Wednesday, July 19, 2017

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ፩

፩. ኢትዮጵያና ሃገር

          ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል ስንሰማ ሃገር የሚል ሃሳብ ወደ ሁላችንም አእምሮ ይመጣል። ነገር ግን ሃገር የሚለውን ስናስብ ታዲያ ምን ይሆን ወደ አእምሮአችን የሚመጣው? ይህ ሃገር የሚለው ቃል ቤተሰብ ፣ ዘመድ አዝማድ ፣ ብሎም ሰፈር መንደሩን ወደ አእምሮአችን ማምጣቱ የማይቀር ነው። በጣም እናስፋውና ሕዝብ እና ተራራ ፣ ሸንትረር ፣ ወንዝ እና ፏፏቴውን ያሳስበን። ከዛም አልፎ የታሪክ አሻራችንን ሁሉ በምናባችን ውልብ ያርግብን እናም በተመስጦ ይሙላን። ይህ ሁሉ መልካም ነው። በእርግጥም የራሳችን የሆነ ታሪክ ያለን ፤ ባህላችንን ለዘመናት ጠብቀን የኖርን በሃይማንኖታችን የምንኮራና አሁንም ለማንነታችን የምንጨነቅ መሆናችን ካወቅንበት በእጅጉ ይጠቅመናል እንጂ አይጎዳንም።

          የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን እንዴት አድርገን ሃገር ከሚለው የውስጥ ስሜትን ዘልቆ ገብቶ ከሚቆረቁረው ሃሳብ ጋር አያይዘን ለሚረባን ነገር እናውለዋለን የሚለውን መዳሰስ ነው። በግልጽ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የሚለው ቃል በራሱ ሲጠራ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድ አይነት ስሜት አይኖረውም። ይህም እንዲሆን መጠበቅ ደግሞ ከልክ ያለፈ የዋህነት ይሆናል። ይህን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ እንዴት አድርገን ለሁሉም የኢትዮጵያዊነት ደም ላለበት ሰው ሲሰማው መልካም ስሜት በውስጡ እንዲፈጥር ማድረግ እንችል ይሆን? በእርግጥ ከባድ ስራን የሚጠይቅ ነው። አሁን ያለንበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ነኝ ለሚል የእኩል ሃገር ነች ከሚል ጭብጥ ለመነሳት አያስደፍርም። ለዚህም ነው ይህን ኢትዮጵያዊነት የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ እንዴት አድርገን ለሁሉም የኢትዮጵያዊነት ደም ላለበት ሰው ሲሰማው መልካም ስሜት በውስጡ እንዲፈጥር ማድረግ እንችላለን የሚለውን እንደዋና ሃሳብ ወስደን በግልጽ እና በሚታይ መልኩ መተንተን ያለብን። ከዛሬ ሦስት ሺህ ዓመትም ይሁን ከመቶ ዓመት ተነስተን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ብናይ የሚያኮሩ ታሪኮችን ብሎም ለዓለም ስልጣኔ ዕድገት ያበረከትነውን ማንሳትና በታሪካችን መኩራት እንችላለን። ያን ታሪካችንን ግን ካለፍንበት የቅርብ ታሪክ እንዲሁም ዛሬ ካለንበት የዓለም ስልጣኔና ዕድገት አንጻር ስናየው ከነበር ተምረን የአሁንን ታሪካችንን መለወጥ እንደሚገባን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በቀላሉ የሚስማማበት ጉዳይ ነው።

