Friday, October 9, 2020

ጥብብ ……………. ለምን?

 1 ቆሮንቶስ 1፡18 — 31 

18 የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።
19 የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና።
20 ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን?
21 በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና።
22 መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥
23 እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥
24 ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው።
25 ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና።
26 ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁን ተመልከቱ፤ እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፥ ኀያላን የሆኑ ብዙዎች፥ ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም።
27 ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤
28 እግዚአብሔርም የሆነውን ነገር እንዲያጠፋ የዓለምን ምናምንቴ ነገር የተናቀውንም ነገር ያልሆነውንም ነገር መረጠ፥
29 ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ።
30 -
31 ነገር ግን። የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው።

በመጀመርያ ጥበብን በሁለት ከፍለን እንድናይ ግድ ይለናል፣ የዓለም ጥበብና የእግዚአብሔር ጥበብ።

በአጭሩ ስንገልገልጻቸው፡

·         የዓለም ጥበብ ጊዜያዊ ነው

·         የእግዚአብሔር ጥበብ ዘላለማዊ ነው

ብዙ ጊዜ ጥበብ ሲነሳ በመጀመርያ የሚታወሰን ጠቢቡ ሰለሞን  ነው ብዬ እገምታለሁ።

ታሪኩም በ1 ነገስት 3 እና 4 ላይ ይገኛል።

የሰለሞን ጥበብ በዋናነት ምድራዊ የነበረና የዓለምን ታላላቅ መንግስታት ቀልብ የሳበ ነበር። የጥበቡም ታላቅነት የሚወዳደረው በዘመኑ ከነበሩ የምስራቅ ሰዎችና ከግብጽ ጋር ነበር። ከነሱም ተወዳድሮ ወደር አልተገኘለትን ነበር። ነገር ግን የሰለሞንን ታሪክ ስናጠናው በእድሜው መገባደጃ ላይ ልቡ ከእግዚአብሄር እንደራቀና እግዚአብሄር እንዳዘነበት በመጨረሻም እንደሞተ እናያለን።

ዛሬ ግን የማተኩረው ከሰለሞን የሚበልጠው በሚል ሉቃስ 11፡31 በተገለጸው ላይ ነው።

የሰለሞን ጥበብ ሲያልፍና ሲረሳ የእርሱ ግን ዘላለማዊ የሆነና ተወዳዳሪ የሌለው ነው።

እስቲ ወደ ዋናው መልእክቴ ከመግባቴ በፊት

ጥበብ ምንድን ነው ወዴትስ ይገኛል የሚለውን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባጭሩ እንይ



ጥበብ ምንድን ነው

ምሳሌ 4፡7 ጥበብ ታላቅ ነገር ናት፤ ስለዚህ ጥበብን አግኛት፤ያለህን ሁሉ ወይም ያገኘኸውን ሁሉ ብታስከፍልህም ማስተዋልን ገንዘብህ አድርጋት።

 ምሳሌ 3፡13-14 ጥበብን የሚያገኛት፣ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርጋት ሰው ቡሩክ ነው፤ እርሷ ከብር ይልቅ ትርፍ የምታመጣ፣ ከወርቅም ይልቅ ጥቅም የምታስገኝ ናትና።

 ምሳሌ 16፡16 ከወርቅ ይልቅ ጥበብን ማግኘት፣ ከብርም ማስተዋልን መምረጥ ምንኛ ይበልጣል!

 ምሳሌ 8፡1 - 6 ጥበብ ጮኻ አትጣራምን? ማስተዋልስ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ አታሰማምን? በመንገድ አጠገብ ባሉ ኰረብቶች፣ መንገዶቹ በሚገናኙበትም ላይ ትቆማለች፤ወደ ከተማዪቱ በሚያስገቡት በሮች አጠገብ፣ በመግቢያዎቹ ላይ፣ ድምጿን ከፍ አድርጋ እንዲህ ስትል ትጮኻለች፤

“ሰዎች ሆይ፤ የምጠራውኮ እናንተን ነው፤ ለሰው ልጆች ሁሉ ድምፄን ከፍ አደርጋለሁ።

እናንተ ብስለት የጐደላችሁ፤ ጠንቃቃነትን ገንዘብ አድርጉ፤እናንተ ተላሎች፤ ማስተዋልን አትርፉ። የምናገረው ጠቃሚ ነገር ስላለኝ አድምጡኝ፤ ቀና ነገር ለመናገር ከንፈሮቼን እከፍታለሁ።

