Tuesday, May 29, 2018

ቀላል ግን የማይቃለል ደግሞም ከባድ ግን የማይካበድ


“እናንተ ሸክማችሁ የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀነበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሁት ነኝና ፤ ለነፍሳችሁ ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬም ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነውና።” ማቴዎስ 11፡28 — 29

ክርስቲያን ለመሆን በጣም ቀላል ነው። ይኽውም ፈላስፋ፣ የተማረ፣ ብዙ ያነበበ፣ ብዙ ሰው ማወቅ ወይ ደግሞ ሌላ ሌላ መሆን አያስፈልግም። በቃ ክርስቶስ የእግዚአብሄር ልጅ መሆኑን ብናምን በአፋችንም ብንመሰክር ድነን ክርስቲያን መሆን ብቻ ነው። የወህኒ ቤቱ ጠባቂ በሓዋርያት ስራ ምዕራፍ 16 ቁጥር 30 ላይ እነ ጳውሎስን “እናንተ ሰዎች እድን ዘንድ ምን ላድርግ” ሲላቸው የነገሩት እጅግ በጣም ቀላል ነገር ነው፣ “በጌታ በኢየሱስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ” በቃ ሌላ የተወሳሰበ ነገር የለውም። ወንጌል ውስብስብ አይደለም፣ ወንጌል ቀላል ነው። ጌታ ኢየሱስም ለዚህ ነው “ወደ እኔ ኑ” ብቻ ያለው። ወደ እኔ እንደዚህ ወይም እንደዚያ ሆናችሁ ኑ አላለም እንዳላችሁ ከነ ከበዳችሁ ነገር ከነ ድካማችሁ ኑ ነው ያለን። ያልተወሳሰበ ቅድመ ሁኔታ የሌለበት ጥሪ።  ማወቅ ያለበን አንድ ነገር ብቻ ነው፤ ዕረፍት መፈለጋችንን ብቻ። ሸክማችሁንና ደከማችሁ እኔ ላይ ጣሉትና እኔ የማሸክማችሁን ቀንበርና ሸክም ተሸከሙ፣ የእናንተን በእኔ ለውጡ ይለናል። ማወቅ ያለብን ዋና ነገር ክርስቶስ ጋ ስንመጣ ሸክማችን የከበደንና ደካሞች መሆናችንን በደንብ ማወቅ ከዛም የኛን ጥለን እርሱ የሚያሸክመንን ደስ ብሎን መሸክም እንዳለብን ነው። የራሳችንን ሸከምና የእርሱን ሸክም አንድ ላይ ይዘን መሄድ እንደማንችል ልብ ብለን መገንዘብ ይኖርብናል። ክርስትና ውሳኔን የሚጠይቅ ተረድተነው የምንገባበት የግል ጉዳይ ነው፤ ማቴዎስ 8፡ 18 — 22 እና ሉቃስ 14፡25—35። በቡድን የምንወስነው፣ ሌላው ስለገባ የምንገባበት ወይ ደግሞ ወላጆቻችን ስለሆኑ እኛም የምንሆነው ነገር እንዳይደለ ማወቅ ግድ ይለናል። የደከምን የከበደን ሁሉ ወደ እርሱ ስንመጣ ዕረፍት እናገኛለን፣ ዕረፍቱ ግን የሚገኘው መስቀሉ ስር ሸክማችንን ከጣልን በኋላ ከእርሱ ስንማር ነው። እርሱ የሚያሸክመንን ቀንበር መያዝ የምንችለው ከእርሱ ስንማር ነው። የእርሱን ማንነት ስናውቅና ስንቀበለው ዕረፍት እናገኛለን። ክርስቶስ ከእኔ የምትማሩት “የዋህነትና ትህትና” ነው ይለናል።