          ኢትዮጵያ ያላት የቅርብ ጊዜ ስም ደሃ፣ ኋላ ቀር፣ ድርቅና ረሃብ ያሉባት፣ ሕዝቦችዋ በስደት የታወቁ እና የመሳሰሉት ናቸው። በእርግጥ አሁን ባለንበት ሁኔታ እነዚህ ስሞች እየተቀየሩ እየሄዱ ይታያል። በኢኮኖሚ እድገት ተስፋ ከሚጣልባቸው ሃገሮች በተለይም ከአፍሪካ የቀዳሚነትን ስፍራ እያገኘች ያለችበት ሁኔታ እየታየ ነው። በዚህ ጊዜ ታዲያ የሕዝብ ስነ ልቦና እና የአስተሳሰብ እድገት አብሮ ካላደገ ለሚታለመው እና ለሚታየው ቁሳዊ ዕድገት ትልቅ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለው መተንበይ አያስቸግርም። ከዛም ባሻገር ነባራዊውን የኢትዮጵያን ገጽታ ለመቀየር ብዙ መስራትና የጅምላ የኢኮኖሚ እድገት ብቻውን ሊቀይረው ስለማይችል በግለሰብ ደረጃ የኢትዮጵያዊነት መገለጫዎችን ለመቀየር መትጋት እንዳለብን አጠያያቂ አይደለም። የሕዝብ ስነ ልቦና እና የአስተሳሰብ እድገት ለመለወጥ መጀመርያ መንግስት ብሎም የተለያዩ የፖለቲካ እና የሃይማኖት ድርቶች እንዲሁም በሃገር ውስጥና በዉጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በግለሰብ ደረጃ ግዴታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል። ኢትዮጵያና ሃገር በሚለው በዚህ ክፍል ውስጥ የምንዳስሰው እነዚህ የጠቀስናቸው እንዴት አድርገው ግዴታቸውን ቢወጡ ነው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ለሁሉም የኢትዮጵያዊነት ደም ላለበት ሰው መልካም ስሜት በውስጡ የሚፈጥረው የሚለውን ይሆናል። እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባን ሁለት ነገሮች አሉ። አንድ ፥ አሁን ባለው ሁኔታ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ደስተኛ አይደለም ወይም ነው ከሚል ተነስተን ሃሳብ መሰንዘር ተገቢ እንዳልሆነና፤ ሁለት ፥ በዚህ መጽሐፍም ይሁን ከሌላ ምንጭ የሚሰጥ ምንም እንኳን የረቀቀ ሃሳብ ቢሆን ሁሉምን ኢትዮጵያዊ ደስተኛ ያደርጋል ማለት ከእውነታ ጋር እነደመጋጨት መሆኑን ነው። በዚህ ጽሑፍም የሚሰነዘሩ ማንኛውም ሃሳቦች ከአንድ ኢትዮጵያዊነት በመልካም እንዲነሳና ከማንነቱ ጋርም ተያይዘው ላሉ መልካም ስሜትን እንዲፈጥር በቅንነት ከሚያስብ ግለሰብ የተነሰነዘሩ መሆናቸውን ልብ እንዲባል ከወዲሁ አሳስባለሁ።

