Tuesday, May 29, 2018

ቀላል ግን የማይቃለል ደግሞም ከባድ ግን የማይካበድ


“እናንተ ሸክማችሁ የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀነበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሁት ነኝና ፤ ለነፍሳችሁ ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬም ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነውና።” ማቴዎስ 11፡28 — 29

ክርስቲያን ለመሆን በጣም ቀላል ነው። ይኽውም ፈላስፋ፣ የተማረ፣ ብዙ ያነበበ፣ ብዙ ሰው ማወቅ ወይ ደግሞ ሌላ ሌላ መሆን አያስፈልግም። በቃ ክርስቶስ የእግዚአብሄር ልጅ መሆኑን ብናምን በአፋችንም ብንመሰክር ድነን ክርስቲያን መሆን ብቻ ነው። የወህኒ ቤቱ ጠባቂ በሓዋርያት ስራ ምዕራፍ 16 ቁጥር 30 ላይ እነ ጳውሎስን “እናንተ ሰዎች እድን ዘንድ ምን ላድርግ” ሲላቸው የነገሩት እጅግ በጣም ቀላል ነገር ነው፣ “በጌታ በኢየሱስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ” በቃ ሌላ የተወሳሰበ ነገር የለውም። ወንጌል ውስብስብ አይደለም፣ ወንጌል ቀላል ነው። ጌታ ኢየሱስም ለዚህ ነው “ወደ እኔ ኑ” ብቻ ያለው። ወደ እኔ እንደዚህ ወይም እንደዚያ ሆናችሁ ኑ አላለም እንዳላችሁ ከነ ከበዳችሁ ነገር ከነ ድካማችሁ ኑ ነው ያለን። ያልተወሳሰበ ቅድመ ሁኔታ የሌለበት ጥሪ።  ማወቅ ያለበን አንድ ነገር ብቻ ነው፤ ዕረፍት መፈለጋችንን ብቻ። ሸክማችሁንና ደከማችሁ እኔ ላይ ጣሉትና እኔ የማሸክማችሁን ቀንበርና ሸክም ተሸከሙ፣ የእናንተን በእኔ ለውጡ ይለናል። ማወቅ ያለብን ዋና ነገር ክርስቶስ ጋ ስንመጣ ሸክማችን የከበደንና ደካሞች መሆናችንን በደንብ ማወቅ ከዛም የኛን ጥለን እርሱ የሚያሸክመንን ደስ ብሎን መሸክም እንዳለብን ነው። የራሳችንን ሸከምና የእርሱን ሸክም አንድ ላይ ይዘን መሄድ እንደማንችል ልብ ብለን መገንዘብ ይኖርብናል። ክርስትና ውሳኔን የሚጠይቅ ተረድተነው የምንገባበት የግል ጉዳይ ነው፤ ማቴዎስ 8፡ 18 — 22 እና ሉቃስ 14፡25—35። በቡድን የምንወስነው፣ ሌላው ስለገባ የምንገባበት ወይ ደግሞ ወላጆቻችን ስለሆኑ እኛም የምንሆነው ነገር እንዳይደለ ማወቅ ግድ ይለናል። የደከምን የከበደን ሁሉ ወደ እርሱ ስንመጣ ዕረፍት እናገኛለን፣ ዕረፍቱ ግን የሚገኘው መስቀሉ ስር ሸክማችንን ከጣልን በኋላ ከእርሱ ስንማር ነው። እርሱ የሚያሸክመንን ቀንበር መያዝ የምንችለው ከእርሱ ስንማር ነው። የእርሱን ማንነት ስናውቅና ስንቀበለው ዕረፍት እናገኛለን። ክርስቶስ ከእኔ የምትማሩት “የዋህነትና ትህትና” ነው ይለናል።