በዚህ ዓለም ስንኖር ክርስቲያን ለመሆን ቀላል፤ ነገር ግን ክርስቲያን መሆን ከባድ ነው። ይህን ያልኩበትም ምክንያት የክርስቶስን ህይወትና አስተምሮ ስናይ ከምንኖርባት ዓለም አካሄድ ጋር የማይገናኝ እንዳውም የሚቃረን ሆኖ እናገኘዋለን። ክርስቶስን ከእኔ ተማሩ የሚለንን እስኪ እንይ። የማቴዎስ ወንጌል ላይ ከምዕራፍ 5 እስከ 7 ክርስቶስ የእርሱ የሆኑት ወይም የእርሱን ቀንበር የተቀበሉት ምን ዓይነት ሰዎች ሊሆኑ እንደሚገባቸው ያስተምራል። በምዕራፍ 5 የተራራው ስብከት ከሚባለው ተነስቶ ስለ መግደል፣ ሰለ ማመንዘር፣ ስለ መሓላ፣ ስለ መቀበል፣ ስለ ምጽዋት አሰጣጥ፣ ስለ ጸሎት፣ ስለ ሀብት፣ ስለ ጭንቀት እና ሌሎች ነገሮች ያስተምራል። በእውነት ለመናገር ለመተግበር ከባድ የሆኑ አስተምህሮዎች ናቸው። ከባድ የሆኑበትም ምክንያት ከዚህ ዓለም የኑሮ አካሄድ ጋር ስለሚጣረሱ ነው። ታድያ ክርስትና ዕረፍት የሚሰጥና ሸክሙ ቀሊል ከሆነ፣ ለምን ስንተገብረው ይከብዳል፣ ለምን እንሰደድበታለን ለምንስ መከራ እንቀበልበታለን ይህ ጥያቄ ትክክለኛ ጥያቄ ነው። ምንአልባትም ሁላችንም በህይወታችን ውስጥ የሚሆነውን አይተን ደጋግመን ጠይቀን ይሆናል።

ለዚህም ነው ርዕሱን “ቀላል ግን የማይቃለል ደግሞም ከባድ ግን የማይካበድ” ያልኩት። ይህን ሁለት ፈርጅ ያለውን ሃሳብ ከመተንተኔ በፊት አንድ እውነታ ላካፍላችሁ። ኢየሱስ ለፈሪሳውያን ታልፎ ከተሰጠ በኋላ በስቅለት ቀን ከባድ ስቃይ ተቀብሏል። በሁለት አበይት ምክንያት፥ 1 እኛን ከአብ ጋር ሊያስታርቅ፣ 2 ከዓለም ጋር የማይስማማ ትምህርት ስለነበረው ነው። ስለ ክርስቶስ የመስቀል ስቃይ ያጠኑ የመጽሓፍ ቅዱስ ምሁራን በስቅለት ቀን ኢየሱስ 39 ጊዜ ተገርፏል ይላሉ፣ በጣም ሲያብራሩትም 13 በደረቱ ላይ  26 ደግሞ  በጀርባው ላይ በጅራፍ ተገርፏል ይላሉ። በዘመኑ በአይሁድ ህግ ትልቁ ግርፋት 40 ነበረ። አንዳንድ ጥናቶች ላይ ኢየሱስ 100 ጊዜ እንደተገረፈ ይናገራሉ። ይኽውም በጊዜው የነበረው የሮማውያን ህግ ምንም የግርፋት ቁጥር ልክ ስላልነበረው፣ እናም የክርስቶስ አስከሬን ተከፍኖበት የነበረውን አሁን ድረስም በጣልያን ቱሪን የሚገኘውን ጨርቅ “Shroud of Turin” ያጠኑ ሰዎችም የሚስማሙበት 100 መገረፉን ነው። ከዛም በላይ ክርስቶስ ዋና የምንላቸው በካቶሊኩም ዓለም “አምስቱ ቅዱስ ቁስሎች” ተብለው የሚታወቁ ቁስሎችን የቆሰለበት የስቅለትን ጊዜ ስናስብ ብሎም ከነ ግርፋቱ ለስድስት ሰዓታት በመስቀል ላይ መቃተቱን ስናስብ፤ ክርስትና ለመቀበል ቀላል ስለሆነ ክርስቶስ ለኛ ዕረፍትን ለመስጠት የከፈለው ግን ቀላል እንዳልሆነ ማወቅ ግድ ይለናል። ለዚህ ነው ክርስትና ቀላል ግን የማይቃለል የሆነው። ደግሞም እርሱ ለኛ ብሎ ያሳለፈው መከራና ስቃይ ሲገባን፣ እኛ ለእርሱ ብለን የምንቀበለውን መከራ እንዳናካብድ ግድ ይለናል። ስለዚህ ክርስትና ከባድ ግን የማይካበድ የሆነው። ከዛም አልፈን የአዲስ ኪዳን ሐዋርያት ስለ ክርስቶስ ያሳለፉትን መከራ እና ስቃይ ስናይ ደግሞም በዚህ ዘመን በክርስቶስ ምክንያት ክርስቲያኖች የሚያልፉበት መከራ በደንብ ብናጤነው፣ በዕውነት እኛ የምናልፍበት መከራ የማይካበድ መሆኑ ይገባናል። 2 ቆሮንቶስ 11፡16 — 33 ላይ ጳውሎስ በዝርዝር ስላለፈበት መከራ ጽፏል። ለጢሞትዮስም ሲመክረው “በእርግጥም በክርስቶስ ኢየሱስ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት መኖር የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።” ይለዋል። እንዲሁም 2 ቆሮንቶስ ላይ “ስለ ክርስቶስ በድካም፣ በስድብ፣ በመከራ፣ በስደትና በጭንቀት ደስ የምሰኘው ለዚህ ነው፤ ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝና።” ይላል። ጴጥሮስም እንዲሁ በመጀመርያ መልዕክቱ ምዕራፍ 3፡18—22 እና ምዕራፍ 4፡12—19 ክርስቲያን በመሆን ስልሚደርስ መከራ ይነግረናል።

