፣ የምንወጣበት፣ ከፍ የምንልበት፣ የሞገስ የምናገኝበት፣ የምንልቅበት ወይስ የምን ይሁንልን? መምረጥ ቢቻል ብዬ ነበር። የኔ ሙግት ግን ሌላ ነው፣ በእርግጥ ለኔ አይደለም ዓመታቶቹ ቀናቶቹም ሁሉ የድል ናቸው ብዬ ነው የማምነው። ተባርከን፣ጥሰን፣ ወጥተን፣ ከፍ ብለን፣ ሞገስ አግኝተንና ልቀን ካበቃን 2010 ዓመታቶች እንዳለፉ የረሳን መሰለኝና ይህን ጽሑፍ ጫር ጫር ለማድረግ ተነሳሁ።  

ክርስትናን ከሌላው እምነት የሚለየው ዋናው ነገር ክርስቶስ በሞቱ ሞትን ድል ነስቶ በትንሳኤው ድል አድራጊነቱን አረጋግጦ ፈጽሞ ወዳለቀ ስራ የጠራን መሆኑ ነው። ክርስቲያን አሁን ሰይጣንን ድል ለማረግ ሳይሆን የሚተጋው፣ በክርስቶስ ያገኘውን ድል ለመውራስ ነው የሚተጋው። በረከትን፣ ከፍታን፣ ሞገስን በክርስቶስ ወራሾች ሆነናል ስለዚህ ዓመት በተቀየረ ቁጥር የመውረስ፣ የመባረክ እያልን ከመታገል ይልቅ የሚበጀን የተሰጠንን የምንወርስበት ዓመት እንዲሆንልን ምን እናድርግ ብለን የምንጠይቅበት እንዲሆ እመክራለሁ። በመጀመርያ እስከዛሬ ባለፉት ዓመታት ያልናቸው ተፈጽመዋል ወይ ብለን ቆም ብለን የምንጠይቅበት ዓመት ይሆንልን ዘንድ እየተመኝሁ፣ የዚህ ዓመት መርሗችንን ከሁሉ በላይ የበረከት፣ የከፍታ፣ የሞገስ፣ የመላቅና የመውጣት ቁልፍ የሆነው እርስ በርስ ያለን ፍቅር እና ለሌሎችም ያለን ፍቅር የሚበዛበትና ብሎም የሚትረፈረፍበት ዓመት ብለን ብናውጀው፥ አንድም ካለንበት የድንብርብር ኑሮ ሳያመን እንወጣለን፣ ደግሞም በተጨማሪ እስካዛሬ ስንመኘው ስንናፍቀው ወደቆየነው፣ ይዘነው እንዳልያዝነው ወደ ቆጠርነው የበረከትና የከፍታ ኑሮ ይዞን ይገባል።

በመጀመርያ ለምን ያለፉት ዓመታት እንዴት አለፉ ብሎ መጠየቅ ለምን ያስፈልጋል? በእኔ አስተሳሰብ የኋላውን የማያውቅ የወደፊቱን ለመቀበል ዝግጁ አይሆንም። በእርግጥ ያልነው ሆኗል ብለን የእውንት መመርመራችን ለሁለት ዋና ዋና ነገሮች ይጠቅመናል። አንዱ ልክ ወይም ስህተት መሆናችንን ለማወቅ ሲጠቅመን ሌላው ደግሞ ለወደፊት እይታችንን እንዴት እንደምናስተካክል ትምህርት ይሰጠናል።

ለምን ፍቅር በዝቶ ይትረፍረፍ? ምክንያቱም ክርስትና ፍቅር ስለሆነ። መጽሓፍ ቅዱስ እንደሚናገረው እግዚአብሄር ፍቅር ነው። ፍቅር ከመሆኑም የተነሳም “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና፤” ዮሓንስ 316። ማርቆስ 12 ላይ ክርስቶስ ፍቅር የህግ ሁሉ መጠቅለያ ለመሆኑ እንዲህ አለ “ከሁሉ የሚበልጠው ይህ ነው፤ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤ አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ።’ ሁለተኛውም ይህ ነው፤ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።’ ከእነዚህም የሚበልጥ ትእዛዝ የለም።” ማርቆስ 12፡29 — 31። ምን ማለት ይሆን እኔ የገባኝን አጠርና ቀለል ብሎ እነሆ።

ጌታ አምላክን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ መውደድ ማለት ሁሉ ነገራችንን ለእግዚአብሄር ማስገዛት ማለት ነው። በሁሉ ነገር ለእርሱ ከተገዛን የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም የሚከብደን አይሆንም ስለዚህ ፈቃዱን ስንፈጽም ወደ ርስታችን ገባን ማለት ነው። እግዚአብሄርን ለመውደዳችን ሌላው ማረጋገጫ ደግሞ ባልንጀራችንን በውደዳችን ነው። ባልንጀራችንን መውደዳችን ደግሞ ምን ያህል እራሳችንን እንደምንወድ ያሳያል። እስቲ እናብራራው፣ ”ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ“ ያለን እግዚአብሔር ስለሆነ እኛም እርሱን ስለምንወድ ለቃሉ እንታዘዛለንና በራሳችን ላይ ሊሆንብን የማንፈልገውን ባንጀራችን ላይ እንዲደርስበት አንፈልግም። ስለዚህም በአስርቱ ትዕዛዝ ላይ ያሉትን ስምንቱን ለመፈጸም አንቸገርም ማለት ነው። እኛ ደግሞ እንታዘዝ እንጂ በጸጋ ዘመን ላይ ስለሆንን መንፈስ ቅዱስ ራሱ ያግዘናል። ባልንጀራየን አላማም፣ ክፉ አላስብበትም፣ አላመነዝርም፣ አልሰርቅም ወዘተ። ይልቁን ያለኝን አካፍላለሁ፣ መልካም ነው ብዬ ያሰብኩትን ሁሉ ለባልንጀራዬ አደርጋለሁ፣ እያየሁ እንዳላየሁ ማለፍ አቆማለሁ፣ ከክፋት ጋር አልተባበርም፣ ለተጎዱ መቆርቆር እጀምራለሁ፣ ባልቴቶችንና ወላጅ የሌላቸውን ህፃናት እየፈለኩ መርዳት እጀምራለሁ፣ የተራቡ አበላለሁ፣ የታረዙ አለብሳለሁ እያለ ይቀጥላል። እስቲ አስቡት እኔ ክርስቲያን ነኝ ብሎ የሚናገር ሁሉ በ2010 እኔ አፈቅራለሁ ብሎ ወገቡን ታጥቆ ቢነሳ በ2011 ላይ የድል፣ የመጣስ፣ የመባረክ፣ የከፍታ፣ የሞገስ እያልን የተመኘናቸውን ዓመታቶች ሁሉ ሳናስበው አጠገባችን እናገኛቸው ነበር። ለነገሩማ ቃሉም የሚለው ያን አይደል፥ “አስቀድማችሁ የእግዚአብሄርን መንግስትና ጽድቁንም ፈልጉ እነዚህ ሁሉ ይጨመርላችኋል።“ ማቴዎስ 633  እነዚህ ሁሉ የሚላቸው ምድራዊ የሆኑ በረከቶችን ነው።