 ምሳሌ 3:13 ጥበብን የሚያገኛት፣ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርጋት ሰው ቡሩክ ነው፤

 ምሳሌ 4:5 ጥበብን አግኛት፤ ማስተዋልን ያዛት፤ ቃሌን አትርሳ፤ ከእርሷም ዘወር አትበል።

ጥበብ ወዴትስ ይገኛል   

ምሳሌ 15፡33 እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብን መማር ነው፤ወይም ጥበብ እግዚአብሔርን መፍራት ታስተምራለች።ትሕትናም ክብርን ትቀድማለች።

ምሳሌ 19:23 እግዚአብሔርን መፍራት ወደ ሕይወት ይመራል፤እንዲህ ያለውም ሰው እፎይ ብሎ ያርፋል፤ መከራም አያገኘውም።

ምሳሌ 23:17 – 18 ልብህ በኀጢአተኞች አይቅና፤ነገር ግን ዘወትር እግዚአብሔርን ለመፍራት ትጋ። ለነገ ርግጠኛ አለኝታ ይኖርሃል፤ ተስፋህም ከንቱ አይሆንም።

ምሳሌ 28:14 እግዚአብሔርን ዘወትር የሚፈራ ሰው ቡሩክ ነው፤ ልቡን የሚያደነድን ግን መከራ ላይ ይወድቃል።

የእግዚአብሔር ፈቃድ

ዳዊት

መዝሙር 40፡8 አምላኬ ሆይ፤ ፈቃድህን ላደርግ እሻለሁ፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ አለ።

መዝሙር 143፡10 አንት አምላኬ ነህና ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ፤ ቅዱስ መንፈስህም በጽድቅ ምድር ይምራኝ።

ሓዋ 13:36 “ዳዊት በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ካገለገለ በኋላ አንቀላፍቶአል፤ …”

ጳውሎስ

1 ቆሮንቶስ 1፡1 በእግዚአብሔር ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ እንዲሆን ከተጠራው ከጳውሎስ፣ 

ሓዋ 21፡14 ምክራችንን አልቀበል ስላለን፣ “እንግዲህ የጌታ ፈቃድ ይሁን” ብለን ተውነው።

ሮሜ 8፡5 እንደ ሥጋ የሚኖሩ ልባቸውን በሥጋ ፍላጎት ላይ ያሳርፋሉ፤ እንደ መንፈስ የሚኖሩ ግን ልባቸውን በመንፈስ ፍላጎት ላይ ያደርጋሉ።

ሮሜ 12፡2 መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።

ክርስቶስ

ማቴዎስ 6፡10 መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን።

ኢሳያስ 53፡10 መድቀቁና መሠቃየቱ ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር፤ እግዚአብሔር ነፍሱን የኀጢአት መሥዋዕት ቢያደርገውም እንኳ፣ ዘሩን ያያል፤ ዕድሜውም ይረዝማል፤ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል።

ሉቃስ22፡42 እንዲህም አለ፤ “አባት ሆይ፤ ፈቃድህ ከሆነ፣ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም።”

ዪሓንስ4፡34 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው፤ 

ዪሓንስ6፡38 ከሰማይ የወረድሁት የራሴን ፈቃድ ለማድረግ ሳይሆን፣ የላከኝን የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም ነውና፤ 

ማቴዎስ 12፡49-50 በእጁም ወደ ደቀ መዛሙርቱ እያመለከተ እንዲህ አለ፤ “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው፤ በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፣ ወንድሜ፣ እኅቴና እናቴም ነው።

ጥበበ እና የእግዚአብሔር ፈቃድ

ምሳሌ 19:21 በሰው ልብ ብዙ ሐሳብ አለ፤ የሚፈጸመው ግን የእግዚአብሔር ሐሳብ ነው።

ምሳሌ 21:30 እግዚአብሔርን ለመቋቋም የሚያስችል፣ አንዳችም ጥበብ ማስተዋልና ዕቅድ የለም።

መክብብ2:25 ከእርሱ ዘንድ ካልሆነ ማን መብላትና መደሰት ይችላል?

(ያለ እርሱ ፈቃድ የበላ ደስ ብሎትም ተድላን የቀመሰ ማነው?

