Wednesday, June 1, 2016

በናፍቆት የሚጠበቅ

ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በናፍቆት ይጠባበቃል። ሮሜ 8:19

ፍጥረት በናፍቆት የሚጠባበቀው ምናችንን ይሆን? በእርግጥ ይህን ጥያቄ ብዙ ጊዜ ለራሴ እጠይቃለሁ። ምናልባትም ሌሎች ሰዎችም ብዙ ጊዜ ይጠይቁ ይሆናል። አዎ በየጊዜው መልስ የሆናሉ ብዬ ያቀረብኩዋችው ብዙ ነገሮች ነበሩ። ለምሳሌ አምልኳችንን፣ ኑሯችንን፣ መውጣት መግባታችንን፣ ጽድቃችንን የመሳሰሉትን። በሁሉም መልኩ በመልካም ሁኔታ መገለጡ ጥሩ ነው። ከሁሉ በላይ ግን ፍጥረት ሁሉ በናፍቆት የሚጠብቁት በየትኛውም ቦታ በየትኛውም ጊዜ ሳንዛነፍ በፍቅር የምንገለጥበትን ጊዜ ይጠበቃሉ። የሁሉ ነገር መጠቅለያው፣ በምንሰራው ማንኛውም ነገር ውስጥ ስንጨምረው መልካም ተጽዕኖ የሚኖረው ፍቅር ነው።

በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና፤ እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው በዓለም ለመፍረድ ሳይሆን፣ ዓለምን በእርሱ ለማዳን ነው። ዮሐንስ 3:16-17


እግዚአብሔር ሁልቀን የማይቀያየር ፍቅሩን በማሳየት እንድንገለጥ በፀጋው ይርዳን።

Sunday, May 29, 2016

እኔ ከአንተ ጋር ነኝ

‘እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ። አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ።’ ኢሳያስ 41:10

እግዚአብሔር አትፍራ ሲለን ሁልጊዜም የሚያስከትለው ማስተማመኛ 'እኔ ከአንተ ጋር ነኝ' የሚለውን ነው። የማንፈራበት አንደኛው እና ብቸኛው ምክንያትም ይኸው ነው። አንዳንዴ በሸለቆ ውስጥ ስናልፍ እግዚአብሔር የተወን ይመስለናል ነገር ግን እግዚአብሔር በተራራ ላይ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ጊዜ አብሮን አለ። እስኪ ለምሳሌ እንዲሆነን ከብዙ ታሪኮች ውስጥ አንዱን የዮሴፍን ታሪክ እንመልከት። ዮሴፍ የተስፋ ቃል የነበረው በሕልምም የተመሰከረልለት ነበረ። ወንድሞቹ ከሸጡት በኋላ ከነጋዴዎቹ ከንደገና ለጲጥፋራ ተሸጠ። ከዛም በዚህ ባለስልጣን ቤት ውስጥ ማገልገል ጀመረ፤ በዛም ወቅት ዮሴፍ ኑሮው መልካም ረ። በዘፍጥረት 38 እንደምናየው ከዚህ በላይ ምን ይፈልጋል እስክንል ድረስ የዮሴፍ ኑሮ ተቃንቶለት ነበር። እንደምናነበውም በዛን ወቅት በእርግጥም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበር።

‘እግዚአብሔር (ያህዌ) ከዮሴፍ ጋር ነበረ፤ ኑሮው ተቃናለት፤ እርሱም በግብፃዊው አሳዳሪው ቤት ኖረ። አሳዳሪውምእግዚአብሔር (ያህዌ) ከእርሱ ጋር እንዳለና ሥራውንም ሁሉ እንዳከናወለት ባየ ጊዜ፣ ዮሴፍ በእርሱ ዘንድ ሞገስ አገኘ፤ የቅርብ አገልጋዩም ሆነ። ጲጥፋራ በቤቱ ላይ ሾመው፤ ያለውንም ሀብት ሁሉ በኀላፊነት ሰጠው። ዮሴፍ በጲጥፋራ ቤትና ባለው ሀብት ሁሉ ላይ ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር (ያህዌ) የግብፃዊውን ቤት ባረከ፣ የእግዚአብሔርም (ያህዌ) በረከት በግቢም በውጭም ባለው የጲጥፋራ ሀብት ንብረት ሁሉ ላይ ሆነ። ስለዚህ ጲጥፋራ ባለው ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጠው፤ የቀረበለትንም ከመመገብ በስተቀር፣ ማናቸውንም ጒዳይ በዮሴፍ ላይ ጥሎ ነበር።’ ዘፍጥረት 38:2-8

ነገር እግዚአብሔር በዛን ወቅት ብቻ ነበርን? ብለን ብንጠይቅ መልሱ፣ በፍጹም ነው። ምክንያቱም ዮሴፍ ወደ እስር ቤት በተጣለበትም ጊዜ የምናየውም ነገር እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንደነበረ ነው።

‘ይሁን እንጂ ዮሴፍ እዚያ እስር ቤት ባለበት ጊዜ ሁሉ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ቸርነቱንም አበዛለት፣ በወህኒ አዛዡም ዘንድ ሞገስን ሰጠው። ስለዚህ የወህኒው አዛዥ ዮሴፍን የእስረኞች ሁሉ አለቃ አደረገው፤ በእስር ቤቱ ላለውም ነገር ሁሉ ኀላፊ ሆነ። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከዮሴፍ ጋር ሆኖ ሥራውን ሁሉ ያሳካለት ስለ ነበር፣ የወህኒ ቤት አዛዡ በዮሴፍ ኀላፊነት ሥር ስላለው ስለማንኛውም ጒዳይ ሐሳብ አይገባውም ነበር። ዘፍጥረት 38:21-23

ስለዚህ ያለንበት ሁኔታ የሚነግረን እንኳን በቃ እግዚአብሔር ትቶሃል ይኸው ነገሮች እየተሳኩለህ አይደለም የሚል ቢመስልም እውነቱ ግን በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ እግዚአብሔር አብሮን እንዳለ ነው።

‘እግዚአብሔር (ያህዌ) ራሱ በፊትህ ይሄዳል፤ ከአንተም ጋር ይሆናል፤ ፈጽሞ አይለይህም፤ አይተውህምም፤ አትፍራ፤ ተስፋም አትቍረጥ።ዘዳግም 31:8