ስለዚህ አፈቃሪዎች ለመሆን ምን እናድርግ መልሱ ፍቅርን እንወቅ ነው። ታዲያ ፍቅርን እንዴት ነው የምናውቀው ፍቅር የሆነውን ክርስቶስን በማወቅ። ክርስቶስን ስናውቀው ከርሱ ፍቅር ይይዘናል፣ ምክንያቱም ፍቅር የሚያሲዝ ልዩ የሆነ ግርማ ስላለው። በቃ ከርሱ ፍቅር ከያዘን እኛም ልክ እንደርሱ አፍቃሪ ለመሆን ምንም አይከብደንም። ይበልጥ ባወቅነው ቁጥር አፍቃሪነታችን ይበልጥ ይበረታል። የሚገርመው ይህ ማርቆስ 12 ላይ ከክርስቶስ ጋር ስለ ትዕዛዛቶች መበላለጥ የሚጠይቀው ፀሃፊ የክርስቶስን መልስ ሰምቶ መምህር ሆይ መልካም ብለሃል ብሎ ከመለሰለት በኋላ ክርስቶስ ፀሃፊውም “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” ብሎ ነበር የመለሰለት።

”ጸሓፊውም እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ መልካም ብለሃል፤ እርሱ አንድ መሆኑን፣ ከእርሱም ሌላ አለመኖሩን መናገርህ ትክክል ነው፤ እርሱን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም አእምሮህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ መውደድ፣ እንዲሁም ባልንጀራህን እንደ ራስህ መውደድ ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች ይበልጣል።”
ኢየሱስም በማስተዋል እንደ መለሰለት አይቶ፣ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው። ከዚህ በኋላ ሊጠይቀው የደፈረ ማንም አልነበረም።“ ማርቆስ 1232 34

የ2010 ጸሎቴ ያገሬን ሕዝብ የአዲስ አመት መርሖውን ከይሁንልን ወደ እንሁን እንዲለውጠው ነው። የዚህ ዓመት መርሗችንን ከሁሉ በላይ የበረከት፣ የከፍታ፣ የሞገስ፣ የመላቅና የመውጣት ቁልፍ የሆነው እርስ በርስ ያለን ፍቅር እና ለሌሎችም ያለን ፍቅር የሚበዛበትና ብሎም የሚትረፈረፍበት ዓመት ብለን ብናውጀው፥ አንድም ካለንበት የድንብርብር ኑሮ ሳያመን እንወጣለን፣ ደግሞም በተጨማሪ እስካዛሬ ስንመኘው ስንናፍቀው ወደቆየነው፣ ይዘነው እንዳልያዝነው ወደ ቆጠርነው የበረከትና የከፍታ ኑሮ ይዞን ይገባል።

ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች የፀለየውን እኔም ለአገሬ ልጆች ልፀልይና ላጠቃልል፥ እርስ በርስ ያላችሁን ፍቅርና ለሌሎችም ያላችሁን ፍቅር ጌታ ያብዛላችሁ፤ ያትረፍርፍላችሁም።

Wednesday, August 23, 2017

መታወቅ ወይስ ማወቅ?

. . . . . . . . በዚያ ጊዜ፣ ‘ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንት ክፉዎች፤ ከእኔ ራቁ’ ብዬ በግልጽ እነግራቸዋለሁ። ማቴዎስ 7: 23
በመጀመሪያ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ማንንም ቡድን ወይም ግለሰብ ለመንቀፍ ወይም የማንም ትምህርት ላይ ጣት ለመቀሰር እንዳልሆነ ለአንባቢዎቼ ለማስገንዘብ እፈልጋለሁ። የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ያለንበት ዘመን የመጨረሻው ዘመን መሆኑን ግነዛቤ ውስጥ በማስገባት ቀለል ባለ ገለጻ የራሴን እይታ ለማስተላለፍና ሌሎችንም ለማነጽ ነው።

“አላወቅኋችሁም” የምትለውን ቃል በጣም የምፈራት ይህን ቃል ሳነብ ነው። ምክንያቱም አውቀዋለሁ የምንለው ሁሉ እኛን ላያውቅን እንደሚችል እንዳስበው ስላምታስገድደኝ ነው። ለምሳሌ ብዙ ታዋቂ ሰዎችን ብዙ ጊዜ በተለያየ መገናኛ ብዙሃን ስለምናያቸው ወይም ስለነሱ ማንበብ ስለቻልን የምናውቃቸው ያህል ይሰማናል። በእርግጥ ይህ አይነት ዕውቀት ራሱን የቻለ ደረጃ ያለው ዕውቀት ነው። ከዚህ አልፈን ዕውቀትን መተንተን የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ስላልሆነ በዚሁ እንለፈው። ከዛም አልፈን በደንብ ቀረብ ብለን የምናውቃውቸው ሰዎች ይኖራሉ፣ ምን እንደሚወዱ ምን እንደሚጠሉና ከዛም ዘልቀን የግል ጉዳያቸውንም ሳይቀር ጠንቅቀን የምናውቅላቸው ሰዎች እኛን ያውቁናል ብለን በልበ ሙሉነት የምንናገርላቸው ሰዎች ይኖሩ ይሆናል።

አንድን ሰው ያወቅነው ስለመሰለን ወይም በደንብም ስላወቅነው በእርግጠኝነት ያ ሰው እኛን ያውቀናል ማለት አይቻልም። ጉዱ የሚታየው ስለማውቃቸው ያውቁናል ብለን ያሰብናቸው ሰዎች ስለኛ ሲጠየቁ ስለኛ ጠንቅቀው አውቀው መመለስ መቻላቸውን ስናረጋግጥ ብቻ ነው። ባጭሩ ያወቅነው የመሰለንን ነገር ሁሉ አውቀነዋል ማለት እንደማይቻል ሁሉ ፤ ያወቅነው ሁሉ አያውቀነም። ለዚህም ነው፣ “አላወቅኋችሁም” የምትለውን ቃል በጣም የምፈራት ይህን ቃል ሳነብ ነው ያልኩት።

በማቴዎስ 7 እና 25 ላይ የምናነበው የመጨረሻ ፍርድ በሚሆንበት ጊዜ የሚከሰተውን ሁኔታ ነው። በዚያም “አላወቅኋችሁም” የሚባሉት ሰዎች ”ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ“ ብለው የሚጠሩቱ፣ አጠራራቸውም የሚመስለው “እንዴ እኛኮ እናውቅሃለን ከማወቅም አልፈን እኮ በስምህ ብዙ ሰርተናል፣ ስላንተ እኮ ብዙ አውርተናል” የሚል ነው። ምስክሮች ኧረ አሉን የሚሉም ይመስላሉ። በተቃራኒው ደግሞ “አውቄያችኋለው” የተባሉቱ “እንዲህ አርገን ነበር እኮ፣ እንዲህ ብለን ነበር እኮ” እያሉ ሲደክሙ አይሰሙም። ኧረ ማድረጋችንንም አናስታውስም ነው የሚሉት።

በዘመናችንም ይህ ታሪክ እየተሰራ ያለ ይመስላል። በተለይም የኢንፎርሜሽን ዘመን ከመሆኑ የተነሳ እንዲሁም የማህበራዊ መገናኛዎች መፈጠርና በቀላሉ ለብዙሃኑ በአንድ መድረክ ብቻ መደረስ የሚቻልበት ዘመን ላይ ስለደረስን እዩኝ እዩኝ ማለት የጊዜያችን ትልቁ ፈተና ነው። በአሁኑ ዘመን እራሳችንን በራሳችን ቀድተን የምንኖርበትን ቤት ይሁን፣ የለበስነውን ልብስ ወይ የምንነዳውን መኪና ይሁን ወይ ቁመናችንን ለማሳየት ግልጽ ባልሆነ መልኩ እዚህ ግቡ የማይናሉ ዓላማቸው ምን እንደሆነ የማይታወቁ መልዕክቶችን ማስተላለፍ የጊዜው ብሂል ከሆነ ቆይቷል። ከዛም አልፎ የቴሌቪዥን አገልግሎት ከሌላችሁ ወንጌል መስበክ አይቻልም የተባለ እስኪመስል ድረስ  ብሎ መናገር የማይከብድበት ጊዜ ሆኗል። ኧረ ይሄ ነገር ልክ አይደለም ብሎ ሃሳብ መሰንዘር ጊዜው እንዳለፈበት ሰው አስቆጠሮ “እንዴ ወጣት አይደለህ፣ እንዴ አራዳ መስለኽኝ፣ ውይ የክፍለ ሃገር ልጅ ነህ እንዴ” የሚያስብልበት ደረጃ ደርሰናል።