          በዚህ አጋጣሚ ስለ መንግስት ስናወራ በደንብ መገንዘብ ያለብን ነገር መንግስት የሕብረተሰብ ነጸብራቅ መሆኑንና ፤ እስከዛሬ የታዩት መንግስታት በዘመናቸው የነበሩት የሕብረተሰብ ክፍሎች በታሪክ አጋጣሚ የወለዱዋቸው እናም ለቀጣዮ ትውልድ ያስተላለፏቸው መሆኑን ፤ ስለዚህ መንግስት እንዲህ ማድረግ አለበት ስንል ፥ ስንኩል የሆነውን የሕብረተሰብ ነጸብራቅ ነቅሶ በማውጣት እኛ የወረስነውን ጥፋት የሚመጣው ትውልድ እንዳይደግመው ከሚል ግልጽነት ተነስቶ መስራት ይገባዋል። መንግስት ስንል ከመዋቅር ጀምሮ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አማራጭ አስቀምጦ የሚተገብር የግለሰቦች ስብስብ ብለን በጣም በቀላሉ ብንገልጸው ጥሩ ነው። ይህ ስብስብ ሥልጣን በሚይዝበት ጊዜ ትክክል ነው ለሕዝብ ይበጃል ብሎ የሚያምንበትን የፖለቲካ ፣ የማህበረሰብና ፣ የኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም መተግበሩ ግልጽ ነው። ነገር ግን ይህን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም የማይቀበሉ አይበጀንም ብለው የሚከራከሩ የተለየ አማራጭ ያላቸውን የግለሰቦች ስብስብ ጋር መጋፈጡ ሳይታለም የተፈታ ነው። በዚህ ጊዜ ነው ታዲያ መንግስት የሚወስደው የመጋፈጥ ዘዴ በመጀመርያ የተለየ አማራጭ ያላቸው የግለሰቦች ስብስብ ላይ ቀጥሎም በሚከተልዋቸው ህዝቦች ላይ ከዛ በራሱ ላይ አልፎ ተርፎም በቀጣዩ ትውልድ ላይ ትልቅ እንደምታ የሚኖረው። እኔ ከሞትኩ አይነት ነገር ያለኔ ሃሳብ አለቀልን ስለዚህ ፀጥ ለጥ በሉ ከሆነ ፤ የመንግስት መልስ እምባ ማግነን ከሆነ ፤ ሰው ስለሃገሩ ሲጠየቅ የደስታ ሳይሆን የሃፍረት እንባ ፣ ልስራላት ፣ ላሻሽላት ሳይሆን ፣ መቼ ልላቀቃት የሚል የኢትዮጵያዊነት ደሙ መልካም ስሜት በውስጡ የሚፈጥር ሳይሆን ሃዘንን የሚሞላው ይሆንበታል። ይህን ደግሞ በሃገራችን ደጋግመን ደጋግመን አይተነዋል። የረጅም ጊዜም የድሃነት ተምሳሌት ያደረገን ከኔ ሌላ ለአሳር ነው የሚሉ መንግስታትን ማፈራረቃችን ዋነኛው ነው። መንግስት የተቃዋሚዎቹን መኖር እንደ መልካም አማራጭ ተቀብሎ የሚጠቅመውን ተቀብሎ ያልተስማማውን አማራጭ በክብር ትቶ መጓዝን ካልተለማመደ የመጀመርያ ተጎጂው እራሱ ነው የሚሆነው። የመጀመርያ ተጎጂ የሚሆንበትም ዋና ምክንያት የሌሎችን አማራጭ ሃሳቦች የማይቀበል ከሆነ ሌሎቹም የኔን ሃሳብ መቀበል ስልማይፈልጉ እንዴት ብዬ ላሳምን በሚል በመታመን ላይ ያልተመሰረተ አስተዳደርን ማራመድ ይጀምራል። ይህም ያለ መቀባበል እና ያለ መከባበር መንፈስን በሃገሪቷ ዜጎች ላይ ይፈጥራል። መቀባበል እና መከባበር የሌለበት ሃገር ደሞ በዜጎቹ የማንነት ስሜት ላይ ትልቅ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል። በዚህም ሂደት አማራጭ ሃሳቦች ምን እንደሆኑ የማያስተውሉ የተባሉትን ብቻ የሚሰሩ ሎሌዎች መዋቅሩን ይሞሉትና አድሎ የሰፈነበት አላዋቂነት የሚያሸልምበት ሃገር ይፈጠርና ኢትዮጵያዊነት ማሸማቀቅ ይጀምራል።

