እኛ ለእናንተ
ፍቅር እንዳለን ሁሉ እርስ በርስ ያላችሁን ፍቅርና ለሌሎችም ያላችሁን ፍቅር ጌታ ያብዛላችሁ፤ ያትረፍርፍላችሁም። 1 ተሰሎንቄ
3:12
በመጀመሪያ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ማንንም ቡድን ወይም ግለሰብ ለመንቀፍ ወይም የማንም ትምህርት
ላይ ጣት ለመቀሰር እንዳልሆነ ለአንባቢዎቼ ለማስገንዘብ እፈልጋለሁ። በዚህ ጦማር ላይ የሚወጡ ማንኛውም ጽሑፎች ሃሳብንና አስተሳሰብን
የሚሞግቱ ብቻ እንጂ ከግለሰብ፣ ከድርጅት ወይም ከማንኛውም ቡድን ጋር ጠብ የሌላቸው እንዲሁም ያልወገኑ መሆናቸውን ከወዲሁ ማሳሰብ
እወዳለሁ።

ክርስትናን ከሌላው እምነት የሚለየው ዋናው ነገር ክርስቶስ በሞቱ ሞትን ድል ነስቶ በትንሳኤው
ድል አድራጊነቱን አረጋግጦ ፈጽሞ ወዳለቀ ስራ የጠራን መሆኑ ነው። ክርስቲያን አሁን ሰይጣንን ድል ለማረግ ሳይሆን የሚተጋው፣ በክርስቶስ
ያገኘውን ድል ለመውራስ ነው የሚተጋው። በረከትን፣ ከፍታን፣ ሞገስን በክርስቶስ ወራሾች ሆነናል ስለዚህ ዓመት በተቀየረ ቁጥር የመውረስ፣
የመባረክ እያልን ከመታገል ይልቅ የሚበጀን የተሰጠንን የምንወርስበት ዓመት እንዲሆንልን ምን እናድርግ ብለን የምንጠይቅበት እንዲሆ
እመክራለሁ። በመጀመርያ እስከዛሬ ባለፉት ዓመታት ያልናቸው ተፈጽመዋል ወይ ብለን ቆም ብለን የምንጠይቅበት ዓመት ይሆንልን ዘንድ
እየተመኝሁ፣ የዚህ ዓመት መርሗችንን ከሁሉ በላይ የበረከት፣ የከፍታ፣ የሞገስ፣ የመላቅና የመውጣት ቁልፍ የሆነው እርስ በርስ ያለን
ፍቅር እና ለሌሎችም ያለን ፍቅር የሚበዛበትና ብሎም የሚትረፈረፍበት ዓመት ብለን ብናውጀው፥ አንድም ካለንበት የድንብርብር ኑሮ
ሳያመን እንወጣለን፣ ደግሞም በተጨማሪ እስካዛሬ ስንመኘው ስንናፍቀው ወደቆየነው፣ ይዘነው እንዳልያዝነው ወደ ቆጠርነው የበረከትና
የከፍታ ኑሮ ይዞን ይገባል።
በመጀመርያ ለምን ያለፉት ዓመታት እንዴት አለፉ ብሎ መጠየቅ ለምን ያስፈልጋል? በእኔ አስተሳሰብ
የኋላውን የማያውቅ የወደፊቱን ለመቀበል ዝግጁ አይሆንም። በእርግጥ ያልነው ሆኗል ብለን የእውንት መመርመራችን ለሁለት ዋና ዋና
ነገሮች ይጠቅመናል። አንዱ ልክ ወይም ስህተት መሆናችንን ለማወቅ ሲጠቅመን ሌላው ደግሞ ለወደፊት እይታችንን እንዴት እንደምናስተካክል
ትምህርት ይሰጠናል።
ለምን ፍቅር በዝቶ
ይትረፍረፍ? ምክንያቱም ክርስትና ፍቅር ስለሆነ። መጽሓፍ ቅዱስ እንደሚናገረው እግዚአብሄር ፍቅር ነው። ፍቅር ከመሆኑም የተነሳም
“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን
እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና፤” ዮሓንስ 3:16። ማርቆስ 12 ላይ ክርስቶስ ፍቅር የህግ ሁሉ መጠቅለያ ለመሆኑ እንዲህ አለ “ከሁሉ የሚበልጠው
ይህ ነው፤ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤ አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣
በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ።’ ሁለተኛውም ይህ ነው፤ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።’ ከእነዚህም የሚበልጥ
ትእዛዝ የለም።” ማርቆስ 12፡29 — 31። ምን ማለት ይሆን? እኔ የገባኝን አጠርና ቀለል ብሎ እነሆ።
ጌታ አምላክን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ መውደድ ማለት
ሁሉ ነገራችንን ለእግዚአብሄር ማስገዛት ማለት ነው። በሁሉ ነገር ለእርሱ ከተገዛን የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም የሚከብደን አይሆንም ስለዚህ
ፈቃዱን ስንፈጽም ወደ ርስታችን ገባን ማለት ነው። እግዚአብሄርን ለመውደዳችን ሌላው ማረጋገጫ ደግሞ ባልንጀራችንን በውደዳችን ነው።