እነዚህ “አላወቅኋችሁም” የተባሉ ሰዎች በእርግጠ ስለ ክርስቶስ ብዙ የሚያወሩ፣ ከዛም አልፈው ተዓምራትና ድንቅ የሚፈጽሙ ኧረ እንዳውም በስሙ ሁሉ አጋንንት የሚያስወጡ ናቸው። ታዲያ እንዲህ ማለትህ በዚህ ዘመን የምናያቸው ይህን አይነት ነገር የሚያደጉ ሰዎች “አላወቅኋችሁም” ይባላሉ ልትለን ነው ብላችሁ መጠየቃችሁ ደግ ነው። እንግዲህ ከጠየቃችሁ መልስ ብዬ የምሰጣችሁ የሚከተለውን ይሆናል።

በክርስቶስ ዘንድ የሚታወቁትንና የማይታወቁትን ለመለየት መልሱን የምናገኘው በዛው በማቴዎስ 7 እና 25 ላይ ነው።
በማቴዎስ 7 15 — 18 “በውስጣቸው ነጣቂ ተኵላዎች ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው መካከላችሁ በመግባት ከሚያሸምቁ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ፤ ከእሾህ ቍጥቋጦ ወይን፣ ከኵርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁም ጥሩ ዛፍ ሁሉ ጥሩ ፍሬ፣ መጥፎ ዛፍ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል። ጥሩ ዛፍ መጥፎ ፍሬ፣ መጥፎም ዛፍ ጥሩ ፍሬ ማፍራት አይችልም። 

ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ ሲለን ስለ ክርስቶስ ብዙ የሚያወሩ፣ ከዛም አልፈው ተዓምራትና ድንቅ የሚፈጽሙ እና በስሙ አጋንንት የሚያስወጡ ሁሉ በደፈናው “አላወቅኋችሁም” ይባላሉ ብዬ አላምንም። ነገር ግን እንዲህ ማድረግ በራሱ ብቻ ፍሬ እንዳልሆነ ያሳየናል እንጂ። ፍሬ ለማየት ጊዜ ወስዶ መከታተል ይጠይቃል።

ለኔ “አላወቅኋችሁም” ይባላሉ ብዬ የማምነው፥
1 ከክርስቶስ ወንጌል ይልቅ የሰውን ፍልስፍና ወይም መጽሓፍ አንብበው እኔን የገባኝ ካልገባችሁ የሚሉ ወንጌል ሳይሆን ግን የሚመስል ፍልስፍና ይዘው ሌላው ካልገባው ብለው በየሰፈሩና በየአገሩ እየዞሩ ወንጌልን የሚሸቅጡ፤
2 ከክርስቶስ ስም ይልቅ ለራሳቸው ስምና ማዕረግ ብዙ የሚተጉ፣ ምስላቸውን በየቦታው በመለጠፍ ለመታየት የቋመጡ እና የነሱ አስተምህሮ ብቻ እንዲሰማ የሚሯሯጡ፤
3 በትምህርታቸው ላይ ጥያቄ ያነሳን በፍጥነት የሆነ ጎራ ጋ ወስደው የሚፈርጁ፣ ከቻሉም እኔን ከተቃወምክ ትሞታለህ ወይ እግዚአብሄር ይቀጣሃል ከማለት የማይቆጠቡ ደፋሮች፤
4 ነገራቸው ሁሉ ከገንዘብ ጋር የተቆራኘ፣ ብልጣልጥ በሆነ አቀራረብ በትምህርታቸው የሰውን ስሜት አስደስተው ከቻሉ ከየቤተክርስቲያኑ ሰዎች አፈናቅለው የራሳቸውን ቤተክርስቲያን ለመትከል ወደኋላ የማይሉ፣ ካልቻሉ አይን ባወጣ መልኩ ገንዘብ ጠይቀው ሰብስበው የሚሄዱ፤
5 ከእውነተኛው የእግዚአብሄር ቃል ይልቅ ለሰዎች የሚመች ስኬት የማግኛ፣ ከድህነት ማምለጫ፣ ከበሽታ መዳኛ እና የመሳሰሉ ምድር ተኮር ጉዳዮች ላይ በሰፊው ጊዜ የሚያጠፉ፤ ከወንጌል ይልቅ ስሜት አነቃቂ የሆኑ አስተምህዎች ላይ ያተኮሩ motivational speaking)
6 ፍሬ ብለው የሚያሳዩት ምን ያህል ገንዘብ እንዳላቸው፣ ምን ያህል አባል እንደመዘገቡ፣ ምን ያህል በዓለም ላይ ዝናን እንዳገኙ ሲሆን፣ በኛ ትምህርት ወይ ተዓምራት ጌታን የተቀበሉ እያሉ ባልለፉበት ነገር የሚመጻደቁና የቁጥር ስሌት ማሳየት የሚወዱ……. “ያልደከማችሁበትን እንድታጭዱ ላክኋችሁ፤ አድካሚውን ሥራ ሌሎች ሠሩ፤ እናንተም የድካማቸውን ፍሬ ሰበሰባችሁ።” ዮሓንስ 438
7 ያለምንም ማስረጃ በድፍረት እግዚአብሄር እንዲህ ብሎኛል የሚሉና፣ መረጃና መሰረት የሌለው ወሬ በድፍረት የሚያወሩ፤
8 ለሚያምነውም ለማያምነውም ተዓምራት ማድረግና ትንቢት መናገር የሚያዘወትሩና፣ መጽሓፍ ቅዱስን ለራሳቸው የውሸት ትምህርት እንደ ደጋፊ የሚወስዱ እንጂ ላነበቡት መጽሓፍም ይሁን ለተገረሙበት ፍልስፍና መጽሓፍ ቅዱስን እንደ መመረመርያ የማይጠቀሙ።

በተቃራኒው “ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን“ የተባሉት፥
1 ለማዕረጋቸው የማይጨነቁ፣ ከራሳቸው ስም ይልቅ ለክርስቶስ ስም የሚሞቱ፣ ልታይ ልታይ የማይሉ፣
2 ሰው የማያውቃቸው ብቻ ሳይሆኑ የሚያደርጉትን ነገር እንኳን የተለየ እንዳልሆነ የሚሰማቸው፣
3 ብልጣልጥነት የማይገባቸው፣ ነገራቸው ሁሉ ከገንዘብ ጋር ያልተቆራኘ፣ ሃብታም የመሆን ከባድ ምኞት የሌላቸው፣
4 ተዓምራትና ድንቅን በየቦታው እየዞሩ የማይከተሉ፣ ምድር ጊዜያዊ መኖርያቸው መሆኑን ስለተረዱ የዚህ ዓለም ጥቅማ ጥቅም የማያታልላቸው፣
5 የክርስቶስ አምባሣደር እንደሆኑ ስለገባቸው እራሳቸውን ከማንም ቡድን ይሁን ተቋም ጋ የማያቆራኙ፣
6 እንደ ክርስቶስ መኖር የህይወታቸው ዘይቤ ስለሆነ ለሚያደርጉት ነገር ማስረጃ እንኳን የማይሰበስቡ፣ ቁጥር እያሰሉ በኔ አገልግሎት ይህን ያህል ሰው እንዲህ ሆነ የማይሉ ‘ጌታ ሆይ፤ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህ? ወይም ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? እንዲሁም ታመህ ወይም ታስረህ አይተን መቼ ጠየቅንህ?’ በማቴዎስ 25 37᎐39 ብለው የጠየቁ።