          መንግስት በተለይም የሚወክሉት ባለስልጣናት ዓላማቸው የተሻለ ሃገርን ብሎም ትውልድን ማፍራት ከሆነ የተለያዩ የፖለቲካ ፣ የማህበረሰብና ፣ የኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም አማራጮችን በልበ ሰፊነት ፣ በቅንነትና በድፍረት ማስተናገድ ሀላፊነታቸው መሆኑን በጥልቅ መረዳት ይገባቸዋል። የመንግስት ባለስልጣናት በመጀመሪያ ለራሳቸው ሲሉ ቀጥሎም ለልጆቻቸውና ለቀጣዮ ትውልድ ካለባቸው ሃላፊነት የተነሳ የሚመሩትን ሃገር ያለበትን ሁኔታ ተረድተው መልካም የሆነውን በማጠንከር መጥፎ የሆነውን በመቀየር የሃገርን ገጽታ የማሻሻልና ብሎም የመቀየር የቅድሚያ ሃላፊነት አለባቸው። አሁን ወዳለው የሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣ በመጀመርያ የሃገራችን ባለስልጣናት ማድረግ ያለባቸው ይህ እነሱ የሚመሩት ትውልድ ሳያልፍ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን ማድረግ እንደሚቻል በገሃድ ማሳየት ፣ ተጠያቂነት የሚባል ነገር እንዳለ ለማስተማር የሚታይ ስኬታቸውን ብቻ ሳይሆን ማድረግ ሲገባቸው ነገር ግን ሳያደርጉ ያለፉትን በማንሳት የሚቀጥለው ሃገር ተረካቢ እንዲማርበት በማድረግ ፣ ሃገሩን ለመልቀቅ ሳይሆን የጠፋውን ለማስተካከል ሃገሩን እንዲወድ ማበረታታት ፣ በፖለቲካዊ አቋማቸው ተቃራኒ ከሆኑዋቸው የፖለቲካ ቡድኖች ጋር ሰላማዊ ፉክክር ማድረግ እንደሚቻል ለትውልዱ ማስተማር ፤ ከኔ ጋር ካልተስማማህ በኔ መንግስት ውስጥ መኖር አትችልምን ትተው ነገ ስልጣን ባይኖረኝም በሃገሬ ተከብሬ የምኖርበትን ሁኔታ አሁን ስልጣን እያለኝ ላስተምር ብለው የሃገርን ገጽታ በቅንንነት እና በሰላማዊ ሁኔታ መቀየር ይጠበቅባቸዋል። ሲሾም ያልበላ የሚለውን ብሒል የመቀየር እድሉ ያለው ብሎም በኔ የስልጣን ዘመን የሕዝብ የኑሮ ደረጃ ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ ዘይቤም ተቀየረ ለማስባል የሚሰሩ ባለስልጣናት መኖራቸው ኢትዮጵያን ከሕዝቦችዋ አልፎ በሌሎች አለም ተወዳጅ የሚያስደርጋት ጊዜ ያለው አሁን ነው። ዘመኑ ምን አይነት እንደሆነ የገባው ባለስልጣን አሁን የሚያደርገው እስከዛሬ እንዳየናቸው ባለስልጣናት ገንዘብን ወደ ባዕድ አገር ማሸሽ ሳይሆን የሃገርን ሃብት ተጠቅሞ ባለቤቱ የሆነውን ሕዝብ ኑሮ አሻሽሎ የራሱን ሃገር ከሰለጠኑት ጎራ አሰልፎ ሳይሰጋ የሚኖርበትን ሃገር መገንባት ነው። መንግስት ይህን ከላይ የተጠቀሱትን ባደረገ መጠን የራሱንም የመኖር ህልውና እያረዘመ መሆኑን መገንዘቡ በጣም ተገቢ ነው። እነዚህን ነገሮች የሚያደርግ መንግስት አሁን ስልጣን የኔ ብቻ ማለቱን ይተውና ፤ ነገ ከስልጣን መውረድ የማያሰጋው ቢወርድም መልሶ ሊይዘው የሚችል እንደሆነ የሚያስብ ጤነኛ መንግስት ይሆናል ማለት ነው። ትዕግስተኛነትህ ምንም ሳይኖርህ ውስጣዊ ማንነትህ ደግሞ ስልጣን ሲኖርህ ይፈተናል እንደሚባለው አሁን ስልጣን ላይ የተቀመጡት መሪዎቻችን ውስጣዊ ማንነታቸውን የሚያሳዩበትን ሰፊ ዕድል የሚጠቀሙበት ሁነኛ ጊዜ ላይ እንዳለን ሁሉም ልብ ይለዋል። ዘመኑን አንብቦ ዘመኑን የሚቀድም ትውልድን መውለድ የምንጀምርበት ፣ ፈርቶና ተሸማቆ ከሃገሩ የሚኮበልልን ትውልድ የምናመክንበት ፣ የኔን ድርሻ መወጣት አለብኝ የሚል ለሆዱ ሳይሆን ለዐላማው የሚሞት ትውልድ የሚፈጠርበት ሁነኛ ጊዜ ላይ መሆናችንን ማስተዋል ያለብን መሆኑን የመንግስትን አመራር የያዙትን ሁሉ ማሳሰብ የግድ ይላል። ኢኮኖሚያችን ሲያድግ የምንመራው እኛው እንድንሆን የሚያስችለን ትልቁ ሚስጥር ያለው የትውልዱን የአስተሳሰብ አድማስ በማሳደግ ላይ ነው። ይህ ካልሆነ ግን የኛን የኢኮኖሚ እድገት ለሌሎች ሃብት ማሰባሰብያ መልካም አጋጣሚ ከማድረግ በላይ ምንም የምንፈይደው ነገር አይኖርም።

          የመንግስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም የሚወክሏቸው ግለሰቦች ዓላማቸው የተሻለ ሃገርን ብሎም ትውልድን ማፍራት ከሆነ የጭፍን ጥላቻ ፖለቲካን አስውግድው አዲስ እና በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ሊያለዝብ እና ከስጋት ነጻ የሚያደርገው የፖለቲካ አማራጭ ይዘው መምጣት ፤ የመንግስትንም ይሁን የሌሎች የፖለቲካ ፣ የማህበረሰብና ፣ የኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም አማራጮችን በልበ ሰፊነት ፣ በቅንነትና በድፍረት ማስተናገድ ሀላፊነታቸው መሆኑን በጥልቅ መረዳት ይገባቸዋል። መንግስት የነካውን ነገር ሁሉ እየወሰዱ እንክን ከማውጣት መልካም የሆነውን ስለ መልካምነቱ እውቅና በመስጠት ፣ ለእንከኑ ደሞ ከመተቸት ባለፈ ቢሆን ጥሩ ነው የሚሉትን የመፍትሔ ሃሳብ መንግስት ተቀበለውም አልተቀበለውም በመሰንዘር ሃላፊነታችሁን በመወጣት ኢትዮጵያን እንደ ሃገር እንድንወዳት የሚያደርግ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል። በገረፍከኝ አለንጋ እኔም እገርፍሃለሁ ካልኩት አለንጋውን ለምን ይሰጠኛል? ይልቁን ቅንነት በአንዱ ወገን ከሌለ በሌላኛውም ወገን መጥፋት አለበትን? ማለትም አንተ ስትኖር ካላኖርከኝ እኔ ስኖር ላላኖርህ ይሆንና መፍትሔ የሌለው አምባጓሮ ይሆናል። አሁን የሚያስፈልገን ማስተዋል የሞላበት የመፍትሔ ማሰባሰብያ ጉባኤ እንጂ ፣ ስሜት የሞላው ለጦርነት የተጋጋለ ስብሰባ አይደለም። አምባጓሮና ጠብ ፣ ጦርነትና ሰቆቃ ፣ ረሃብና እርዛት የመገለጫችን ዋናዎች ሆነው ሰንብተናል። አሁን ማድረግ ያለብን እስከዛሬ ያልሞከርነውን በልዩነት መስማማትን ፣ ጦርነት ሳናነሳ መጣላትን ፣ ረሃብን ለማስወገድ የምንስማማበት ነገር ላይ አብረን መስራትን ነው። አምባጓሮና ጠብ ፣ ጦርነትና ሰቆቃ ፣ ረሃብና እርዛት በኛ አልተጀመሩም ነገር ግን ከነዚህ አስቀያሚ ነገሮች ጋር ተለማምዶ መኖርን ግን ሳስበው በኛ እንዳይጀመር እሰጋለሁ። ዘመኑን መርምረን ለጊዜው የሚሆንን የተቃውሞ ብልሃትን መፍጠር ግድ የሚለን ጊዜ ላይ ሳለን በጣም ጊዜ ያለፈባቸው አይነቶች የስድድብ ተራ ተቃውሞ ብሎም ሲጠነክር አሁን በስልጣን ላይ የወጣውን መንግስት ዘዴ ተጠቅሞ የፖለቲካ ለወጥ ለማምጣት ጦርነትን እንደ አማራጭ መያዝ በራሱ ታሪክን ወደ ሗላ መመለስ ይሆናል ብዬ እሰጋለሁ። በደም ወጥቼ በባዶ አልወርድም እዳሉት በደም የወጡት ፣ ያሁኑስ ይህን የማይልበት ምን ምክንያት ይኖረዋል? ለዚህም ነው ታሪክን የሗሊዮሽ የመውሰድ ነው የሚያስብለው። በተለይም አሁን ባለው የልከክልህ እከክልኝ የዓለም የፖለቲካ ድራማ ውስጥ ተቃዋሚዎች የሚመርጡት ድጋፍ ሰጪ ቡድን ስልጣን ከያዙ በሗላ ምን ያህል በስልጣን ላይ በነፃነት ሃገርን የማሳደግ የአሁን ህልማቸውን ያለ እንከን ሊያሰራቸው ይችላል? ወይስ ወደ ስልጣን አውጣን አንጂ የምተፈልገውን ታገኛለህ ብለው ነው የጦርነትን አማራጭ የወሰዱት? የሚለንውን ጥያቄም መጠየቅ ግድ ይላል። እንደ ግለሰብ አሁንን እያሰቡ ብቻ መኖር የሚረባን ነገር ለመከወን ካልጠቀመ ሃገር የሚያክልን ነገር ይዞ ታዲያ ዛሬን ብቻ እያዩ ነገ ለሚመጣው ትውልድ ምን የሚረባ ነገር ላውርስ ካልተባለ ባለንበት መሄድን መቀጠላችን የማይቀር ነው። በነገራችን ላይ ያለውን የመንግስት እንከን በሠለጠነ እንዲሁም በበሰለ መንገድ የሚያወግዙ በግለሰብ ደረጃ የሚያስገርም መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉ ሰዎች እንዳሉ መርሳት የለብንም። እንደዚህ ያሉ ግለሰቦች ዛሬ እንደ ስጋት ቢቆጠሩም የታሪክ አሻራቸውን በትልቁ ጥለው እንደሚያልፉ አይጠረጠርም። ያለንበት ዘመን ተለምዷዊ አምባገነናዊነትን የሚያስተናግድ እንዲሁም የስልጣን ጥሜ እስኪረካ ልኑር የሚያስብል ጊዜ አይደለም። የመንግስት ሥልጣን ይዞ ህዝብን በቅንነት መምራትና የህዝብን የኑሮ ደረጃ ካለበት ከፍ ማድረግ ካልቻለ የኢኮኖሚ እድገትን ቁጥር በማስላት ብቻ አደግን ማለት እንደ መሪነት የሚቆጠርበትም ጊዜ አይደለም። አሁን ሕዝብ ከመሪው የበለጠ መረጃ የሚያገኝበት የሚፈልገውን ሃገር መርጦ የሚኖርበት ዘመን እየመጣ ባለበት ዘመን አማራጭ የሌለውንና መረጃ ተነፍጎት ምንም ማደረግ የተሳነውን ሕዝብ መምራት እንደ መምራት የማይቆጠርበት ጊዜ ነው። ዘመንን ያለመረዳት የመንግስትንና ባለስልጣናቱን ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚ ፖለቲከኞችም ጭምር ከሆነ ፣ ሃገርን በጅምላ ከተቀረው የዓለም ክፍል የሚነጥል ብሎም ካለን የሚያሳፍር ታሪክ የማያስወጣን ክፉ በሽታ ነው። ይህን በመረዳት አሁን ያሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እራሳቸውን ዘመናዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሁልጊዜም እራሳቸውን በእርግጥ አሁን ባሉበት ሁኔታ ሃገር መምራት የሚያስችል ብቃት አለን ወይ ብለው መጠየቅ ይኖርባቸዋል። መቃወምና ሃገር መምራት ለየቅል ናቸውና። ብቃት ያለው አመራርን ይዘው መቅረብ ካልቻሉ ትርፉ የባሰ ወደ ሗላ መራመድ ይሆናል።

