Wednesday, April 8, 2020

በዚህ ጊዜ ምን እናድርግ?

ከብዙ ዝምታ በኋላ ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ የተነሳሁት ጥልቅ የሆነውን የዓለም ጉዳይ የተረዳን ስላልመሰለኝ ነው። በተለይም የኮሮና ቫይረስ ክትባት አፍሪካ ውስጥ ይሞከር የሚለው ጉዳይ ሳይታሰብ አፈትልኮ ሲወጣ አሁን ዝምታው ይብቃኝ ብዬ ነው።

በመጀመርያ ኮሮና ቫይረስ ምንድን ነው? የሚለውን ባጭሩ ላብራራ። ኮሮና እንደ ማንኛውም ቫይረስ፣ ቫይረስ ነው። ቫይረስ ማለት ደግሞ ከተክልም፣ ከእንስሳትም ሆነ ከባክቴርያ ዘር ውጭ የሆነ፣ ሕይወት ካላቸው ነገሮች ጋር የማይመደብ ከሚኖርበት ሕይወት ያለው ነገር ውጭ ሕይወት የለሽ የሆነ በአይን የማይታይ “ነገር” ነው። በተራቀቀው የማይክሮ ባዮሎጂ (Microbiology) አገላለጽ ቫይረስ ማለት የኒኩሊክ  አሲድ(Nucleic acid)፣ የዘረ መል (DNA) ወይም የቅድመ ዘረመል (RNA) እና የፕሮቲን (protein) ቅንብር ሲሆን፤ መኖርያ የሚሆነው ሕዋስ ሲያገኝ ውስጡ ባለው በኑክሊክ አሲድ አማካኝነት አዳዲስ የዘረ መል ቅንብር ያላቸው ሌሎች ቫይረሶችን ማባዛት ይጀምርና እነዚህም የተባዙት ቫይሪኦን (Virion) የተሰኙ ኢንፌክሽን የማሰከተል አቅም ያላቸው ተውሃሶች፣ የሚኖሩበትን ሕዋስ በፍጥነት ይወሩታል። ቫይረሶች በአጠቃላይ ያለ ሕዋስ (አትክልት፣ ሰው፣ እንስሳ) ረጅም ዕድሜ የላቸውም፣ እንዲሁም በራሳቸው የሚያስከትሉት ጉዳትም እምብዛም የሌለ ሲሆን ይልቁንም ቫይረሱ የሚኖርበት ሕዋስ የቫይረሱን ወረራ ለመከላከል በሚያደርገው ትንቅንቅ (immune response) የተለያዩ የህመም ምልክቶችን ማየት እንጀምራለን፤ ለምሳሌ በዋነኝነት ትኩሳት። በዚህ መልኩ ሰውነታች በራሱ የመከላከል እርምጃ የቫይረሱን መራባት ይገታውና ከከፋ ኢንፌክሽን ያድነናል።

ወደ ኮሮና ስንመጣ ኮቪድ—19 የተባለው ቫይረስም እንዲሁ እንደሌሎቹ ቫይረሶች የራሱ የሆነ ሕይወት የሌለው “ነገር” ነው። ነገር ግን አዲስና ከዚህ በፊት ከነበሩት የቫይረስ ዓይነቶች የሚለይበት የራሱ የሆነ መለያ ያለውና እስካሁን የሰው ልጆች ከጋጠማቸው ቫይረሶች የተለየ ስለሆነ፣ የሰውነታችን የመከላከያ ስርዓት እምብዛም ስለማያውቀው፣ ሰውነታችን የመዋጋት አቅሙን ጨምሮ የራሱን የሰውነት ክፍሎች የሚጎዳበት ሁኔታ ይፈጠርና፣ በተለይም ኮቪድ—19 የሚያጠቃው የመተንፈሻ አካላትን ስለሆነ፣ ከሳምባ ጋር ተያይዞ የመተንፈስ አቅምን ሲያሳጥርና የተለመደውን የኦክሲጅን ኡደት ሲዛባ ወደ ከፋ አደጋ ይሻገራል። ይህ ቫይረስ አዲስና ባልተለመደ መልኩ የተለያዩ ቁሶች ላይ በሕይወት የመቆየት አቅሙ ከፍተኛ ስለሆነ፣ በቤተ ሙከራ ውስጥ የተፈጠረ ቫይረስ ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር ያስችላል። የግሌ መላምትም ይህ ቫይረስ በተለይ ብረት ነክ ነገሮች ላይ በሕይወት የመቆየት አቅሙ ከፍተኛ መሆኑንና በአየር ላይ እስከ 8 ሜትር የመንሳፈፍ ባህሪው ሰው ሰራሽ ቫይረስ ይሆናል የሚል ነው።