ከዚህም በላይ ለሁለቱም ጎራ ዝረዝር ማውጣት ይቻላል። ዋናው ጥያቄ ግን እኔስ የት እሆን ያለሁት ብሎ መጥየቅ ነው። እግዚአብሔር ባስቅመጠን ቦታ ላይ ሆነን የእነ እከሌ መታወቅ አስደምሞን እኔም ካልታወኩ ብለን ከተቀመጥንበት ቦታ ተነስተን እንደ ዝንጉዎቹ ልጃገረዶች ዘየት ልንገዛ ስንሄድ በድንገት ሙሽራው መጥቶ ከሰርጉ እንዳንቀር እግዚአብሔር ይርዳን።  

Thursday, August 17, 2017

በእርግጥ መጽሐፉ ምን ይላል?

ለዚህ ጽሑፍ ምክንያት የሆነኝን ጉዳይ አንስቼ ልጀምር። በቅርቡ ከአንድ የቅርብ ወዳጄ ጋር ሆነን ስለ ብልጽግና ወንጌል እንዲሁም አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ስለተስፋፋው ”የነብያት“ እንቅስቃሴ አንስተን ስንጫወት የሊሊ መዝሙር እንደ አንድ ጥሩ መልስ መቅረቡ ስላስገረመኝ እስኪ ምንአልባት ይህ ጉዳይ ለብዙዎች የመነጋገርያ ጉዳይ ስለሆነ በሰፊው ልምጣበት ብዬ ይህን ጽሁፈ ጫር ጫር እንዳደርግ ምክንያት ሆነኝ።

ከአንኳሩ ጉዳይ ልጀምርና ፤ የትኛውንም የክርስትና አስተምህሮ መመዘን ያለብን በምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ በአጭሩና በማያሻማ መልኩ ስንመልሰው በመጽሓፍ ቅዱስ ብለን ነው። ለዚህም ነው ወንድሜ በመዝሙር መልስ ለመስጠት ሲታገል ሳየው ያሳዘነኝ። መጽሓፉ በእርግጥ ምን ይላል አትታመሙም፣ አትደኽዪም፣ ችግር ወይም መከራ አያገኛችሁም፣ አተጎሳቆሉም፣ አትሞቱም ይላል ሃብት በምድር አከማቹ፣ ጤነኞች ካልሆናችሁ ስለመዳናችሁ ተጠራጠሩ፣ ችግር ወይም መከራ ከመጣባችሁ የኔ ደቀ መዛሙርት ላለመሆናችሁ ምልክት ይሁን፣ ደግሞም የምን መጎሳቆል እንደዛማ ከሆናችሁ የኔ አይደላችሁም ይላል

በእርግጥ መጽሓፉ ምን ይላል እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንትም እኔን ምሰሉ ሲል ጳውሎስ ፤ ክርስቶስ በእርግጥ በምድር ሳለ በምድራዊ ቁሳቁስ ልቡ ተይዞ በዘመኑ አንደኛ የተባለ መኖርያ ቤት ውስጥ ይኖር ነበር፣ ሲጓጓዝም ምርጥ ምርጥ ጀልባዎች ላይ ይሳፈር ነበር እንዳውም አብዛኛዎቹ ጀልባዎች የግሎቹ ነበሩ፣ ደቀ መዛሙርቱም ዋናው ስራቸው የእርሱ ክቡር ዘበኛ መሆን ነበር፣ ከህዝብ በተሰበሰበ ገንዘብ የተሰራ በጊዜው አለ የተባለ መድረክ ላይ ነበር ትምህርት የሚያስተምረው ማለቱ ይሆን

በእርግጥ መጽሓፉ ምን ይላል ኧረ እንዳውም እኔ ስሄድ በእኔ ስም ህዝብ ሰብስባችሁ ሰዎችን ሰብስባችሁ ደስ ደስ የሚሉ ቃላቶች የሞሉባቸውን ትምህርቶች እያስተማራችሁ፣ አጋንንት በስሜ እያስወጣችሁ፣ ሰዉን ስጋዊ ፈውስ ብቻ እየፈወሳችሁ፣ ከቻላችሁ በዶላር ካልቻላችሁም ደግሞ በብር ገንዘብ እየሰበሰባችሁ ጠብቁኝ፣ ስመጣ ሂሳብ አወራርዳለሁ ይላልበእርግጥ መጽሓፉ ይህን ይላል
በእርግጥ መጽሓፉ ምን ይላልከእናንተ ላነሰው ለዛ ወንደማችሁ ወይም እህታችሁ ካልቻላችሁ በፌስ ቡክ ከቻላችሁ በራሳችሁ ቴሌቪዥን ምን ያህል ከሌላው የተሻለ ዕውቀትና የኑሮ ደረጃ እንዳላችሁ ጉራችሁን እየዘራችሁ ጠብቁኝ እንጂ የምን የተራበ ማብላት፣ የተጠማ ማጠጣት፣ የታረዘ ማልበስ ነው ለዛውም ማንም ሳያያችሁ፣ ሳይጨበጨብላችሁ ይል ይሆን  

በእርግጥ መጽሓፉ ምን ይላልእንኳን ካላችሁ ላይ ልትሰጡ ቀርቶ ከቻላችሁ በተዓምር ብር አባዝታችሁ ካልሆነም በእኔ ስም ተከልላችሁ ምንም የማያውቁትን የዋሆች አሳምናችሁ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በምድር አከማችታችሁ የሚያማምሩ ልብሶችንና  መኪናዎችን በየቀኑ እያቀያየራችሁ በሃብት ሰክራችሁ ስስትን ጠግባችሁ እኔን ከማያውቁኝና ከፈሪሳውያን በልጣችሁ ካልጠበቃችሁኝማ እኔም በተራዬ አላውቃችሁም እላችኋለሁ ይል ይሆን  