በዚህ ዓለም ስንኖር ክርስቲያን ለመሆን ቀላል፤ ነገር ግን ክርስቲያን መሆን ከባድ ነው። ይህን ያልኩበትም ምክንያት የክርስቶስን ህይወትና አስተምሮ ስናይ ከምንኖርባት ዓለም አካሄድ ጋር የማይገናኝ እንዳውም የሚቃረን ሆኖ እናገኘዋለን። ክርስቶስን ከእኔ ተማሩ የሚለንን እስኪ እንይ። የማቴዎስ ወንጌል ላይ ከምዕራፍ 5 እስከ 7 ክርስቶስ የእርሱ የሆኑት ወይም የእርሱን ቀንበር የተቀበሉት ምን ዓይነት ሰዎች ሊሆኑ እንደሚገባቸው ያስተምራል። በምዕራፍ 5 የተራራው ስብከት ከሚባለው ተነስቶ ስለ መግደል፣ ሰለ ማመንዘር፣ ስለ መሓላ፣ ስለ መቀበል፣ ስለ ምጽዋት አሰጣጥ፣ ስለ ጸሎት፣ ስለ ሀብት፣ ስለ ጭንቀት እና ሌሎች ነገሮች ያስተምራል። በእውነት ለመናገር ለመተግበር ከባድ የሆኑ አስተምህሮዎች ናቸው። ከባድ የሆኑበትም ምክንያት ከዚህ ዓለም የኑሮ አካሄድ ጋር ስለሚጣረሱ ነው። ታድያ ክርስትና ዕረፍት የሚሰጥና ሸክሙ ቀሊል ከሆነ፣ ለምን ስንተገብረው ይከብዳል፣ ለምን እንሰደድበታለን ለምንስ መከራ እንቀበልበታለን ይህ ጥያቄ ትክክለኛ ጥያቄ ነው። ምንአልባትም ሁላችንም በህይወታችን ውስጥ የሚሆነውን አይተን ደጋግመን ጠይቀን ይሆናል።

ለዚህም ነው ርዕሱን “ቀላል ግን የማይቃለል ደግሞም ከባድ ግን የማይካበድ” ያልኩት። ይህን ሁለት ፈርጅ ያለውን ሃሳብ ከመተንተኔ በፊት አንድ እውነታ ላካፍላችሁ። ኢየሱስ ለፈሪሳውያን ታልፎ ከተሰጠ በኋላ በስቅለት ቀን ከባድ ስቃይ ተቀብሏል። በሁለት አበይት ምክንያት፥ 1 እኛን ከአብ ጋር ሊያስታርቅ፣ 2 ከዓለም ጋር የማይስማማ ትምህርት ስለነበረው ነው። ስለ ክርስቶስ የመስቀል ስቃይ ያጠኑ የመጽሓፍ ቅዱስ ምሁራን በስቅለት ቀን ኢየሱስ 39 ጊዜ ተገርፏል ይላሉ፣ በጣም ሲያብራሩትም 13 በደረቱ ላይ  26 ደግሞ  በጀርባው ላይ በጅራፍ ተገርፏል ይላሉ። በዘመኑ በአይሁድ ህግ ትልቁ ግርፋት 40 ነበረ። አንዳንድ ጥናቶች ላይ ኢየሱስ 100 ጊዜ እንደተገረፈ ይናገራሉ። ይኽውም በጊዜው የነበረው የሮማውያን ህግ ምንም የግርፋት ቁጥር ልክ ስላልነበረው፣ እናም የክርስቶስ አስከሬን ተከፍኖበት የነበረውን አሁን ድረስም በጣልያን ቱሪን የሚገኘውን ጨርቅ “Shroud of Turin” ያጠኑ ሰዎችም የሚስማሙበት 100 መገረፉን ነው። ከዛም በላይ ክርስቶስ ዋና የምንላቸው በካቶሊኩም ዓለም “አምስቱ ቅዱስ ቁስሎች” ተብለው የሚታወቁ ቁስሎችን የቆሰለበት የስቅለትን ጊዜ ስናስብ ብሎም ከነ ግርፋቱ ለስድስት ሰዓታት በመስቀል ላይ መቃተቱን ስናስብ፤ ክርስትና ለመቀበል ቀላል ስለሆነ ክርስቶስ ለኛ ዕረፍትን ለመስጠት የከፈለው ግን ቀላል እንዳልሆነ ማወቅ ግድ ይለናል። ለዚህ ነው ክርስትና ቀላል ግን የማይቃለል የሆነው። ደግሞም እርሱ ለኛ ብሎ ያሳለፈው መከራና ስቃይ ሲገባን፣ እኛ ለእርሱ ብለን የምንቀበለውን መከራ እንዳናካብድ ግድ ይለናል። ስለዚህ ክርስትና ከባድ ግን የማይካበድ የሆነው። ከዛም አልፈን የአዲስ ኪዳን ሐዋርያት ስለ ክርስቶስ ያሳለፉትን መከራ እና ስቃይ ስናይ ደግሞም በዚህ ዘመን በክርስቶስ ምክንያት ክርስቲያኖች የሚያልፉበት መከራ በደንብ ብናጤነው፣ በዕውነት እኛ የምናልፍበት መከራ የማይካበድ መሆኑ ይገባናል። 2 ቆሮንቶስ 11፡16 — 33 ላይ ጳውሎስ በዝርዝር ስላለፈበት መከራ ጽፏል። ለጢሞትዮስም ሲመክረው “በእርግጥም በክርስቶስ ኢየሱስ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት መኖር የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።” ይለዋል። እንዲሁም 2 ቆሮንቶስ ላይ “ስለ ክርስቶስ በድካም፣ በስድብ፣ በመከራ፣ በስደትና በጭንቀት ደስ የምሰኘው ለዚህ ነው፤ ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝና።” ይላል። ጴጥሮስም እንዲሁ በመጀመርያ መልዕክቱ ምዕራፍ 3፡18—22 እና ምዕራፍ 4፡12—19 ክርስቲያን በመሆን ስልሚደርስ መከራ ይነግረናል።