ባልንጀራችንን መውደዳችን ደግሞ ምን ያህል እራሳችንን እንደምንወድ ያሳያል። እስቲ እናብራራው፣ ”ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ“ ያለን እግዚአብሔር ስለሆነ እኛም እርሱን ስለምንወድ ለቃሉ እንታዘዛለንና በራሳችን ላይ
ሊሆንብን የማንፈልገውን ባንጀራችን ላይ እንዲደርስበት አንፈልግም። ስለዚህም በአስርቱ ትዕዛዝ ላይ ያሉትን ስምንቱን ለመፈጸም አንቸገርም
ማለት ነው። እኛ ደግሞ እንታዘዝ እንጂ በጸጋ ዘመን ላይ ስለሆንን መንፈስ ቅዱስ ራሱ ያግዘናል። ባልንጀራየን አላማም፣ ክፉ አላስብበትም፣
አላመነዝርም፣ አልሰርቅም ወዘተ። ይልቁን ያለኝን አካፍላለሁ፣ መልካም ነው ብዬ ያሰብኩትን ሁሉ ለባልንጀራዬ አደርጋለሁ፣ እያየሁ
እንዳላየሁ ማለፍ አቆማለሁ፣ ከክፋት ጋር አልተባበርም፣ ለተጎዱ መቆርቆር እጀምራለሁ፣ ባልቴቶችንና ወላጅ የሌላቸውን ህፃናት እየፈለኩ
መርዳት እጀምራለሁ፣ የተራቡ አበላለሁ፣ የታረዙ አለብሳለሁ እያለ ይቀጥላል። እስቲ አስቡት እኔ ክርስቲያን ነኝ ብሎ የሚናገር ሁሉ
በ2010 እኔ አፈቅራለሁ ብሎ ወገቡን ታጥቆ ቢነሳ በ2011 ላይ የድል፣ የመጣስ፣ የመባረክ፣ የከፍታ፣ የሞገስ እያልን የተመኘናቸውን
ዓመታቶች ሁሉ ሳናስበው አጠገባችን እናገኛቸው ነበር። ለነገሩማ ቃሉም የሚለው ያን አይደል፥ “አስቀድማችሁ የእግዚአብሄርን መንግስትና ጽድቁንም ፈልጉ
እነዚህ ሁሉ ይጨመርላችኋል።“ ማቴዎስ 6:33 እነዚህ ሁሉ የሚላቸው ምድራዊ የሆኑ በረከቶችን ነው።
ስለዚህ አፈቃሪዎች ለመሆን ምን እናድርግ? መልሱ ፍቅርን እንወቅ ነው። ታዲያ ፍቅርን እንዴት ነው የምናውቀው? ፍቅር የሆነውን ክርስቶስን በማወቅ። ክርስቶስን ስናውቀው ከርሱ ፍቅር
ይይዘናል፣ ምክንያቱም ፍቅር የሚያሲዝ ልዩ የሆነ ግርማ ስላለው። በቃ ከርሱ ፍቅር ከያዘን እኛም ልክ እንደርሱ አፍቃሪ ለመሆን
ምንም አይከብደንም። ይበልጥ ባወቅነው ቁጥር አፍቃሪነታችን ይበልጥ ይበረታል። የሚገርመው ይህ ማርቆስ 12 ላይ ከክርስቶስ ጋር
ስለ ትዕዛዛቶች መበላለጥ የሚጠይቀው ፀሃፊ የክርስቶስን መልስ ሰምቶ መምህር ሆይ መልካም ብለሃል ብሎ ከመለሰለት በኋላ ክርስቶስ
ፀሃፊውም “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” ብሎ ነበር የመለሰለት።
”ጸሓፊውም እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ መልካም ብለሃል፤ እርሱ አንድ መሆኑን፣
ከእርሱም ሌላ አለመኖሩን መናገርህ ትክክል ነው፤ እርሱን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም አእምሮህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ
መውደድ፣ እንዲሁም ባልንጀራህን እንደ ራስህ መውደድ ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች ይበልጣል።”
ኢየሱስም
በማስተዋል እንደ መለሰለት አይቶ፣ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው። ከዚህ በኋላ ሊጠይቀው
የደፈረ ማንም አልነበረም።“ ማርቆስ 12:32 — 34
የ2010
ጸሎቴ ያገሬን ሕዝብ የአዲስ አመት መርሖውን ከይሁንልን ወደ እንሁን እንዲለውጠው ነው። የዚህ ዓመት መርሗችንን ከሁሉ በላይ የበረከት፣
የከፍታ፣ የሞገስ፣ የመላቅና የመውጣት ቁልፍ የሆነው እርስ በርስ ያለን ፍቅር እና ለሌሎችም ያለን ፍቅር የሚበዛበትና ብሎም የሚትረፈረፍበት
ዓመት ብለን ብናውጀው፥ አንድም ካለንበት የድንብርብር ኑሮ ሳያመን እንወጣለን፣ ደግሞም በተጨማሪ እስካዛሬ ስንመኘው ስንናፍቀው
ወደቆየነው፣ ይዘነው እንዳልያዝነው ወደ ቆጠርነው የበረከትና የከፍታ ኑሮ ይዞን ይገባል።
ጳውሎስ
ለተሰሎንቄ ሰዎች የፀለየውን እኔም ለአገሬ ልጆች ልፀልይና ላጠቃልል፥ እርስ በርስ ያላችሁን ፍቅርና ለሌሎችም ያላችሁን ፍቅር ጌታ
ያብዛላችሁ፤ ያትረፍርፍላችሁም።