በእርግጥ መጽሓፉ ምን ይላልእስቲ እኔ ከምነግራችሁ እራሱ መጽሓፉን ምን እንደሚል አብረን አናነበውም።
ዮሐንስ 16: 33 “በእኔ ሰላም እንዲኖራችሁ፣ ይህን ነግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።
ማቴዎስ 10: 38-39 መስቀሉን ተሸክሞ የማይከተለኝ የእኔ ሊሆን አይገባውም። ሕይወቱን ሊያድን የሚፈልግ ያጠፋታል፤ ሕይወቱን ስለ እኔ አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያገኛታል።
ሮሜ 8: 35 ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? ችግር ነው ወይስ ሥቃይ፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ረሀብ፣ ወይስ ዕራቍትነት፣ ወይስ አደጋ ወይስ ሰይፍ?
1 ጴጥሮስ 4: 1 እንግዲህ ክርስቶስ በሥጋው መከራን ስለ ተቀበለ እናንተም በዚሁ ዐላማ ታጥቃችሁ ተነሡ፤ ምክንያቱም በሥጋው መከራን የሚቀበል ሰው ኀጢአትን ትቶአል።
1 ጴጥሮስ 3 : 13,14 መልካም ነገር ለማድረግ ብትቀኑ የሚጐዳችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራ ቢደርስባችሁ ብፁዓን ናችሁ፤ “ዛቻቸውን አትፍሩ፤ አትታወኩም።” 
ገላትያ 6: 2-3አንዱ የሌላውን ከባድ ሸክም ይሸከም፤ በዚህም ሁኔታ የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ። አንድ ሰው ምንም ሳይሆን ትልቅ የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላል። 
ፊልጵስዩስ 1: 29-30 በክርስቶስ እንድታምኑ ብቻ ሳይሆን ስለ እርሱ መከራ እንድትቀበሉም ይህ ጸጋ ተሰጥቶአችኋልና፤ ቀድሞ እንዳያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ በምትሰሙት በዚያው ዐይነት ተጋድሎ እናንተም እያለፋችሁ ነውና።
1 ጴጥሮስ 2: 21የተጠራችሁትም ለዚሁ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው።
ሮሜ8: 18የአሁኑ ዘመን ሥቃያችን ወደ ፊት ሊገለጥ ካለው ለእኛ ከተጠበቀልን ክብር ጋር ሲነጻጸር ምንም እንዳይደለ እቈጥራለሁ።
ማቴዎስ 7: 21 - 23 “በሰማይ ያለውን ያባቴን ፈቃድ ሳይፈጽም ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ አይገባም። በዚያ ቀን ብዙዎች፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህ አጋንንት አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ታምራት አላደረግንምን?’ ይሉኛል። በዚያ ጊዜ፣ ‘ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንት ክፉዎች፤ ከእኔ ራቁ’ ብዬ በግልጽ እነግራቸዋለሁ።

በመጨረሻብ ማቴዎስ 25 ላይ ከቁጥር 23 ጀምሮ እስከ 46 ያለውን እራሳችሁ እንድታነቡ እየጋበዝኩ፡ እንደ ማጠቃለያ በዘመናችን ለተከሰቱት አዲስ ለሚመስሉ ነገር ግን ከነጳውሎስ ዘመን ጀምሮ ለነበሩ እንግዳ መሰል አስተምህሮዎች እጃችንን ከመስጠታችን በፊት በእርግጥ መጽሓፉ ምን ይላል ብለን መጠየቅ እንጂ እነ እከሌ እኮ እንዲህ ብለው ዘምረዋል እንዲህ ብለው አስተምረዋል በማለት ለጆሮዋችን በሚመች መልኩ የመጣውን ትምህርት ይሁን ትንቢት አስተናጋጆች እንዳንሆን እንጠንቀቅ። ይልቁን የዘመኑ ትምህርትና ትንቢት ምነው የተራራውን ስብከት የሚሰብክ እና የሚተነብይ ያልሆነው ምነው ዝቅ በሉ፣ ታገሱ፣ በጽድቅ ኑሩ፣ ያላችሁን ስጡ፣ የተገፉትን ፈልጉ፣ልታይ ልታይ ከማለት ተቆጠቡ የሚል ትምህርት እና ትንቢት የሞኝነት ያህል የተቆጠረው እንዳያሰናክሏችሁ ከዚህ ዓለም ተግዳሮቶች ተጠበቁ ሳይሆን በዓለም እንደ ድል አድራጊነት የሚያስቆጥሩት ቁሳቁስ እና ገንዘብ ታገኛላችሁ ይሆንላችኋል ይሳኩላችኋል ላይ ብቻ ተነጠለጠሉ ይህን መጠየቅ በዘማናዊ ክርስትና ለተጠመቁት እንደ ሞኝነት ነውም አይደል


በእርግጥ መጽሓፉ ምን ይላልአትታመሙም፣ አትደኽዪም፣ ችግር ወይም መከራ አያገኛችሁም፣ አተጎሳቆሉም፣ አትሞቱም ይላል ሃብት በምድር አከማቹ፣ ጤነኞች ካልሆናችሁ ስለመዳናችሁ ተጠራጠሩ፣ ችግር ወይም መከራ ከመጣባችሁ የኔ ደቀ መዛሙርት ላለመሆናችሁ ምልክት ይሁን፣ ደግሞም የምን መጎሳቆል እንደዛማ ከሆናችሁ የኔ አይደላችሁም ይላል

እንደዛማ ከሆነ ብልጽግና ወንጌልን ብልጥ - ግና ብለን ብንጠራው ይሻል ይሆን

Wednesday, July 19, 2017

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ፩

፩. ኢትዮጵያና ሃገር

          ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል ስንሰማ ሃገር የሚል ሃሳብ ወደ ሁላችንም አእምሮ ይመጣል። ነገር ግን ሃገር የሚለውን ስናስብ ታዲያ ምን ይሆን ወደ አእምሮአችን የሚመጣው? ይህ ሃገር የሚለው ቃል ቤተሰብ ፣ ዘመድ አዝማድ ፣ ብሎም ሰፈር መንደሩን ወደ አእምሮአችን ማምጣቱ የማይቀር ነው። በጣም እናስፋውና ሕዝብ እና ተራራ ፣ ሸንትረር ፣ ወንዝ እና ፏፏቴውን ያሳስበን። ከዛም አልፎ የታሪክ አሻራችንን ሁሉ በምናባችን ውልብ ያርግብን እናም በተመስጦ ይሙላን። ይህ ሁሉ መልካም ነው። በእርግጥም የራሳችን የሆነ ታሪክ ያለን ፤ ባህላችንን ለዘመናት ጠብቀን የኖርን በሃይማንኖታችን የምንኮራና አሁንም ለማንነታችን የምንጨነቅ መሆናችን ካወቅንበት በእጅጉ ይጠቅመናል እንጂ አይጎዳንም።

          የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን እንዴት አድርገን ሃገር ከሚለው የውስጥ ስሜትን ዘልቆ ገብቶ ከሚቆረቁረው ሃሳብ ጋር አያይዘን ለሚረባን ነገር እናውለዋለን የሚለውን መዳሰስ ነው። በግልጽ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የሚለው ቃል በራሱ ሲጠራ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድ አይነት ስሜት አይኖረውም። ይህም እንዲሆን መጠበቅ ደግሞ ከልክ ያለፈ የዋህነት ይሆናል። ይህን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ እንዴት አድርገን ለሁሉም የኢትዮጵያዊነት ደም ላለበት ሰው ሲሰማው መልካም ስሜት በውስጡ እንዲፈጥር ማድረግ እንችል ይሆን? በእርግጥ ከባድ ስራን የሚጠይቅ ነው። አሁን ያለንበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ነኝ ለሚል የእኩል ሃገር ነች ከሚል ጭብጥ ለመነሳት አያስደፍርም። ለዚህም ነው ይህን ኢትዮጵያዊነት የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ እንዴት አድርገን ለሁሉም የኢትዮጵያዊነት ደም ላለበት ሰው ሲሰማው መልካም ስሜት በውስጡ እንዲፈጥር ማድረግ እንችላለን የሚለውን እንደዋና ሃሳብ ወስደን በግልጽ እና በሚታይ መልኩ መተንተን ያለብን። ከዛሬ ሦስት ሺህ ዓመትም ይሁን ከመቶ ዓመት ተነስተን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ብናይ የሚያኮሩ ታሪኮችን ብሎም ለዓለም ስልጣኔ ዕድገት ያበረከትነውን ማንሳትና በታሪካችን መኩራት እንችላለን። ያን ታሪካችንን ግን ካለፍንበት የቅርብ ታሪክ እንዲሁም ዛሬ ካለንበት የዓለም ስልጣኔና ዕድገት አንጻር ስናየው ከነበር ተምረን የአሁንን ታሪካችንን መለወጥ እንደሚገባን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በቀላሉ የሚስማማበት ጉዳይ ነው።