በትንሳኤው ደግሞ የገለጠልን፣ በብዙ ስቃይ እና መከራ ያለፈው ይህ ጌታ በቃ አለቀ አሸነፍነው ሲሉ ድንገት ሳያስቡት በሶስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ የሲኦልን መክፈቻ ይዞ ተነሳ። ምን መከራው ቢበዛ፣ ስቃዩ የማያልፍ ቢመስል፣ ተሸነፈ አለቀለት የሚያስብል ሁኔታ ቢፈጠር ድል አድራጊው ጌታ በሰዓቱ ጊዜውን ጠብቆ በሶስተኛው ቀን በድል እንደተነሳ፣ እርሱን ለማክበር ብለው በመከራ ለሚያልፉትም በጊዜውና በሰዓቱ ሳይዘገይ ወይም ሳይፈጥን በትንሳኤው ሃይል ይመጣላቸዋል። ጳውሎስ አሁንም በ 2 ቆሮንቶስ 4 ላይ “ከየአቅጣጫው ብንገፋም አንንኮታኮት፤ ግራ ብንጋባም ተስፋ አንርቆጥም፤ ብንሰደድም ተጥልን አንቀርም፤ መትተው ቢጥሉንም አንጠፋም” ያለው። ለእርሱ ከተገዛንና የዓለምን ብልጭልጭ ነገር ንቀን በመንፈሳዊ ህይወታችን እርሱን ለመምሰል ከቆረጥን ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እንወቅ።

ስለዚህ ክርስትና ቀሎብን ከሆነ መስቀሉን እንይ፤ ደግሞም ክርስትና ከብዶብንም ከሆነ መስቀሉን እንይ። የዛን ጊዜ ቀላል ግን የማይቃለል ደግሞም ከባድ ግን የማይካበድ ይሆንልናል። ክርስትና ከድል ጀምረን የምንኖረው እንጂ ድል ለማድረግ ገና በራሳችን የምንታገለው እንዳልሆነ እንዲገባን ትንሳኤውን እናስተውል። ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ ብሎናል፥ “በእኔ ሰላም እንዲኖራችሁ፣ ይህን ነግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ ኧለባችሁ፤ ነገር ግን አይዟችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” ማቴዎስ 5፡11 — 12

Sunday, April 1, 2018

እውነተኛ ክርስትና ምንድን ነው?