ማቴዎስ 7፡21 “በሰማይ ያለውን ያባቴን ፈቃድ ሳይፈጽምጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ አይገባም።

እንግዲህ ጥበብ እንደ ሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ። ቀኖቹ ክፉ ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ። ስለዚህ ሞኞች አትሁኑ፤ የጌታ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ እንጂ።

ኤፌሶን 5: 15 – 17

ከእናንተ ማንም ጥበብ ቢጎድለው፣ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉም የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፤ ለእርሱም ይሰጠዋል

ያዕቆብ 1:5


በእ/ር ቃል መቃኘት

 

“እርሱ ኋጢአትን ሊያስወግድ እንደተገለጠ ታውቃላችሁ፤ በእርሱም ኋጢአት የለም። በእርሱ የሚኖር ኋጢአትን  አያደርግም፤ ኋጢአትን  የሚያደርግ ግን እርሱን አላየውም ወይም  አላወቀውም። ልጆች ሆይ፤ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ እርሱ ጻድቅ እንደሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ጻድቅ ነው። ኋጢአትን የሚያደርግ ከዲያቢሎስ ነው። ምክንያቱም ዲያቢሎስ ከመጀመርያው አንስቶ ኋጢአትን የሚያደርግ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ የተገለጠውም የዲያቢሎስን ስራ ሊያፈርስ ነው። ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኋጢአትን አያደርግም፤ የእርሱ ዘር በውስጡ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔር የተወለደ ኋጢአትን ሊያደርግ አይችልም። የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያቢሎስ ልጆች ተለይተው የሚታወቁት በዚህ ነው፤ ጽድቅን የማያደርግ፣ ወንድሙንም የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።”  1 ዮሐንስ 3 ፡ 5—10

የነዚህን አምስት ቁጥሮች በአጥጋቢ መልኩ ለመረዳት በጠቅላላ የዮሐንስ መልዕክትን ማወቅ ግድ ስለሚል፣ የዮሐንስን መልዕክት በአጭሩ እንከልሰውና፣ በዚህ ዘመን ከዚህ መልዕክት ምን እንማራለን የሚለውን አይተን እንጨርሳለን።

ሐዋርያው ዮሐንስ በጥንቷ ኤፌሶን ተቀምጦ ሳለ ሐዋርያዊ ሃላፊነት ተቀብሎባቸው ለነበሩ በአጎራባች ከተሞች ላሉ በርከት ያሉ የቤት ለቤት ቤተክርስቲያኖችን የተጻፈ ተጓዥ  መልዕክት ነው ለዚህ ነው በአንደኛ መልዕክቱ ላይ ለማን እንደተጻፈ ያልተገለጠበት ምክንያት።


በመልዕክቶቹ ላይ እንደምንረዳው የተጻፈላቸው አማኞች ለሆኑ አይሁዶች የነበረ ሲሆን፣ የተጻፈበት ዋና ምክንያትም በዛ ወቅት በነበረው የሃሰት ትምህርት እንዳይናወጡ ነው።

ይህ የሃሰት ትምህርትም የተነሳው በተወሰኑ ቤተክርስቲያናቱን ጥለው በወጡ ስብስቦች ሲሆን፣ እነርሱም

·    የክርስቶስን መሲህነት የማይቀበሉ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የሚክዱና ይህን የሃሰት ትምህርትንም አንቀበልም ብለው በቤተክርስታያናቸው የቀሩትን ሰዎች እንደ አላዋቂዎችና ለእውነት ጠላቶች አድርገው ይቆጥሩ ስለነበር ነው።

እነዚህ የሃሰት አስተማሪዎች ወይም ሐዋርያው ዮሐንስ “አሳቾች”የሚላቸው፣ የሚያስተምሩት ከኋጢአትና ከዓለም መለየት ድነትን ለሚያስገኝ እምነት አስፈላጊ አይደሉም በማለት  ስለነበር ነው።

ይህንንም ዓይነት ትምህርት በማስተማር ከሥነ—ምግባር ውጭ የሆነ ኋጢአትን የማይጠየፍ የኑሮ ልምምድ ይከተሉ የነበሩ ሲሆን፣

ለዚህ ነው ዮሐንስ

“በእርሱ የሚኖር ኋጢአትን  አያደርግም፤ ኋጢአትን  የሚያደርግ ግን እርሱን አላየውም ወይም  አላወቀውም። ልጆች ሆይ፤ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ እርሱ ጻድቅ እንደሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ጻድቅ ነው። ኋጢአትን የሚያደርግ ከዲያቢሎስ ነው።” ብሎ የፃፈው።