ስለዚህ ምን እናድርግ? የውን ከመመለሳችን በፊት ቫይረስ ምን እንደሆነና የኮሮናን ባህርይ ደግሞ ማየታችን የሚጠቅመን፣ ከዚህ ወረርሽኝ ኢትዮጵያን ከከፋ አደጋ ለማዳን ምን ማድረግ ይቻል ነበር የሚለውንና፣ አሁንስ ምን እናድርግ የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ነው።

እንደኔ ሃሳብ ምንም እንኳን የዘገየ አስተያየት ቢሆንም፣ እንደ አገር ማድረግ የነበረብን የመንገደኞች አየር በረራዎችን ከአንድ እስከ ሦስት ወር ድረስ መዝጋት ይገባን ነበር ብዬ አስባለሁ። የአየር መንገዱንም አሁን ለኮረና መከላከያ ተብሎ የተሰበሰበው ገንዘብ በድጎማ መልክ በመስጠት ኪሳራውን መሸፈን ይሻል ነበር የሚል አቋም ነው ያለኝ። በሌላ አማራጭም በረራዎችን መዝጋት ኢኮኖሚው ላይ ከባድ አደጋ አለው ከተባለ፣ አሁንም ቀላሉ እና አዋጩ መንገድ ይሆን የነበረው በጣም ዘግይቶ የተጀመረው ወደ አገር የሚገቡ መንገደኞችን ለይቶ ለ14 ቀናት መከታተል ቀደም ብሎ ቢጀመር ነበር። ነገር ግን እነዚህ ሁለት ነገሮች በጊዜው አልተተገበሩም።

አሁንም እስኪ ተመልሰን ስለ ቫይረሱ እናንሳ። ከላይ እንዳልነው ቫይረስ የራሱ የሆነ ሕይወት የሌለው “ነገር” ነው፣ ስለዚህ አገራችን የሌለን ቫይረስ በእርግጥም ይዞ የሚመጣው ቫይረሱ ካለበት ቦታ የመጣ ሰው ብቻ ነው።

አሁን ታድያ ምን እናድርግ? እንደ አገር ዋነኛ ማድረግ ያለብን ነገር ሙሉ ለሙሉ የሰዎችን እንቅስቃሴ ማቆም ብቻ ነው። ይህ እርምጃ ለእኛ ዓይነቱ ደሃ አገር አዋጭ አይደለም የሚሉ ሃሳቦች ይነሳሉ። አሁንም በአጽንኦት የምመክረው ነገር፣ የዕለት ጉርሻውን እያሳደደ የሚኖረው ምን ይሁን፣ ጎዳና ተዳዳሪዎችስ፣ የሥርዓተ አልበኝነቱስ ነገር እና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ። አንድ ነገር ግን ማየት ያልቻልነው እነዚህ ሰዎች በረሃብ ያልቃሉ ብለን ነው የፈራነው እንጂ እንቅስቃሴዎችን ባለመግታታችን በበሽታ ማለቃቸውን አናስቀረውም። መንግስት እስካሁን የወሰዳቸው እርምጃዎች ያላዋቂ ሳሚ ዓይነት ሆነውብኛል። ለተወሰነ ጊዜ እንቅስቃሴ ማገድ ስንል ምን ማለት እንደሆነ የፖለቲካ ሹመኞቹ የገባቸው አይመስሉም። የሰዎች እንቅስቃሴ ሲቆም የቫይረሱም እንቅስቃሴ ይቆማል፣ ቫይረሱ ባለበት ሲቆይ ደግሞ ይሞታል። ቫይረሱ የያዛቸው ሰዎች ደግሞ ግፋ ቢል ጥቂት ሰዎች ላይ ብቻ አስተላልፈው የበሽታው ምልክት ይታይባቸውና፣ እነርሱም ሆኑ ከእነርሱ ጋር የተነካኩ ሰዎች ተለይተው ጥብቅ ሕክምና ይደረግላቸዋል፣ በዚህም ቫይረሱን እኛን ከመቆጣጠሩ በፊት እኛ እንቆጣጠረዋለን።