በማግሥቱ ከቢታንያ ሲወጡ ኢየሱስ ተራበ። እርሱም ቅጠል ያላት የበለስ ዛፍ ከሩቅ አየ፤ ምናልባት ፍሬ ይገኝባት እንደሆነ ብሎ ወደ እርሷ መጣ፤ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። ከዚያም ዛፏን፣ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ፍሬ ከአንቺ አይብላ” አላት። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲናገር ሰሙ። ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፣ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያስወጣ ጀመር። የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ ገለባበጠ፤ ማንም ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳያልፍ ከለከለ። ሲያስተምራቸውም፣ “‘ቤቴ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት!” አላቸው። የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም፣ ይህን ሲሰሙ እንዴት እንደሚያጠፉት መንገድ ይፈልጉ ጀመር፤ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ በመገረማቸው ፈርተውታልና። በመሸም ጊዜ ከከተማዪቱ ወጥተው ሄዱ። የማርቆስ ወንጌል 11 ፥ 12 — 19

በዚህ ክፍል ውስጥ ኢየሱስ ሁለት ነገሮችን ሲያደርግ እንመለከታለን 1 ፍሬ ያላፈራችውን የበለስ ዛፍ ሲረግማትና 2 ለሁለተኛ ጊዜ ቤተ መቅደስ ውስጥ ገብቶ ነጋዴዎችን ሲያስወጣ እንመለከታለን። ሁለቱንም ድርጊቶች የፈጸመው የህማማት ሳምንት ተብሎ በሚገለፀው ሳምንት ውስጥ ነው። ሁለቱም ድርጊቶች አንድ አይነት ሃሳብ አላቸው ብዬ አምናለሁ። እስኪ ሁለቱንም በተራ እንመልከታቸው።

1 ፍሬ ያላፈራችውን የበለስ ዛፍ፦ የበለስ ዛፍ በተፈጥሮው ሰፋፊ ቅጠሎች ያሉት፣ ስሩ በጣም ጥልቅና ውሃን ከሩቅ ቦታ ስቦ ማምጣት የሚችል ሲሆን፣ ፍሬውና ቅጠሉ እኩል ነው የሚወጡት። በብሉይ ኪዳንም የበለስ ዛፍ የእስራኤል ብሔራዊ ምልከት ነበር። ክርስቶስ ፍሬ አገኛለሁ ብሎ ወደ ዛፏ የተጠጋው ቅጠሎቿን ከሩቅ አይቶ ነበር። ነገር ግን ፍሬ አጥቶባት ዳግመኛ እንዳታፈራ ሲረግማት እናያለን። በማግስቱ ጠዋትም ደቀ መዛሙርቱ ደርቃ አይተዋት ተገርመው ሲጠይቁት ስለ እምነት ሲያስተምራቸው በሚቀጥለው ክፍል ላይ እናያለን። እዚህ ክፍል ላይ የምንታዘበው የበለስ ዛፍዋን አስመሳይነት ነው። ፍሬ እንዳለው የበለስ ዛፈ በቅጠሎች ብቻ የታጀበች ነገር ግን ምንም ፍሬ የሌላት። ከዚህም ጋር ሌላ ተያይዞ የምናየው ጠቅላላ እስራኤል እንደ መንግስት ፍሬ አልባ ከሃይማኖተኝነት በቀር መንፈሳዊ መካን እንደሆነች በምሳሌአዊ ዘይቤ የሚያስረዳ ድርጊት ኢየሱስ እንደተናገረ የሚገልጽም አሉ።