ወደዚህ ዓይነት አኗኗር ያስገባቸው ትልቁ ስህተትና የትምህርታቸው ዋና መሰረት የሆነው፣ መንፈስ በጠቅላላው ጥሩ ሲሆን፣ ቁስ ወይም ስጋ ደግሞ ሰይጣናዊ ነው የሚለው Gnosticism የተባለው አስየምህሯቸው ነው።

የዚህ አስተምህሮ ከዋናዎቹ መሰረታዊ ስህተቶቹ ጥቂቶቹ፡

1.      ቁስ ስለሆነ ሰዎች ስጋ ሳይሆኑ መንፈስ ናቸው፣ ምክንያቱም ቁስ ከሰይጣን ነው፣ መንፈስ ብቻ ነው ከእ/ር የሆነው

2.     ክርስቶስ በስጋ አልተገለጠም ወይም ሥጋ የሚመስል ነገር ነበር ያለው እንጂ ስጋ ለብሶ አልተመላለሰም

3.     የክርስቶስ አምላካዊ ባህርይ በምድር የተገለጠው ክርስቶስ ሲጠመቅ እንጂ ሰውም አምላክም ሆኖ አልመጣም፣ ደግሞም ሲጠመቅ የተገለጠው አምላካዊ ባህርይ ሲሞት ተለይቶታል።

4.     ስጋ ከሰይጣን ስለሆነና ቁስ ብቻ ስለሆነ በስጋችን የእ/ርን ሕግ ብንጥስም ምንም አይነት ችግር አያመጣም፣ ምክንያቱም መንፈሳችን ብቻ ነው ደህንነት ያገኘው የሚሉት ናቸው

ዚህ ዮሐንስ በዚያ ዘመን (1 ና 2ኛ ክ/ዘመን) ላይ ለነበሩ እውነተኛውን ወንጌል የተቀበሉት ሰዎች በነዚህ የሃሰት ትምህርቶች እንዳይናወጡ ነው ይህን መልዕክት የሚጽፍላቸው።

ይህ መልዕክት ከደብዳቤነቱ ይልቅ ግጥማዊ ቃና ያለው ለየት ባለ የአፃፃፍ ዘይቤ “Amplification” የተባለውን ዓይነት በስዕላዊ መግለጫና ዋናውን የወንጌልን ሃሳብ

·         ይወትን፣ እውነትንና ፍቅርን

በተደጋጋሚ በተለያዩ አንግሎች በማንሳትና፤

·         ውነትን ከውሸት፣

·         ፍቅርን ከጥላቻ፣

·         ብርሃንን ከጨለማ፣

·         የእ/ር ልጅነትን ከዲያቢሎስ ልጅነት

ንጽጽር እያስቀመጠ ከዚህ በፊት ያስተማራቸውን የወንጌል ትምህርት በድጋሚ የሚያብራራበት ክፍል ነው።

ቅድም ያነበብነው ክፍል ላይም

“የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያቢሎስ ልጆች ተለይተው የሚታወቁት በዚህ ነው፤ ጽድቅን የማያደርግ፣ ወንድሙንም የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።” ይላል።

ጠቅልል አድርገን ስናየው ይህ የዮሐንስ መልዕክት ጠንካራ መግቢያ Introduction 1:1-4 ያለው ሲሆን

“ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመርያ የነበረውን፣የሰማነውን፣ በዓይኖቻችን ያየነውንና እጆቻችን የዳሰሱትን እንናገራለን።” ብሎ በጠንካራ መግቢያ ይጀምራል

ዩሐንስ ምን እያላቸው ነው፣ ከክርስቶስ ከራሱ የተማርነውን ፣ ክርስቶስን በስማ በለው አይደለም የምናውቀው፣ ሕያው ምስክሮች ነን።

በመደምደምያው Conclusion ላይ ደግሞ 5፡18—21 እርግጠኝነት በተላበሰ አባባል ተመሳሳይ ነገር ይናገራ።

“የእግዚአብሔር ልጅ እንደመጣ፣ እውነተኛ የሆነውን እርሱን እርሱን እንድናውቅ ማስተዋልን እንደሰጠን እናውቃለን፤ እኛም እውነተኛው በሆነው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አለን።  እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።”