ከዚህ ክስተት ምን እንማር? ከዚህ ክስተት እምናየው ድህነታችን የኢኮኖሚ ብቻ አለመሆኑን፣ ይልቅም የአስተሳሰብ መሆኑን ነው። አሁን ዞር ብለን እስከዛሬ የኖርንበትን የአኗኗር ዘይቤ የምናስተውልበት ጊዜ መሆን ይገባዋል። እስከዛሬ ፖለቲካ አገሪቷን ሲመራ ነበር፣ የኛው ፖለቲካ ደግሞ የሚመራው በጥቅመኛና አስመሳይ ሰዎች እንጂ በዕውቀት አይደለም። ዛሬ ላይ ቆመን ችግሩን እያየን መድሐኒት አገኘን እያልን የምንዘባበትበት ጊዜ የለንም፣ እስከዛሬ በሰላሙ ጊዜ እንስራ የሚሉ ሰዎች የሚገፉበትን ውጤት አሁን እያየነው ነው። ሹመት በዕውቀት ሳይሆን በፓርቲ አባልነትና በትውውቅ ስንሰጥ ከርመን፣ ዛሬ በሚያሳፍር ሁኔታ ምን መወሰን እንዳለብን ቆርጦ የሚናገር አዋቂና ደፋር ባናገኝ አይገርምም። እስካሁን በብድርም ይሁን በልገሳ ያገኘናቸውን ገንዘቦች በማይረባ ዲስኩርና ስብሰባ ስንበትናቸው ከርመን፣ አሁን የሳይንስና ምርምርን ፋይዳ በቁጭት እያየነው ይሆናል። ትላንት በጥቅም ይዞ የሚያጎበድድና ሁሉን እሺ የሚል ለሆዱ የሚሞት ሰውን እየቀጠሩ ወንበራቸውን ያስጠበቁ፣ ዛሬ መፍትሄ ሲፈለግ ድምጻች አጥፍተው ወደ ጉድጓዳቸው ገብተዋል። ዛሬ እስኪ እስካሁን የኖርንበተን ዘይቤ ዘወር ብለን እንይና ወደ እውነታው እንመለስ። ዕውቀት፣ተጠያቂነትንና ለእውነት ፊት ለፊት መጋፈጥ ምን ያህል ከእንደዚህ ዓይነቱ የጉድ ጊዜ ሊታደጉን ይችሉ እንደነበር ዞር ብለን እናስተውል። በግሌ እንስራ ኧረ እባካችሁ እንስራ እያልኩ ሃገሬ ከመጣሁ በኋላ በሳይንሱ ዘርፍ ብዙ ታግያለሁ፣ የሚገርመው ግን የተባልኩት አርፈህ ደሞዝህን እየበላህ ኑር፣ ብር አልተከለከልክ የምን መሟገት ነው ካልሰራሁ ብለህ፣ አግኝተህ ነው ሳትሰራ ደሞዝ ማግኘት ነበር። መቼም አሁን የእንስራ ንዝነዛዬና መጋፈጤ ይገባቸዋል ብዬ አስባለሁ።

አገሪቷንም ለሚመሩት የማስተላልፈው፣ አሁን ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት በዕውቀት ላይ የተመሰረት ውሳኔ እንጂ በመልካም ቃል የታጀበ ዓረፍተ ነገርና ፖለቲካዊ ሃተታ አይደለም። ሕዝቦች በአሰቃቂ ሁኔታ በበሽታ እንዳያልቁ በፍጥነት በየቀበሌው የችግረኞችና አቅም የሌላቸውን ወገኖች አድራሻ ለይቶ፣ ለነርሱም በተወሰነ ቀን ራሽን የማድረስ መርሃ ግብር አውጥቶ በተቻለ ፍጥነት ወደ ሙሉ እንቅስቃሴን ማቆም መግባት ይበጀናል።

በነገራችን ላይ ትምህርት ቤትን ዘግቶ፣ ስራን ከፍቶ፣ ከዛም የመንግስትን ስራ ዘግቶ የግል ድርጅቶች ከፍቶ፣ ገበያው ደርቶ ትራንስፖርት እንደወትሮው ቀጥሎ ባለበት ሁኔታ አገሪቷ አይደለም ከወረርሽኙ ልትድን ቀርቶ ከሁለት ያጣች የሚያደርግ ውሳኔ መሆኑን ሳልጠቅስ አላልፍም። መካሪም ተመካሪም የሌለባት አገር ይሏል ይሄ ነው። ከሁሉም ግን የሚያስፈራኝ የአፍሪካ መሪዎች ምዕራባውያኑን ለማስደሰትና እርጥባንን ለማግኝት ብለው ልምና በለመደው ባህርያቸው ለምነው የክትባቱን ስራ በአፍሪካ እንዳያስጀመሩት ብቻ ነው።

እግዜር ምህረቱን ለዓለም ሕዝብ ሁሉ ያውርድልን ለኛም የሚያስብ አእምሮ ይስጠን።
አማኑኤል ብሩ ዶ/ር