2 የክርስቶስ ቤተ መቅደሱ ማንፃት፦ ቤተ መቅደሱ የፋሲካ በዓል በመድረሱ ብዙ ሰዎች የመንፃት ስርዓትን ለመፋጸም የሚመጡትን ሰዎች በማሰብ በቤተ መቅደሱ አካባቢና ውስጥ ይሸጡና ገንዘብ ይለውጡ ነበር። እነዚህ ነጋዴዎች የህዝቡን ልብ ያወቁና ጊዜውንም ተጠቅመው ብዙ ትርፍ ለግላቸው ሰብስበው ለመሄድ የመጡ እንጂ፣ ለህዝቡ ወይም ለእግዚአብሔር ቤት አስበው የመጡ እንዳልነበሩ በግልጽ ይታያል። ቤተ መቅደሱንም ካፀዳ በኋላ ኢየሱስ ቤተ መቅደሱን ለትክክለኛ ተግባር ሲያውለው እናያለን፣ ይኽውም ለማስተማርና እውነተኛ ፈውስ የሚፈልጉን በነፃ መፈወስ ነበር። ማቴዎስ 21 ፥ 12 — 15 ይመልከቱ።
እነዚህ ሁለት የኢየሱስ ድርጊቶች አስመሳይ የሆነ ወይም እውነታኛ ያልሆነን ክርስትና ከሩቅ በሚታዪ አማላይና ሃይማኖታዊ ነገሮች የታጀበ ነገር ግን ሲጠጉት ፍሬ ቢስ የሆነና፣ ሁኔታንና አመቺ ጊዜን ተጠቅሞ ግላዊ ጥቅምን ብቻ የሚሳድዱትን እየተቃወመ እንደሆነ ያሳዪናል። እንግዲህ ይህን ነገር ወደ ራሳችን፣ ወደ ቤተክርስትያናችን፣ ወደ ሃገራችንና ብሎም ወደ ዘመናችን ስናመጣው እንዲህ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ፍሬ ያለው እውነተኛ ክርስትያን ነኝን ሁኔታንና አመቺ ጊዜን ተጠቅሜ ግላዊ ጥቅሜን ብቻ የሚሳድድ ነኝንእውነትኛ ፍሬ ያለው ክርስቲያን አስመሳይና ሁኔታንና አመቺ ጊዜን ተጠቅሞ ግላዊ ጥቅምን ብቻ የሚሳድድ ሊሆን በፍፁም  አይችልም። እውነትኛ የመንፈስ ፍሬዎች በገላትያ መጽሃፍ ምዕራፍ 5፡22 — 26 ላይ ተጠቅሷል። የሥጋ ፍሬዎችም እነደዚሁ በገላትያ መጽሃፍ ምዕራፍ 5፡19 — 21 ላይ ተጠቅሷል። ታድያ እነዚህን እውነትኛ የመንፈስ ፍሬዎች ለማፍራት ምን ማድረግም እንዳለብን በዪሐንስ 15 ላይ በግልጽ ተጽፏል። የዪሐንስ 15 ዋና መልዕት እውነትኛ የመንፈስ ፍሬዎች ለማፍራት ከግንዱ መጣበቅ እንዳለብን ይተነትናል፣ ይህም ግንድ እራሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ተገልጿል። ከግንዱ መጣበቅስ ምን ማለት ነው እንዴት ነውስ የምንጣበቀውበዪሐንስ 15 ቁጥር 17 ላይ በግልጽ ተጽፏል፣ እንዲህም ይላል “እርስ በእርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትዕዛዜ ይህቺ ናት”። ስለዚህም በግንዱ ላይ መጣበቅ ማለት በፍቅር መኖር ማለት ነው፣ በዪሐንስ 15 ቁጥር 9 ላይ “አብ እንደ ወደደኝ ሁሉ እኔም ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ” ተብሎ ተጽፏል። ስለዚህ እውነትኛ የመንፈስ ፍሬዎችን ለማፍራት ፍቅር ቁልፉ ነው ማለት ነው። ለዚህም ነው ክርስቶስ እንዚህን ሁለት ነገሮች ባደረገበት ሳምንት በመስቀል ላይ የፍቅርን ጥግ ያሳየን። በዪሐንስ 15 ቁጥር 13 ላይ “ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።” ይላል። ዳዊትም በመዝሙር 63፡3 “ፍቅርህ ክህይወት ይበልጣልና ከንፈሮቼ ያመሰግኑሃል።” ይላል።

