በማግሥቱ ከቢታንያ ሲወጡ ኢየሱስ ተራበ። እርሱም ቅጠል ያላት የበለስ ዛፍ ከሩቅ
አየ፤ ምናልባት ፍሬ ይገኝባት እንደሆነ ብሎ ወደ እርሷ መጣ፤ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። ከዚያም
ዛፏን፣ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ፍሬ ከአንቺ አይብላ” አላት። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲናገር ሰሙ። ወደ
ኢየሩሳሌምም መጡ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፣ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያስወጣ ጀመር። የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛና የርግብ
ሻጮችን መቀመጫ ገለባበጠ፤ ማንም ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳያልፍ ከለከለ። ሲያስተምራቸውም፣
“ ‘ቤቴ
ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት!” አላቸው። የካህናት አለቆችና
ጸሐፍትም፣ ይህን ሲሰሙ እንዴት እንደሚያጠፉት መንገድ ይፈልጉ ጀመር፤ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ በመገረማቸው ፈርተውታልና። በመሸም
ጊዜ ከከተማዪቱ ወጥተው ሄዱ። የማርቆስ ወንጌል 11 ፥ 12 — 19
በዚህ ክፍል ውስጥ ኢየሱስ ሁለት ነገሮችን ሲያደርግ እንመለከታለን 1 ፍሬ ያላፈራችውን
የበለስ ዛፍ ሲረግማትና 2 ለሁለተኛ ጊዜ ቤተ መቅደስ ውስጥ ገብቶ ነጋዴዎችን ሲያስወጣ እንመለከታለን። ሁለቱንም ድርጊቶች የፈጸመው
የህማማት ሳምንት ተብሎ በሚገለፀው ሳምንት ውስጥ ነው። ሁለቱም ድርጊቶች አንድ አይነት ሃሳብ አላቸው ብዬ አምናለሁ። እስኪ ሁለቱንም
በተራ እንመልከታቸው።
1 ፍሬ ያላፈራችውን የበለስ ዛፍ፦ የበለስ ዛፍ በተፈጥሮው ሰፋፊ ቅጠሎች
ያሉት፣ ስሩ በጣም ጥልቅና ውሃን ከሩቅ ቦታ ስቦ ማምጣት የሚችል ሲሆን፣ ፍሬውና ቅጠሉ እኩል ነው የሚወጡት። በብሉይ ኪዳንም የበለስ
ዛፍ የእስራኤል ብሔራዊ ምልከት ነበር። ክርስቶስ ፍሬ አገኛለሁ ብሎ ወደ ዛፏ የተጠጋው ቅጠሎቿን ከሩቅ አይቶ ነበር። ነገር ግን
ፍሬ አጥቶባት ዳግመኛ እንዳታፈራ ሲረግማት እናያለን። በማግስቱ ጠዋትም ደቀ መዛሙርቱ ደርቃ አይተዋት ተገርመው ሲጠይቁት ስለ እምነት
ሲያስተምራቸው በሚቀጥለው ክፍል ላይ እናያለን። እዚህ ክፍል ላይ የምንታዘበው የበለስ ዛፍዋን አስመሳይነት ነው። ፍሬ እንዳለው
የበለስ ዛፈ በቅጠሎች ብቻ የታጀበች ነገር ግን ምንም ፍሬ የሌላት። ከዚህም ጋር ሌላ ተያይዞ የምናየው ጠቅላላ እስራኤል እንደ
መንግስት ፍሬ አልባ ከሃይማኖተኝነት በቀር መንፈሳዊ መካን እንደሆነች በምሳሌአዊ ዘይቤ የሚያስረዳ ድርጊት ኢየሱስ እንደተናገረ
የሚገልጽም አሉ።
2 የክርስቶስ ቤተ መቅደሱ ማንፃት፦ ቤተ መቅደሱ የፋሲካ በዓል በመድረሱ
ብዙ ሰዎች የመንፃት ስርዓትን ለመፋጸም የሚመጡትን ሰዎች በማሰብ በቤተ መቅደሱ አካባቢና ውስጥ ይሸጡና ገንዘብ ይለውጡ ነበር።
እነዚህ ነጋዴዎች የህዝቡን ልብ ያወቁና ጊዜውንም ተጠቅመው ብዙ ትርፍ ለግላቸው ሰብስበው ለመሄድ የመጡ እንጂ፣ ለህዝቡ ወይም ለእግዚአብሔር