          ኢትዮጵያ ያላት የቅርብ ጊዜ ስም ደሃ፣ ኋላ ቀር፣ ድርቅና ረሃብ ያሉባት፣ ሕዝቦችዋ በስደት የታወቁ እና የመሳሰሉት ናቸው። በእርግጥ አሁን ባለንበት ሁኔታ እነዚህ ስሞች እየተቀየሩ እየሄዱ ይታያል። በኢኮኖሚ እድገት ተስፋ ከሚጣልባቸው ሃገሮች በተለይም ከአፍሪካ የቀዳሚነትን ስፍራ እያገኘች ያለችበት ሁኔታ እየታየ ነው። በዚህ ጊዜ ታዲያ የሕዝብ ስነ ልቦና እና የአስተሳሰብ እድገት አብሮ ካላደገ ለሚታለመው እና ለሚታየው ቁሳዊ ዕድገት ትልቅ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለው መተንበይ አያስቸግርም። ከዛም ባሻገር ነባራዊውን የኢትዮጵያን ገጽታ ለመቀየር ብዙ መስራትና የጅምላ የኢኮኖሚ እድገት ብቻውን ሊቀይረው ስለማይችል በግለሰብ ደረጃ የኢትዮጵያዊነት መገለጫዎችን ለመቀየር መትጋት እንዳለብን አጠያያቂ አይደለም። የሕዝብ ስነ ልቦና እና የአስተሳሰብ እድገት ለመለወጥ መጀመርያ መንግስት ብሎም የተለያዩ የፖለቲካ እና የሃይማኖት ድርቶች እንዲሁም በሃገር ውስጥና በዉጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በግለሰብ ደረጃ ግዴታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል። ኢትዮጵያና ሃገር በሚለው በዚህ ክፍል ውስጥ የምንዳስሰው እነዚህ የጠቀስናቸው እንዴት አድርገው ግዴታቸውን ቢወጡ ነው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ለሁሉም የኢትዮጵያዊነት ደም ላለበት ሰው መልካም ስሜት በውስጡ የሚፈጥረው የሚለውን ይሆናል። እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባን ሁለት ነገሮች አሉ። አንድ ፥ አሁን ባለው ሁኔታ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ደስተኛ አይደለም ወይም ነው ከሚል ተነስተን ሃሳብ መሰንዘር ተገቢ እንዳልሆነና፤ ሁለት ፥ በዚህ መጽሐፍም ይሁን ከሌላ ምንጭ የሚሰጥ ምንም እንኳን የረቀቀ ሃሳብ ቢሆን ሁሉምን ኢትዮጵያዊ ደስተኛ ያደርጋል ማለት ከእውነታ ጋር እነደመጋጨት መሆኑን ነው። በዚህ ጽሑፍም የሚሰነዘሩ ማንኛውም ሃሳቦች ከአንድ ኢትዮጵያዊነት በመልካም እንዲነሳና ከማንነቱ ጋርም ተያይዘው ላሉ መልካም ስሜትን እንዲፈጥር በቅንነት ከሚያስብ ግለሰብ የተነሰነዘሩ መሆናቸውን ልብ እንዲባል ከወዲሁ አሳስባለሁ።

          በዚህ አጋጣሚ ስለ መንግስት ስናወራ በደንብ መገንዘብ ያለብን ነገር መንግስት የሕብረተሰብ ነጸብራቅ መሆኑንና ፤ እስከዛሬ የታዩት መንግስታት በዘመናቸው የነበሩት የሕብረተሰብ ክፍሎች በታሪክ አጋጣሚ የወለዱዋቸው እናም ለቀጣዮ ትውልድ ያስተላለፏቸው መሆኑን ፤ ስለዚህ መንግስት እንዲህ ማድረግ አለበት ስንል ፥ ስንኩል የሆነውን የሕብረተሰብ ነጸብራቅ ነቅሶ በማውጣት እኛ የወረስነውን ጥፋት የሚመጣው ትውልድ እንዳይደግመው ከሚል ግልጽነት ተነስቶ መስራት ይገባዋል። መንግስት ስንል ከመዋቅር ጀምሮ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አማራጭ አስቀምጦ የሚተገብር የግለሰቦች ስብስብ ብለን በጣም በቀላሉ ብንገልጸው ጥሩ ነው። ይህ ስብስብ ሥልጣን በሚይዝበት ጊዜ ትክክል ነው ለሕዝብ ይበጃል ብሎ የሚያምንበትን የፖለቲካ ፣ የማህበረሰብና ፣ የኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም መተግበሩ ግልጽ ነው። ነገር ግን ይህን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም የማይቀበሉ አይበጀንም ብለው የሚከራከሩ የተለየ አማራጭ ያላቸውን የግለሰቦች ስብስብ ጋር መጋፈጡ ሳይታለም የተፈታ ነው። በዚህ ጊዜ ነው ታዲያ መንግስት የሚወስደው የመጋፈጥ ዘዴ በመጀመርያ የተለየ አማራጭ ያላቸው የግለሰቦች ስብስብ ላይ ቀጥሎም በሚከተልዋቸው ህዝቦች ላይ ከዛ በራሱ ላይ አልፎ ተርፎም በቀጣዩ ትውልድ ላይ ትልቅ እንደምታ የሚኖረው። እኔ ከሞትኩ አይነት ነገር ያለኔ ሃሳብ አለቀልን ስለዚህ ፀጥ ለጥ በሉ ከሆነ ፤ የመንግስት መልስ እምባ ማግነን ከሆነ ፤ ሰው ስለሃገሩ ሲጠየቅ የደስታ ሳይሆን የሃፍረት እንባ ፣ ልስራላት ፣ ላሻሽላት ሳይሆን ፣ መቼ ልላቀቃት የሚል የኢትዮጵያዊነት ደሙ መልካም ስሜት በውስጡ የሚፈጥር ሳይሆን ሃዘንን የሚሞላው ይሆንበታል። ይህን ደግሞ በሃገራችን ደጋግመን ደጋግመን አይተነዋል። የረጅም ጊዜም የድሃነት ተምሳሌት ያደረገን ከኔ ሌላ ለአሳር ነው የሚሉ መንግስታትን ማፈራረቃችን ዋነኛው ነው። መንግስት የተቃዋሚዎቹን መኖር እንደ መልካም አማራጭ ተቀብሎ የሚጠቅመውን ተቀብሎ ያልተስማማውን አማራጭ በክብር ትቶ መጓዝን ካልተለማመደ የመጀመርያ ተጎጂው እራሱ ነው የሚሆነው። የመጀመርያ ተጎጂ የሚሆንበትም ዋና ምክንያት የሌሎችን አማራጭ ሃሳቦች የማይቀበል ከሆነ ሌሎቹም የኔን ሃሳብ መቀበል ስልማይፈልጉ እንዴት ብዬ ላሳምን በሚል በመታመን ላይ ያልተመሰረተ አስተዳደርን ማራመድ ይጀምራል። ይህም ያለ መቀባበል እና ያለ መከባበር መንፈስን በሃገሪቷ ዜጎች ላይ ይፈጥራል። መቀባበል እና መከባበር የሌለበት ሃገር ደሞ በዜጎቹ የማንነት ስሜት ላይ ትልቅ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል። በዚህም ሂደት አማራጭ ሃሳቦች ምን እንደሆኑ የማያስተውሉ የተባሉትን ብቻ የሚሰሩ ሎሌዎች መዋቅሩን ይሞሉትና አድሎ የሰፈነበት አላዋቂነት የሚያሸልምበት ሃገር ይፈጠርና ኢትዮጵያዊነት ማሸማቀቅ ይጀምራል።