በትንሳኤው ደግሞ የገለጠልን፣ በብዙ ስቃይ እና መከራ ያለፈው ይህ ጌታ በቃ አለቀ አሸነፍነው ሲሉ ድንገት ሳያስቡት በሶስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ የሲኦልን መክፈቻ ይዞ ተነሳ። ምን መከራው ቢበዛ፣ ስቃዩ የማያልፍ ቢመስል፣ ተሸነፈ አለቀለት የሚያስብል ሁኔታ ቢፈጠር ድል አድራጊው ጌታ በሰዓቱ ጊዜውን ጠብቆ በሶስተኛው ቀን በድል እንደተነሳ፣ እርሱን ለማክበር ብለው በመከራ ለሚያልፉትም በጊዜውና በሰዓቱ ሳይዘገይ ወይም ሳይፈጥን በትንሳኤው ሃይል ይመጣላቸዋል። ጳውሎስ አሁንም በ 2 ቆሮንቶስ 4 ላይ “ከየአቅጣጫው ብንገፋም አንንኮታኮት፤ ግራ ብንጋባም ተስፋ አንርቆጥም፤ ብንሰደድም ተጥልን አንቀርም፤ መትተው ቢጥሉንም አንጠፋም” ያለው። ለእርሱ ከተገዛንና የዓለምን ብልጭልጭ ነገር ንቀን በመንፈሳዊ ህይወታችን እርሱን ለመምሰል ከቆረጥን ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እንወቅ።

ስለዚህ ክርስትና ቀሎብን ከሆነ መስቀሉን እንይ፤ ደግሞም ክርስትና ከብዶብንም ከሆነ መስቀሉን እንይ። የዛን ጊዜ ቀላል ግን የማይቃለል ደግሞም ከባድ ግን የማይካበድ ይሆንልናል። ክርስትና ከድል ጀምረን የምንኖረው እንጂ ድል ለማድረግ ገና በራሳችን የምንታገለው እንዳልሆነ እንዲገባን ትንሳኤውን እናስተውል። ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ ብሎናል፥ “በእኔ ሰላም እንዲኖራችሁ፣ ይህን ነግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ ኧለባችሁ፤ ነገር ግን አይዟችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” ማቴዎስ 5፡11 — 12