በመግቢያውና በመደምደምያው መሃከል ደግሞ ለሁለት ከፍሎ ሰፋ ያለ ማብራርያ ይሰጠናል።

በመጀመርያው ክፍል 1፡5 — 3፡10 ስለ ብርሃን የሚገልጽበት ሲሆን

ሁለተኛው ክፍል 3፡11—5፡17  ደግሞ ስለ ፍቅር የሚገልጽበት ነው።

በሁለቱም ክፍሎች መግቢያ

1፡5 ከእርሱ የሰማነውን ለእናንተም የምንነግራችሁ መልዕክት 

3፡11 ከመጀመርያ የሰማችኋት . . . . . . ይህች ናት this is the message

ባጭሩ ዮሐንስ በመጀመርያው ክፍል ላይ በብርሃን መመላለስ ማለት ከእ/ር ጋር ህብረት ማድረግ ማለት ነው ይላል። ህብረት የሚለው ቃል በተለይ እዚህ ጋር ትርጉሙ ጥምረት፣ ተካፋይ መሆን፣ ተሳታፊ መሆን ማለት ነው። ከእ/ር ጋር ያጣመረን፣ ተካፋዮች የሆነው ደግሞ በልጁ በክርስቶስ በኩል ነው የለናል።

ከእ/ር ጋር ህብረት አለን ስንል ደግሞ በብርሃን እንመላለለን ማለት ነው። በብርሃን መመላለስ ማለት ደግሞ ትዕዛዙን እንጠብቃለን ማለት ነው። ይህ ማለት እ/ርን በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችን፣ በፍጹም ሃሳባችን መውደድ ማለት ሲሆን፣ ነገር ግን ትዕዛዛቱን ሁሉ መጠበቅ ከባድ ቢሆንም ነገር ግን ብትወድቁ ከኋጥያት የሚያነጻችሁ የክርቶስ ደም አለ ብሎ      1፡5—10 ያገልጽላቸዋል።

በብርሃን መመላለስ ደግሞ ማለት እርስ በእርስ ህብረት መፍጠርም ጭምር ነው ብሎም ይገልጸዋል።

ደግሞም በብርሃን ከተመላለሳችሁ በዚህ አለም ላይ ድል ትቀዳጃላችሁ በዚህም ኋጥያትን እንዳትሰሩ ትጠበቃላችሁ የሚልም መልዕክ ያስተላልፍላችዋል።

በሁለተኛውም ክፍል 3፡11 — 5 ፡17

እ/ር ፍቅር ነው እናም የእ/ር የሆኑት እርስ በእርስ ይዋደዳሉ፣ ስለዚህ ጥላቻ በእናንተ ዘንድ አይኑር ይላቸዋል። ይህንንም የተማርነው ከአንዱ ከእ/ር ልጅ ከክርስቶስ ነው፣ እርሱም ስለእኛ ነፍሱን አሳልፎ እስኪሰጠን ድረስ አለም ወዷልና። ስለዚህ ክርስቶስ ያስተማረን ባልንጀራህን ውደድ የሚል ነው። ለዚህም ነው ባነበብነው ክፍል ላይም “ወንድሙንም የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።”

ስለዚህ መናፍስትን መርምሩ ምክንያቱም ብዙ ሃሰተኛ ነቢያት ወደ ዓለም መጥተዋልና። እነዚህንም ሃሰታኛ ነብያት የምትለዩዋቸው በትምህርታቸው ነው። ብሎ በም 4 ላይ ይናገራል።

እነርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ አልተገለጠም ብለው የሚያስተምሩና የዓለምን ስርዓት የሚከተሉ ናችው፣ የሚናገሩትም እንደ ዓለም ነው፣ ዓለምም ይሰማቸዋል። ስለዚህ ዓለም እናንተን ባይሰማችሁ አይግረማችሁ እናንተ ከዓለም ስላይደላችሁ ነው።

በ2፡16 —17 “በዓለም ያለው ሁሉ፥ የስጋ ምኞት፣ ያዓይን አምሮት የኑሮ ትምክህት ከዓለም የሚመጣ እንጂ ከእ/ር አይደለም። ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእ/ርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።”  ይላል።

ሐዋርያው ደጋግሞ የምጽፍላችሁ የመጀመርያውን የቆየውን ትዕዛዝ እንጂ ሌላ አዲስ ትዕዛዝ አይደለም እያለ ይነግራቸዋል። ይህም ማለት በመጀመርያ ከክርስቶስ የተማርነውንና ያየነውን የነገርናችሁን አሁንም አጥብቃችሁ ያዙ እያላቸው ነው።

ይህች በመጀመርያ ከክርስቶስ የሰሟት ትዕዛዝ በማቴዎስ ወንጌል 22፡35 — 40 ላይ ያለው

“ከእነርሱም አንድ የኦሪት ሕግ አዋቂ ሊፈትነው ፈልጎ እንዲህ አለው።

መምህር ሆይ ከህግ ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ትዕዛዝ ነው?