          መንግስት በተለይም የሚወክሉት ባለስልጣናት ዓላማቸው የተሻለ ሃገርን ብሎም ትውልድን ማፍራት ከሆነ የተለያዩ የፖለቲካ ፣ የማህበረሰብና ፣ የኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም አማራጮችን በልበ ሰፊነት ፣ በቅንነትና በድፍረት ማስተናገድ ሀላፊነታቸው መሆኑን በጥልቅ መረዳት ይገባቸዋል። የመንግስት ባለስልጣናት በመጀመሪያ ለራሳቸው ሲሉ ቀጥሎም ለልጆቻቸውና ለቀጣዮ ትውልድ ካለባቸው ሃላፊነት የተነሳ የሚመሩትን ሃገር ያለበትን ሁኔታ ተረድተው መልካም የሆነውን በማጠንከር መጥፎ የሆነውን በመቀየር የሃገርን ገጽታ የማሻሻልና ብሎም የመቀየር የቅድሚያ ሃላፊነት አለባቸው። አሁን ወዳለው የሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣ በመጀመርያ የሃገራችን ባለስልጣናት ማድረግ ያለባቸው ይህ እነሱ የሚመሩት ትውልድ ሳያልፍ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን ማድረግ እንደሚቻል በገሃድ ማሳየት ፣ ተጠያቂነት የሚባል ነገር እንዳለ ለማስተማር የሚታይ ስኬታቸውን ብቻ ሳይሆን ማድረግ ሲገባቸው ነገር ግን ሳያደርጉ ያለፉትን በማንሳት የሚቀጥለው ሃገር ተረካቢ እንዲማርበት በማድረግ ፣ ሃገሩን ለመልቀቅ ሳይሆን የጠፋውን ለማስተካከል ሃገሩን እንዲወድ ማበረታታት ፣ በፖለቲካዊ አቋማቸው ተቃራኒ ከሆኑዋቸው የፖለቲካ ቡድኖች ጋር ሰላማዊ ፉክክር ማድረግ እንደሚቻል ለትውልዱ ማስተማር ፤ ከኔ ጋር ካልተስማማህ በኔ መንግስት ውስጥ መኖር አትችልምን ትተው ነገ ስልጣን ባይኖረኝም በሃገሬ ተከብሬ የምኖርበትን ሁኔታ አሁን ስልጣን እያለኝ ላስተምር ብለው የሃገርን ገጽታ በቅንንነት እና በሰላማዊ ሁኔታ መቀየር ይጠበቅባቸዋል። ሲሾም ያልበላ የሚለውን ብሒል የመቀየር እድሉ ያለው ብሎም በኔ የስልጣን ዘመን የሕዝብ የኑሮ ደረጃ ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ ዘይቤም ተቀየረ ለማስባል የሚሰሩ ባለስልጣናት መኖራቸው ኢትዮጵያን ከሕዝቦችዋ አልፎ በሌሎች አለም ተወዳጅ የሚያስደርጋት ጊዜ ያለው አሁን ነው። ዘመኑ ምን አይነት እንደሆነ የገባው ባለስልጣን አሁን የሚያደርገው እስከዛሬ እንዳየናቸው ባለስልጣናት ገንዘብን ወደ ባዕድ አገር ማሸሽ ሳይሆን የሃገርን ሃብት ተጠቅሞ ባለቤቱ የሆነውን ሕዝብ ኑሮ አሻሽሎ የራሱን ሃገር ከሰለጠኑት ጎራ አሰልፎ ሳይሰጋ የሚኖርበትን ሃገር መገንባት ነው። መንግስት ይህን ከላይ የተጠቀሱትን ባደረገ መጠን የራሱንም የመኖር ህልውና እያረዘመ መሆኑን መገንዘቡ በጣም ተገቢ ነው። እነዚህን ነገሮች የሚያደርግ መንግስት አሁን ስልጣን የኔ ብቻ ማለቱን ይተውና ፤ ነገ ከስልጣን መውረድ የማያሰጋው ቢወርድም መልሶ ሊይዘው የሚችል እንደሆነ የሚያስብ ጤነኛ መንግስት ይሆናል ማለት ነው። ትዕግስተኛነትህ ምንም ሳይኖርህ ውስጣዊ ማንነትህ ደግሞ ስልጣን ሲኖርህ ይፈተናል እንደሚባለው አሁን ስልጣን ላይ የተቀመጡት መሪዎቻችን ውስጣዊ ማንነታቸውን የሚያሳዩበትን ሰፊ ዕድል የሚጠቀሙበት ሁነኛ ጊዜ ላይ እንዳለን ሁሉም ልብ ይለዋል። ዘመኑን አንብቦ ዘመኑን የሚቀድም ትውልድን መውለድ የምንጀምርበት ፣ ፈርቶና ተሸማቆ ከሃገሩ የሚኮበልልን ትውልድ የምናመክንበት ፣ የኔን ድርሻ መወጣት አለብኝ የሚል ለሆዱ ሳይሆን ለዐላማው የሚሞት ትውልድ የሚፈጠርበት ሁነኛ ጊዜ ላይ መሆናችንን ማስተዋል ያለብን መሆኑን የመንግስትን አመራር የያዙትን ሁሉ ማሳሰብ የግድ ይላል። ኢኮኖሚያችን ሲያድግ የምንመራው እኛው እንድንሆን የሚያስችለን ትልቁ ሚስጥር ያለው የትውልዱን የአስተሳሰብ አድማስ በማሳደግ ላይ ነው። ይህ ካልሆነ ግን የኛን የኢኮኖሚ እድገት ለሌሎች ሃብት ማሰባሰብያ መልካም አጋጣሚ ከማድረግ በላይ ምንም የምንፈይደው ነገር አይኖርም።

          የመንግስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም የሚወክሏቸው ግለሰቦች ዓላማቸው የተሻለ ሃገርን ብሎም ትውልድን ማፍራት ከሆነ የጭፍን ጥላቻ ፖለቲካን አስውግድው አዲስ እና በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ሊያለዝብ እና ከስጋት ነጻ የሚያደርገው የፖለቲካ አማራጭ ይዘው መምጣት ፤ የመንግስትንም ይሁን የሌሎች የፖለቲካ ፣ የማህበረሰብና ፣ የኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም አማራጮችን በልበ ሰፊነት ፣ በቅንነትና በድፍረት ማስተናገድ ሀላፊነታቸው መሆኑን በጥልቅ መረዳት ይገባቸዋል። መንግስት የነካውን ነገር ሁሉ እየወሰዱ እንክን ከማውጣት መልካም የሆነውን ስለ መልካምነቱ እውቅና በመስጠት ፣ ለእንከኑ ደሞ ከመተቸት ባለፈ ቢሆን ጥሩ ነው የሚሉትን የመፍትሔ ሃሳብ መንግስት ተቀበለውም አልተቀበለውም በመሰንዘር ሃላፊነታችሁን በመወጣት ኢትዮጵያን እንደ ሃገር እንድንወዳት የሚያደርግ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል። በገረፍከኝ አለንጋ እኔም እገርፍሃለሁ ካልኩት አለንጋውን ለምን ይሰጠኛል? ይልቁን ቅንነት በአንዱ ወገን ከሌለ በሌላኛውም ወገን መጥፋት አለበትን? ማለትም አንተ ስትኖር ካላኖርከኝ እኔ ስኖር ላላኖርህ ይሆንና መፍትሔ የሌለው አምባጓሮ ይሆናል። አሁን የሚያስፈልገን ማስተዋል የሞላበት የመፍትሔ ማሰባሰብያ ጉባኤ እንጂ ፣ ስሜት የሞላው ለጦርነት የተጋጋለ ስብሰባ አይደለም። አምባጓሮና ጠብ ፣ ጦርነትና ሰቆቃ ፣ ረሃብና እርዛት የመገለጫችን ዋናዎች ሆነው ሰንብተናል። አሁን ማድረግ ያለብን እስከዛሬ ያልሞከርነውን በልዩነት መስማማትን ፣ ጦርነት ሳናነሳ መጣላትን ፣ ረሃብን ለማስወገድ የምንስማማበት ነገር ላይ አብረን መስራትን ነው። አምባጓሮና ጠብ ፣ ጦርነትና ሰቆቃ ፣ ረሃብና እርዛት በኛ አልተጀመሩም ነገር ግን ከነዚህ አስቀያሚ ነገሮች ጋር ተለማምዶ መኖርን ግን ሳስበው በኛ እንዳይጀመር እሰጋለሁ። ዘመኑን መርምረን ለጊዜው የሚሆንን የተቃውሞ ብልሃትን መፍጠር ግድ የሚለን ጊዜ ላይ ሳለን በጣም ጊዜ ያለፈባቸው አይነቶች የስድድብ ተራ ተቃውሞ ብሎም ሲጠነክር አሁን በስልጣን ላይ የወጣውን መንግስት ዘዴ ተጠቅሞ የፖለቲካ ለወጥ ለማምጣት ጦርነትን እንደ አማራጭ መያዝ በራሱ ታሪክን ወደ ሗላ መመለስ ይሆናል ብዬ እሰጋለሁ። በደም ወጥቼ በባዶ አልወርድም እዳሉት በደም የወጡት ፣ ያሁኑስ ይህን የማይልበት ምን ምክንያት ይኖረዋል? ለዚህም ነው ታሪክን የሗሊዮሽ የመውሰድ ነው የሚያስብለው። በተለይም አሁን ባለው የልከክልህ እከክልኝ የዓለም የፖለቲካ ድራማ ውስጥ ተቃዋሚዎች የሚመርጡት ድጋፍ ሰጪ ቡድን ስልጣን ከያዙ በሗላ ምን ያህል በስልጣን ላይ በነፃነት ሃገርን የማሳደግ የአሁን ህልማቸውን ያለ እንከን ሊያሰራቸው ይችላል? ወይስ ወደ ስልጣን አውጣን አንጂ የምተፈልገውን ታገኛለህ ብለው ነው የጦርነትን አማራጭ የወሰዱት? የሚለንውን ጥያቄም መጠየቅ ግድ ይላል። እንደ ግለሰብ አሁንን እያሰቡ ብቻ መኖር የሚረባን ነገር ለመከወን ካልጠቀመ ሃገር የሚያክልን ነገር ይዞ ታዲያ ዛሬን ብቻ እያዩ ነገ ለሚመጣው ትውልድ ምን የሚረባ ነገር ላውርስ ካልተባለ ባለንበት መሄድን መቀጠላችን የማይቀር ነው። በነገራችን ላይ ያለውን የመንግስት እንከን በሠለጠነ እንዲሁም በበሰለ መንገድ የሚያወግዙ በግለሰብ ደረጃ የሚያስገርም መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉ ሰዎች እንዳሉ መርሳት የለብንም። እንደዚህ ያሉ ግለሰቦች ዛሬ እንደ ስጋት ቢቆጠሩም የታሪክ አሻራቸውን በትልቁ ጥለው እንደሚያልፉ አይጠረጠርም። ያለንበት ዘመን ተለምዷዊ አምባገነናዊነትን የሚያስተናግድ እንዲሁም የስልጣን ጥሜ እስኪረካ ልኑር የሚያስብል ጊዜ አይደለም። የመንግስት ሥልጣን ይዞ ህዝብን በቅንነት መምራትና የህዝብን የኑሮ ደረጃ ካለበት ከፍ ማድረግ ካልቻለ የኢኮኖሚ እድገትን ቁጥር በማስላት ብቻ አደግን ማለት እንደ መሪነት የሚቆጠርበትም ጊዜ አይደለም። አሁን ሕዝብ ከመሪው የበለጠ መረጃ የሚያገኝበት የሚፈልገውን ሃገር መርጦ የሚኖርበት ዘመን እየመጣ ባለበት ዘመን አማራጭ የሌለውንና መረጃ ተነፍጎት ምንም ማደረግ የተሳነውን ሕዝብ መምራት እንደ መምራት የማይቆጠርበት ጊዜ ነው። ዘመንን ያለመረዳት የመንግስትንና ባለስልጣናቱን ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚ ፖለቲከኞችም ጭምር ከሆነ ፣ ሃገርን በጅምላ ከተቀረው የዓለም ክፍል የሚነጥል ብሎም ካለን የሚያሳፍር ታሪክ የማያስወጣን ክፉ በሽታ ነው። ይህን በመረዳት አሁን ያሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እራሳቸውን ዘመናዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሁልጊዜም እራሳቸውን በእርግጥ አሁን ባሉበት ሁኔታ ሃገር መምራት የሚያስችል ብቃት አለን ወይ ብለው መጠየቅ ይኖርባቸዋል። መቃወምና ሃገር መምራት ለየቅል ናቸውና። ብቃት ያለው አመራርን ይዘው መቅረብ ካልቻሉ ትርፉ የባሰ ወደ ሗላ መራመድ ይሆናል።

የሃይማኖት ተቋማትና ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የህብረተሰብ ክፍል ላይ ተጽእኖኦ ያላቸው መሆኑን በቀላሉ ማስተዋል የሚቻል ነው። ስለዚህም በሃገር ለውጥ ላይ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው የሚል እምነት አለኝ። ይህን በተመለከተም አንድ አንድ እራሳቸውን የቻሉ ምዕራፍ ሰጥቼ ሰፋ አድርጌ ዳስሼዋለሁ። በዚህ የመግቢያ ክፍል ውስጥ አጽንዖት ሰጥቼ ማየት የምፈልገው ፣ ሃገርን ከሕዝብ ጋር አቆራኝተን እንድናይና ሃገር ማለት አንዱና ዋነኛው ሕዝብ ስለሆነ የዛ ሃገር ሕዝብ ሃገርን ሲውክል ምን ሊፈጠር እንደሚችል በግሌ የማስበውን ማጋራት ነው።    መቼም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሃገሩ ከድህነት ተራ ወጥታ ካደጉትና ከበለጸጉት ሃገሮች ተርታ እንድትሰለፍ ይመኛል። ይህንን ምኞቱን ግን ዕውን ለማድረግ ምን ማድረግ ይጠበቅበታል? በመጀመርያ ራሱን ከማንም ጋር ሳያነጻጽር የኔ ሃላፊነት ምንድን ነው ብሎ የመጠየቅ ግዴታ አለበት ብዬ አስባለሁ።