ክርስቶስም በማርቆስ 12፡28 – 34 ላይ ስለ ታላቁ ትዕዛዝ ይናገራል። “ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ከሁሉ የሚበልጠው ይህ ነው፤ እስራኤል ሆይ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤ አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ።’ ሁለተኛውም ይህ ነው፤ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።“ ከእነዚህም የሚበልጥ ትእዛዝ የለም።” በማቴዎስ 22፡40 ላይም “ሕግና ነብያት በሙሉ በነዚህ ሁለት ትዕዛዛት ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው።” ብሎ ኢየሱስ ይናገራል። ይህን ሲል ምን ማለቱ ነው፤ እግዚአብሔር አምላክህን ከወደድክ እንዲሁም ጐረቤትህን እንደራስህ ከወደድክ የቀሩትን ትዕዛዛት መፈጸም እጅግ በጣም ቀላል ነው ማለቱ ነው። ስለዚህ እውነተኛ ክርስትና ፍቅር ነው ብለን በአንድ ቃል መግለጥ እንችላለን። ጳውሎስ ስለ እውነትኛ የመንፈስ ፍሬዎች በገላትያ መጽሃፍ ምዕራፍ 5፡22 — 26 ላይ ሲተነትንም “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደነዚህ ያሉትንም የሚከለክል ሕግ የለም። የክርስቶስ ኢየሱስ የሆኑት ሥጋን ከክፉ ምኞቱና መሻቱ ጋር ሰቅለውታል። በመንፈስ የምንኖር ከሆን፣ በመንፈስ እንመላለስ። እርስ በርሳችን እየተጎነታተልንና እየተቀናናን በከንቱ ውዳሴ አንመካ።ል። ለዚህ ይሆናል ፍቅርን በአንደኝነት የጠቀሰው። ከዛም በበለጠ ጳውሎስ 1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 13 ላይ በጣም የተብራራ መልዕክት ስለ ፍቅር ጽፏል። 1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 13ትን በተለይ ከቁጥር 4 ጀምሮ ስታንቡት ፍቅር እውነትኛ የመንፈስ ፍሬዎች አጭቆ የያዘ የሁሉም ፍሬዎች መፈልፈያ እንደሆነ ልብ ማለት አያዳግትም። “ፍቅር ታጋሽ ነው፤ ደግሞም ቸር ነው። ፍቅር አይመቀኝም፤ አይመካም፤ አይታበይም፤ ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፤ ራስ ወዳድ አይደለም፤ አይበሳጭም፣ በደልን አይቈጥርም። ፍቅር ከእውነት ጋር እንጂ በዐመፅ ደስ አይሰኝም። ፍቅር ሁል ጊዜ ይታገሣል፤ ሁል ጊዜ ያምናል፤ ሁል ጊዜ ተስፋ ያደርጋል፤ ሁል ጊዜ ጸንቶ ይቆማል።

ፍቅር ከቶ አይወድቅም፤ ነገር ግን ትንቢት ቢሆን ይሻራል፤ ልሳንም ቢሆን ይቀራል፤ ዕውቀትም ቢሆን ይሻራል። ምክንያቱም የምናውቀው በከፊል ነው፤ ትንቢት የምንናገረውም በከፊል ነው። ነገር ግን ፍጹም የሆነው ሲመጣ በከፊል የነበረው ይሻራል።”
ስጠቀልለው እውነተኛ ክርስትና ማለት በፍቅር መመላለስ ማለት ነው። ወይም ደግሞ እውነተኛ ክርስትና በአንድ ቃል ግለጹት ከተባልን “ፍቅር” ብለን መግለጸ እንችላለን። ደግሞም ኢየሱስ ይህን ፍቅር በተግባር አሳይቶናል። በፍቅር በመኖር፣ እርስ በርሳችን በመዋደድ፣ አልፎም ጠላቶቻችንን በመውደድ ፍሬ ያለው እውነተኛ ክርስትናን እንኑር፣ አስመሳይ፣ ሁኔታንና አመቺ ጊዜን ተጠቅመን ግላዊ ጥቅምን ብቻ የሚሳድዱ ክርስቲያኖች ከመሆንም ከእንደዛ አይነቶቹም እንጠበቅ።

ጸሓፊውም እንዲህ አለው፤መምህር ሆይ፤ መልካም ብለሃል፤ እርሱ አንድ መሆኑን፣ ከእርሱም ሌላ አለመኖሩን መናገርህ ትክክል ነው፤ እርሱን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም አእምሮህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ መውደድ፣ እንዲሁም ባልንጀራህን እንደ ራስህ መውደድ ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች ይበልጣል።”“ ማርቆስ 12፡ 32 — 33