እርሱም እንዲህ አለው፤ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህ በፍጹም ሃሳብህ ውደድ”፣ ይህ የመጀመርያው ከሁሉ የሚበልጠው ትዕዛዝ ነው፤

ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል ይህም “ጎረቤትህን እንደራስህ  ውደድ” የሚለው ነው፤ ሕግና ነቢያት በሙሉ በእነዚህ ሁለት ትዕዛዛት ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው።”

አሁንም ዮሃንስ መልሶ የሚያስተምራቸው ይህንኑ ትዕዛዝ ነው።

እኛም በዚህ ዘመን ሃሰተኞች ነብያትን የምንለየው በዚሁ መንገድ ነው። የቀደመውን ትዕዛዝ በመፈጸም። ያንንም የምናገኘው በእ/ር ቃል ውስጥ ነው።

በአሜሪካ ውስጥ ሃሰተኛ የዶላር ኖቶችን የሚይዙ ሰዎች የሚሰለጥኝት እንዴት እንደሆነ ታውቃላችሁ?

ሃሰተኛ የዶላር ኖቶችን ሰብስቦ በማጥናት አይደለን፣ ይልቁንም እውነተኛውን የዶላር ኖት በደንብ በማጥናት እንጂ። እውነተኛውን በደንብ ጠንውቀው ሰለሚያውቁት ሃሰተኛውን በቀላሉ ይለዩታል።

እኛም የእ/ር ቃል ጠንቅቀን ካወቅን ሃሰተኛ ትምህርቶችን ለይተን ማወቅ እንችላለን። ዳዊት ከዚህ ነው “ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው የሚለው”

የመጀመርያው ሃሰተኛ አስተማሪዎችን የምንለይበት መንገድ ትምህርታቸው ክርስቶስ ማዕከል ያላደረገ እንደሆነ ነው። ለዚህ ነው 4፡3 ኢየሱስን የማይቀበል መንፈስ ግን ከእ/ር አይደለም።

ብዙ ጊዜ ሃሰተኛ አስተማሪዎች ስለራሳቸው ነው የሚያወሩት፣ እነርሱ እንዴት ልዩ እንደሆኑና በእ/ር እንደተመረጡ። እ/ር እነርሱን ብቻ እንደሚናገራቸው፣ እነርሱ ብቻ እንዲታዮ ነው የሚፈልጉት።

ሌላው ዓለማዊ ነገር ላይ፣ የሚያልፍ ነገር ላይ ትኩረት ይሰጣሉ፣ ሃብት ጤና ምቾት። እ/ር ልጁን የላከው እኛ በሚያልፈው ዓለም ላይ ተመችቶን እንድንኖር ሳይሆን ዘላለምን በመንግሰት ሰማያት ከአባታችን ጋር እንድንኖር ነው። ትንቢታቸውም ትምህርታቸውም ትበለጽጊያለሽ ይሳካልሻል ብቻ ነው።

ጽድቅን ብዙ ጊዜ አይሰብኩም፣ ከነርሱ ትምህርት ጋር የማይስማማውንም ልክ እውነትን እንደሳት እንዳልገባው ኋላ እንደቀረ አድርገው ያንቋሽሻሉ።

በመጨረሻም ዮሐንስ የመጀመርያውን መልዕክቱን የደመደመው

“ልጆች ሆይ ራሳችሁን ከጣዖቶች ጠብቁ” ነው ያለው።

ምን ማለቱ ነው ራሳችሁን ከማንኛውም ታላቁን እ/ርን ከራሱ ዕውቀት ብቻ ተነስቶ የእ/ርን ማንነት ለማናገር ከሚያስደፍር ሙከራ አርቁ ማለቱ ነው።

በዚህ ዘመን ያለው ጣዖት ራስን አግዝፎ የማየት፣ የዕውቀት ሁሉ ምንጭ ማድረግ፣ ከዚህም የተነሳ ልክ ዓለም ውስጥ እንዳሉ ሰዎች ሁሉ ለመታወቅ መጣር ነው።

ክርስቶስን ማወቅ ማለት እ/ርን ማወቅና ሌሎችን እንደራስ ማየትና ለሌሎች መኖር ማለት ብቻና ብቻ እንደሆነ ተገንዘቡ።

የሚመጣው ዓመት የሁሉ መሰረት በሆነው በእ/ር ቃል የመቃኘት ዓመት እንዲሆንልን ምኞቴና ፀሎቴ ነው።