ቤት አስበው የመጡ እንዳልነበሩ በግልጽ ይታያል። ቤተ መቅደሱንም ካፀዳ በኋላ ኢየሱስ ቤተ መቅደሱን ለትክክለኛ ተግባር ሲያውለው
እናያለን፣ ይኽውም ለማስተማርና እውነተኛ ፈውስ የሚፈልጉን በነፃ መፈወስ ነበር። ማቴዎስ 21 ፥ 12 — 15 ይመልከቱ።
እነዚህ ሁለት የኢየሱስ ድርጊቶች አስመሳይ የሆነ ወይም እውነታኛ ያልሆነን ክርስትና
ከሩቅ በሚታዪ አማላይና ሃይማኖታዊ ነገሮች የታጀበ ነገር ግን ሲጠጉት ፍሬ ቢስ የሆነና፣ ሁኔታንና አመቺ ጊዜን ተጠቅሞ ግላዊ ጥቅምን
ብቻ የሚሳድዱትን እየተቃወመ እንደሆነ ያሳዪናል። እንግዲህ ይህን ነገር ወደ ራሳችን፣ ወደ ቤተክርስትያናችን፣ ወደ ሃገራችንና ብሎም
ወደ ዘመናችን ስናመጣው እንዲህ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ፍሬ ያለው እውነተኛ ክርስትያን ነኝን? ሁኔታንና አመቺ ጊዜን ተጠቅሜ ግላዊ ጥቅሜን ብቻ የሚሳድድ ነኝን?እውነትኛ
ፍሬ ያለው ክርስቲያን አስመሳይና ሁኔታንና አመቺ ጊዜን ተጠቅሞ ግላዊ ጥቅምን ብቻ የሚሳድድ ሊሆን በፍፁም አይችልም። እውነትኛ የመንፈስ ፍሬዎች በገላትያ መጽሃፍ ምዕራፍ 5፡22 —
26 ላይ ተጠቅሷል። የሥጋ ፍሬዎችም እነደዚሁ በገላትያ መጽሃፍ ምዕራፍ 5፡19 — 21 ላይ ተጠቅሷል። ታድያ እነዚህን እውነትኛ
የመንፈስ ፍሬዎች ለማፍራት ምን ማድረግም እንዳለብን በዪሐንስ 15 ላይ በግልጽ ተጽፏል። የዪሐንስ 15 ዋና መልዕት እውነትኛ የመንፈስ
ፍሬዎች ለማፍራት ከግንዱ መጣበቅ እንዳለብን ይተነትናል፣ ይህም ግንድ እራሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ተገልጿል። ከግንዱ መጣበቅስ ምን
ማለት ነው? እንዴት ነውስ የምንጣበቀው?በዪሐንስ 15 ቁጥር 17 ላይ በግልጽ
ተጽፏል፣ እንዲህም ይላል “እርስ በእርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትዕዛዜ ይህቺ ናት”። ስለዚህም በግንዱ ላይ መጣበቅ ማለት በፍቅር መኖር
ማለት ነው፣ በዪሐንስ 15 ቁጥር 9 ላይ “አብ እንደ ወደደኝ ሁሉ እኔም ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ” ተብሎ ተጽፏል። ስለዚህ እውነትኛ
የመንፈስ ፍሬዎችን ለማፍራት ፍቅር ቁልፉ ነው ማለት ነው። ለዚህም ነው ክርስቶስ እንዚህን ሁለት ነገሮች ባደረገበት ሳምንት በመስቀል
ላይ የፍቅርን ጥግ ያሳየን። በዪሐንስ 15 ቁጥር 13 ላይ “ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።”
ይላል። ዳዊትም በመዝሙር 63፡3 “ፍቅርህ ክህይወት ይበልጣልና ከንፈሮቼ ያመሰግኑሃል።” ይላል።
ክርስቶስም በማርቆስ 12፡28 – 34 ላይ ስለ ታላቁ ትዕዛዝ ይናገራል። “ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ከሁሉ የሚበልጠው ይህ ነው፤ እስራኤል ሆይ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤ አንተም
ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣
በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ።’ ሁለተኛውም ይህ ነው፤ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።“ ከእነዚህም የሚበልጥ ትእዛዝ የለም።”