Thursday, March 29, 2018

ይድረስ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትራችን


 . . . ሥልጣን ከሰማያት እንደ ሆነ ካወቅህ . . . ትንቢት ዳንኤል 4፡26

ዳንኤል የንጉስ አማካሪ የነበረ በዘመኑ ከነበሩት አዋቂ ተብዬዎች በጥበብና በማስተዋል አስር እጅ የበለጠ ነበር። ትንቢት ዳንኤል 4 ላይ ለሚያማክረው ንጉስ ናቡከደናጾርም ህልም ሲፈታለት በአጽንዖት የሚነግረው አንድ ጉዳይ ነበር፣ ይህም ስልጣን “ከሰማይ እንደሆን እድዲያውቅ ነው”። ከዛም በመቀጠል “የደህንነትህ ዘመንህ ወይም በንግስና/በስልጣን የመቆየትህ ዘመን ይረዝም ዘንድ ኃጢአትህን በጽድቅ ፥ በደልህንም ለድሆች በመመጽወት አስቀር” ይለዋል።

በእኔ የግል አስተያየት በኢትዮጵይ ውስጥ የሰለጠነ የመንግስት አስዳደር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ የዳንኤልን ምክር የሰማም ሆን ያነበበ የአገር መሪ ኢትዮጵያ ነበራት ብዬ አላስብም። ሃይማኖትን ከስልጣን ጋር ቀላቅለው ያስተዳደሯት አፄዎችም ስዩመ እግዚአብሄር ብለው ተጠያቂነትን ከራሳቸው ለማውረድ እናም እድሜ ልክ ለመንገስ ተጠቀሙበት እንጂ ፣ በትክክል ትርጉሙ ገብቷቸው አልኖሩበትም። በዚህም ምክንያት አሁን ያለችውን ኢትዮጵያን አስረክበውናል። እግዚአብሄርን ፈርተው ፣ ሥልጣን ከሰማያት እንደ ሆነ አውቀው ቢመሩን ኖሮ ምንኛ በታደልን ነበር።

ብዙ ሰዎች ኢትዮጵያ ፈርጀ ብዙ ችግሮች ያሉባት ፣ እነዚህንም ችግሮች ለመፍታት አዳጋች እንደሆነ ፥ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖምያዊ እና ማህበራዊ ትንታኔዎችን በመስጠት ጭብጥ ያላቸው መረጃዎችን በማቅረብ ትንተናዎችን ሲያቀርቡ ይደመጣል። በእርግጥም ኢትዮጵያ ፈርጀ ብዙ ችግሮች ያሉባት ሃገር ለመሆንዋ የምንከራከርበት ጉዳይ አይደለም። ነገር ግን እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የምንጠቀመው ዘዴ ነው እንጂ ችግሮችን ለመፍታት አዳጋች የሚያደርገው ፣ በእኔ እይታ ለእነዚህ ፈርጀ ብዙ ችግሮች መፍትሔ ማምጣት ከባድ ነው ብዬ አላምንም።

 ዋናው የእኔ መልዕክት ለአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትራችን በስልጣን የመቆየትዎ ዘመን የተሳካና የረዘመ ይሆን ዘንድ እርስዎም ሆነ ካቢኔዎ ውስጥ የሚመርጧቸው ሰዎች እስከዛሬ የተሰራውን ኃጢአት በጽድቅ፥ እስከዛሬ የተሰራውን በደልንም ለድሆች በመቆርቆርና ፍትህን በማስፈን እንዲቀይሩ፤ በዚህም ውስጥ እግዚአብሄርን ፈርተው ፣ ሥልጣን ከሰማያት እንደ ሆነ አውቀው ቢመሩን ፣ ከባድ የተባለው ችግር በሰው ዓይን እንጂ በእግዚአብሄር ዓይን እጅግ ቀላል እንደሆነና፣ መፍትሔውንም እራሱ የሚፈሩት እግዚአብሄር በእጅዎ ይሰጥዎታ የሚል ነው። የጥበብ መጀመርያ እግዚአብሄርን መፍራት ነው ፤ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው። ምሳሌ 9፥10

ወደ ተጨባጭ ሁኔታዎች ስንመጣ ፣ በእኔ የግል አስተያየት የአገራችንን ችግሮች በሦስት እከፍላቸዋለሁ። 

1 ወጥ የሆነ መዋቅራዊ የሆነ አሰራር ማጣት በእንግሊዝኛው system የምንለው በተቀናጀ መልኩ አለመኖሩ፣ 
2 የትምህርት መዋቅራችን ወይም curriculum ገና ሀ ተብሎ የሰለጠነ የትምህርት አሰጣጥ ሲመጣ ጀምሮ የተበላሸ መሆኑ እና 
3 አገራችን ኢትዮጵያ በዘመኗ በሙሉ ይሄ ነው የተባለ የባህል አብዮት አለማካሄድዋ ናቸው። 