የሃይማኖት ተቋማትና ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የህብረተሰብ ክፍል ላይ ተጽእኖኦ ያላቸው መሆኑን በቀላሉ ማስተዋል የሚቻል ነው። ስለዚህም በሃገር ለውጥ ላይ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው የሚል እምነት አለኝ። ይህን በተመለከተም አንድ አንድ እራሳቸውን የቻሉ ምዕራፍ ሰጥቼ ሰፋ አድርጌ ዳስሼዋለሁ። በዚህ የመግቢያ ክፍል ውስጥ አጽንዖት ሰጥቼ ማየት የምፈልገው ፣ ሃገርን ከሕዝብ ጋር አቆራኝተን እንድናይና ሃገር ማለት አንዱና ዋነኛው ሕዝብ ስለሆነ የዛ ሃገር ሕዝብ ሃገርን ሲውክል ምን ሊፈጠር እንደሚችል በግሌ የማስበውን ማጋራት ነው።    መቼም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሃገሩ ከድህነት ተራ ወጥታ ካደጉትና ከበለጸጉት ሃገሮች ተርታ እንድትሰለፍ ይመኛል። ይህንን ምኞቱን ግን ዕውን ለማድረግ ምን ማድረግ ይጠበቅበታል? በመጀመርያ ራሱን ከማንም ጋር ሳያነጻጽር የኔ ሃላፊነት ምንድን ነው ብሎ የመጠየቅ ግዴታ አለበት ብዬ አስባለሁ። 

No comments:

Post a Comment