በማቴዎስ 22፡40 ላይም “ሕግና ነብያት በሙሉ በነዚህ ሁለት ትዕዛዛት ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው።” ብሎ ኢየሱስ ይናገራል። ይህን
ሲል ምን ማለቱ ነው፤ እግዚአብሔር አምላክህን ከወደድክ እንዲሁም ጐረቤትህን እንደራስህ ከወደድክ የቀሩትን ትዕዛዛት መፈጸም እጅግ
በጣም ቀላል ነው ማለቱ ነው። ስለዚህ እውነተኛ ክርስትና ፍቅር ነው ብለን በአንድ ቃል መግለጥ እንችላለን። ጳውሎስ ስለ እውነትኛ
የመንፈስ ፍሬዎች በገላትያ መጽሃፍ ምዕራፍ 5፡22 — 26 ላይ ሲተነትንም “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣
ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት
ነው። እንደነዚህ ያሉትንም የሚከለክል ሕግ የለም። የክርስቶስ ኢየሱስ
የሆኑት ሥጋን ከክፉ ምኞቱና
መሻቱ ጋር ሰቅለውታል። በመንፈስ የምንኖር ከሆን፣ በመንፈስ እንመላለስ። እርስ በርሳችን እየተጎነታተልንና እየተቀናናን በከንቱ ውዳሴ አንመካ።” ይላል። ለዚህ ይሆናል ፍቅርን በአንደኝነት የጠቀሰው።
ከዛም በበለጠ ጳውሎስ 1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 13 ላይ በጣም የተብራራ መልዕክት ስለ ፍቅር ጽፏል። 1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 13ትን በተለይ
ከቁጥር 4 ጀምሮ ስታንቡት ፍቅር እውነትኛ የመንፈስ ፍሬዎች አጭቆ የያዘ የሁሉም ፍሬዎች መፈልፈያ እንደሆነ ልብ ማለት አያዳግትም።
“ፍቅር ታጋሽ ነው፤ ደግሞም ቸር ነው። ፍቅር አይመቀኝም፤ አይመካም፤ አይታበይም፤ ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፤ ራስ
ወዳድ አይደለም፤ አይበሳጭም፣ በደልን አይቈጥርም። ፍቅር ከእውነት ጋር እንጂ በዐመፅ ደስ አይሰኝም። ፍቅር ሁል
ጊዜ ይታገሣል፤ ሁል ጊዜ ያምናል፤ ሁል ጊዜ ተስፋ ያደርጋል፤ ሁል ጊዜ ጸንቶ ይቆማል።
ፍቅር ከቶ አይወድቅም፤ ነገር ግን ትንቢት ቢሆን ይሻራል፤ ልሳንም ቢሆን ይቀራል፤
ዕውቀትም ቢሆን ይሻራል። ምክንያቱም የምናውቀው በከፊል ነው፤ ትንቢት የምንናገረውም በከፊል ነው። ነገር ግን ፍጹም
የሆነው ሲመጣ በከፊል የነበረው ይሻራል።”
ስጠቀልለው እውነተኛ ክርስትና ማለት በፍቅር መመላለስ ማለት ነው። ወይም ደግሞ እውነተኛ
ክርስትና በአንድ ቃል ግለጹት ከተባልን “ፍቅር” ብለን መግለጸ እንችላለን። ደግሞም ኢየሱስ ይህን ፍቅር በተግባር አሳይቶናል።
በፍቅር በመኖር፣ እርስ በርሳችን በመዋደድ፣ አልፎም ጠላቶቻችንን በመውደድ ፍሬ ያለው እውነተኛ ክርስትናን እንኑር፣ አስመሳይ፣
ሁኔታንና አመቺ ጊዜን ተጠቅመን ግላዊ ጥቅምን ብቻ የሚሳድዱ ክርስቲያኖች ከመሆንም ከእንደዛ አይነቶቹም እንጠበቅ።
”ጸሓፊውም እንዲህ አለው፤
“መምህር ሆይ፤ መልካም ብለሃል፤ እርሱ አንድ መሆኑን፣ ከእርሱም ሌላ አለመኖሩን መናገርህ ትክክል
ነው፤ እርሱን በፍጹም ልብህ፣
በፍጹም አእምሮህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ መውደድ፣ እንዲሁም ባልንጀራህን እንደ ራስህ መውደድ
ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች ይበልጣል።”“ ማርቆስ 12፡ 32 — 33