እነዚህ ሶስቱ በጥቅሉ ተጠያቂነት የጎደለው የመንግስት የስራ አስፈፃሚ እንዲፈጠር ፣ ለአገር ችግር መፍትሔ ሰጪ የፈጠራ ሰው innovative የሆነ የተማረ ሃይል እንዳይኖር እና የህብረተሰቡ የአስተሳሰብ አድማስ እንዳይሰፋ ያደረጉ ችግሮች ናቸው።እንዚህን ችግሮች ለመፍታትም መጠቅም ያሉብን መንገዶች እንደተለመደው ከላይ ወደ ታች ሳይሆን፤ ከታች ወደ ላይ መሆን ይገባዋል። ይህ ምን ማለት ነው፣ በተለምዶ የተማሩና ችግር ለመፍታት አቅም ያላቸውን ሰዎች critical thinkers and problem solvers በሚኒስትር ደረጃ አስቅምጦ መፍትሔ ማፈላለግ እሩቅ የማያስኬድና ፈጣን መፍትሔም ለማምጣት የማይበጅ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለማንሳት ወደድኩ። መዋቅራዊ የሆነ አሰራርንም ቢሆን ከታች ወደ ላይ ማለትም ከቀበሌ ወይም ከወረዳ ወደ አገር አቀፍ ማሳደግ፣ የተማሩና ችግር ለመፍታት አቅም ያላቸውን ሰዎች የቀበሌ እና የወረዳ መሪዎች በማድረግ የተማረውን እና ቀና የሆነውን የሰው ሃይል ለድሆችና ላልተማሩት ዕውቀቱን የሚያውልበትን መንገድ ማመቻቸት ግድ ይለናል። ትምህርት ቤቶችንና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ደግሞ ለውጣዊ progressive የሆነን ትምህርት በሂደት እዲያስተምሩና፣ በዘላቂነት ደግሞ ኢትጵያዊ የሆነ አዲስ የትምህርት መርሓ ግብር curriculum በመንደፍ አሮጌውን መቀየር ወሳኝ ነው። በአጭር ጊዜም መፍትሔያዊ የሆኑ እንቅስሴዎች እንዲዳብሩን የፈጠራ ማዕከሎችን innovation centers በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ እንዲቋቋሙ ማድረግና፣ መንግስት ከግል ተቋማት፣ ከከፍተኛ ትምህርትና አሁን በስራ ላይ ካሉ የምርምር ተቋማት ጋር በመሆን ፈጣን ሃገራዊ ችግር ፈቺ እና ፈር ቀያሽ ምርምሮችንና ጥናቶችን የሚያካሂድ ጠንካራ ተቋምን በአጭር ጊዜ ውስጥ ቢያቋቁም መልካም ነው የሚል ሃሳብ አለኝ።

ከሁሉ በላይ ይቅርታ የተሞላው፣ ያለፈውን ትተን ወደፊታችን ላይ ያሚያተስኩር፣ የግለሰብን መብት የሚያከብር እና ከቡድን አሳቢነት የሚገላግል፤ ፍቅርን ማዕከላዊ ያደረገ ርዕዮተ ዓለም ለምድራችን ያስፈልጋታል። የህግና የትዕዛዛት ሁሉ ማንጠልጠያ የሆኑትን ሁለቱን ትዕዛዛት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እንዝራ በማለት መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።

መልካም የአገልግሎት ዘመን እንዲሆንልሆ እየተመኝሁ እግዚአብሄር ፀጋና ጥበብ እንዲያበዛልዎ ፀሎቴ ነው። ስራው የእርስዎ ብቻ ሳይሆን የሁላችን ስለሆነ ሕዝቡንም በቀናነት መሪያችንን እያገዝን የበኩላችንን ድርሻ እንፈጽም ብዬ አሳስባለሁ።   

ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው፤ ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል፤ ይህም፣ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድየሚለው ነው፤ ሕግና ነቢያት በሙሉ በእነዚህ ሁለት ትእዛዛት ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው።” ማቴዎስ 22፡ 37 — 40